የመገናኛ ብዙኃን ሙሉ በሙሉ ባልተስፋፋባቸው ወይም የማኅበረሰቡን የዕለት ተለት ጉዳዮች የሚሸፍኑ መገናኛ ብዙኃን በሌሉባቸው የሀገራችን አካባቢዎች ለማኅበረሰቡ ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት የሚሠራጩ የማኅበረሰብ ሬዲዮንና ቴሌቪዥን አገልግሎቶችን ማስፋፋት፤ ለማኅበረሰቡ ወቅታዊ መረጃ በማቅረብ፣ በማስተማር እና በማዝናናት ፈጣንና ቀጣይነት ላለው ሁለንተናዊ ዕድገት ቁልፍ የሆነውን በመረጃ የበለፀገ ሕብረተሰብ በመፍጠር በአገራችን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን በማመን፤
ሀገራችን የበርካታ ብሔረሰቦች አገር በመሆኗ፤ የአገራችንን ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጥቅም መሠረት ያደረገ፣ ብዝኃነቱ የተረጋገጠ፣ ጥራቱን የጠበቀ፣ ተደራሽና ቀጣይነት ያለው የማኅበረሰብ ብሮድካስት አገልግሎት እንዲስፋፋ ልዩ ትኩረት በመስጠት መንቀሳቀስ የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል በመሆኑ፤
በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 30 መሠረት በማኅበረሰብ የብሮድካስት አገልግሎት ሥራ ለመሠማራት የማኅበረሰብ ብሮድካስት ፈቃድ ማግኘት በማስፈለጉና ፈቃድ አሰጣጥ ሒደቱን ግልፅ፣ ፍትሐዊ፣ አሳታፊ እና የሃሳብና የመረጃ ብዝኃነትን የሚያስፋፋ እንዲሆን ማድረግ በማስፈለጉ፤
በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 6(1)፣ (5) እና 31(1)(መ)፡(2)፤ መሠረት የማኅበረሰብ ብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ በመስጠት መገናኛ ብዙኃንን ማስፋፋት እና ባለፈቃዶችም የሙያዊ ሥነ-ምግባር፣ ሕገ መንግስቱን፣ የአገሪቱን ሕጎች እንዲሁም፤ የሕዝብን ሰላም፣ ደኅንነት፣ የዜጎችን ተነፃፃሪ መብቶችና ጥቅሞች ባከበረ መልኩ በኃላፊነት ስሜት ሥራቸውን ማከናወናቸውን ማረጋገጥ በማስፈለጉ፤
በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 12(7) እና አንቀጽ 90(2) መሠረት ይህ መመሪያ በባለሥልጣኑ ቦርድ ወጥቷል፡፡