የሥነ-ምግባር ደንብ የአንድ ተቋም ሰራተኞች ከአመራሩ፣ ከደንበኞች፣ ከአጋር አካላት እንዲሁም ከሌሎች ሰራተኞች ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት በሚደነግግ መልኩ የሚቀርፅ መመሪያ ሆኖ ሰራተኞች የተሰጣቸውን ተግባር ሲያከናውኑ የሚኖራቸውን ጠንካራ አንድነትና መንፈስ፣ በስራ ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የፍላጎት ግጭቶችን እንዴት ማስወገድ እንደሚገባ እንዲሁም ሰራተኞች በህዝባዊ አገልግሎት እና በግላዊ ህይወታቸው በሚኖራቸው እንቅስቃሴ ረገድ ስለሚጠበቀው መልካም ባህሪ የሚገለፅበት ደንብ ነው፡፡
ለዚህ ደንብ ውጤታማነት አመራሩ የስራ ኃላፊዎች የስራ ክፍላቸውንም ሆነ ሰራተኞቻቸውን በአግባቡ ማስተዳደር እና በሥነ-ምግባር ማነፅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የስራ ሀላፊዎች ሰራተኞች ይህን የሥነ-ምግባር ደንብ ያመኑበት፣ የተቀበሉትና ለደንቡ ተገዥ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል የሥነ-ምግባር ደንብ አብይ ዓላማው በአንድ ተቋም ውስጥ ያሉ ሰራተኞችን አርአያነት ያለው የአገልግሎት ሥነ-ምግባር ማበልፀግ፣ ማበረታታት እና መገንባት ነው፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ የተቋም መልካም ስም ይገነባል፣ አገልግሎቶች ተደራሽ ይሆናሉ፡፡ የአንድን ተቋም መልካም ስም ጠብቆ ለማቆየት ሰራተኞች በየትኛውም ሁኔታና ሰዓት ከፍተኛ በሆነ የሥነ-ምግባር አኳኋን ስራቸውን በአግባቡ ሲሰሩና አገልግሎት ሲሰጡ ነው፡፡ ይህ የስነ-ምግባር ደንብ ሰራተኞች በግላቸውም ሆነ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር የተሰጣቸውን ተግባራት በሚያከናውኑበት ጊዜ የሚቃኝበት የስነ-ምግባር መመሪያ ነው ማለት ይቻላል፡፡