የፌደራል የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩት በአዋጅ ቁጥር 1071/2010 እንዲቋቋም ሲደረግ ከዚህ በፊት በተለያዩ ተቋማት በተበታተነ ሁኔታ ይሰሩ የነበሩ የሕግ ጥናትና፣ የፍትሕ አካላት ባለሙያዎች ሥልጠና፣ የፍትሕ ሥርዓት እና የሕግ ትምህርት ማሻሻያ ተግባራትን በማጠቃለል በአንድ ተቋም እንዲከናወኑ ማድረግ በተቋማቱ መካከል ያለውን የኃላፊነት ድግግሞሽ ማስቀረት ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚረዳ በመገንዘብ እንደሆነ ይታሰባል፡፡
ኢንስቲትዩቱ የተቋቋመበትን ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲችል በአዲስ ስያሜ አዲስ አደረጃጀት በማዘጋጀት በመንግሥት እንዲጸድቅ ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ ኢንስቲትዩቱን ዓላማ በማስፈጸም ሥራ ላይ የሚሠማሩ ባለሙያዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እና የሌሎች መሰል የምርምር ተቋማትን መሠረታዊ መርሆዎች ተከትሎ በመንግሥት በሚጸድቅ መመሪያ መሠረት እንዲሁም ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች በመንግሥት ሰራተኞች ሕግና አሠራር መሠረት እንደሚቀጥርና እንደሚያስተዳድር የተመለከተ ቢሆንም ከዚህ በተፈቀደው አደረጃጀት ጉድለት ያለበት በመሆኑ ለአማካሪ ምክር ቤት አቅርበን ችግሩን በመረዳት አቅጣጫ መሰጠቱ አንድ እርምጃ ወደፊት እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ነባሩን መዋቅር ጠበብ በማድረግ የተሻለ አቅም ያላቸውን ባለሙዎች ለመሳብ የሚያስችል የደመወዝ ስኬልና ጥቅማጥቅም መነሻ ጥናት ፕሮፖዛል ለመንግሥት በቅርብ ጊዜ ውስጥ በማቅረብ ይሁንታ ለማግኘት እንደምንችል ሙሉ እምነት አለን፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌዴራል የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩቱ በዚህ በጀት ዓመት የሥልጠና ማዕከል ከሌላቸው ስድስት ክልሎች በቁጥር ውስን የሆኑ ቅድመ-ሥራ ሠልጣኞችን በመቀበል ለዳኝነትና ለዐቃቤ ሕግነት እንድያበቃቸው ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ለሰልጣኞች ወቅቱን ያገናዘበ የኪስ ገንዘብ አከፋፈልና የጥቅማጥቅም አሰጣጥ ሥርዓት ያልተበጀ በመሆኑ በሥራ ሂደት ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም በሥራ ላይየነበረውን መመሪያ ማሻሻል አስፈላጊ በመሆኑ ይህ መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡