በአገራችን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ቁልፍ ሚና የሚጫወት ሲሆን የኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት በማሳደግ ለአገር ልማት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማጎልበት በዘርፉ ያሉትን ዋና ዋና ችግሮች መፍታት ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ፤
ዘርፉ በዲዛይን ዝግጅት፣ በግብዓት አጠቃቀምና በግንባታ ወቅት የሚከሰት የገንዘብና የጊዜ ብክነትን ለመቀነስ፣ ጥራት ያለው የግንባታ ውጤት ለማስገኘት እንዲሁም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ በቂ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸውን አነስተኛና መለስተኛ ባለሙያዎችን የሚያስፈልግ በመሆኑና እነዚህ ባለሙያዎች የሚበቁበትና የሚመዘኑበት የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት እና ከዚህ ቀደም ተግባራዊ የተደረገው መመሪያ ቁጥር 20/2005 ውስጥ የታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት የሙያ ብቃትና የምዘና ሥርዓቱ የተሻሻለ እንዲሆን ማድረግ በማስፈለጉ፣
መመሪያው ከፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ ጋር በመመካከር በአገር አቀፍ ደረጃ በትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ወጥተው እየተሠራባቸው ከሚገኙ መመሪያዎች በተለይም ውጤት ተኮር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ሥርዓቱን ለመተግበር ከወጣው የሙያ ብቃት ምዘና መመሪያ ጋር እንዲጣጣም ማድረግ በማስፈለጉ፣
የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በሕንጻ አዋጅ ቁጥር 624/2001 አንቀጽ 26 እና ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም በወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሕንጻ ደንብ ቁጥር 243/2003 አንቀጽ 20 ላይ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህን የተሻሻለ መመሪያ ቁጥር 001/2009 አውጥቷል፡፡