የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የካቲት 2008 ዓ.ም በአዲስ መልክ ተቋቋሟል፡፡ ኤጀንሲው የሚያከናወናቸውን ተግባርና ኃላፊነት በደንብ ቁጥር 374/2008 የተሰጡት በመሆኑ ይህንኑ ለማስፈጸም እንዲያግዘው መዋቅራዊ አደረጃጀቱን በማጥናት ለመንግሥት በማቅረብ አጸድቋል፡፡
በዚሁ መሠረት ለኤጀንሲው የተዘጋጀውን መዋቅራዊ አደረጃጀት ተግባራዊ ለማድረግ እና እያንዳንዱ ሠራተኛ ይበልጥ ውጤታማ ሊሆን በሚችልበት የሥራ መደብ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለመመደብ እንዲያስችል የድልድል መመሪያ ማዘጋጀት አስፈልጓል፡፡ የድልድል መስፈርቱ ሲዘጋጅ ለመስሪያ ቤቱ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማስፈጸም የተቀመጡ አቅጣጫዎች፣ የዘርፉን እና የሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እንዲሁም የሌሎች ተቋማት ተሞክሮዎችን በመውሰድ እና የመስሪያ ቤቱን ተጨባጭ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ተለይተው ተቀምጠዋል፡፡ በተፈቀደው መዋቅራዊ አደረጃጀት ላይ የሠራተኞችን ድልድል ለማከናወን የተለዩት የድልድል መስፈርቶችም በተቻለ መጠን ሊለኩ የሚችሉ እንዲሆኑ ጥረት ተደርጓል፡፡
በመሆኑም በከተሞች የሥራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የተያዘውን ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ለማሳካት የሠራተኛውን የሥራ ባህሪ፣ ከሠራተኛው የሚጠበቁ የስነምግባር ሁኔታዎች፣ የሠራተኛው የሥራ አፈጻጸም ውጤትና የማህደር ጥራት ታሳቢ በማድረግ እያንዳንዱን ሠራተኛ ለመመዘን የሚያስችሉ መስፈርቶችንና መለኪያዎችን የያዘ የድልድል መመሪያና መስፈርት የፕብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ህዳር 2000 ዓ.ም ያወጣውን የመንግሥት ሠራተኞች የደረጃ ዕድገት አፈጻጸም መመሪያ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 1 መነሻ በማድረግ ሚኒስቴሩ በኤጀንሲው ማቋቋሚያ በደንብ ቁጥር 374/2008 ዓ.ም አንቀጽ 14 በተሠጠው ሥልጣን መሠረት ይህን መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡