የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ በከተማው የአስተዳደር ወሰን ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሞተር ብስክሌቶች በከተማው ነዋሪና የትራፊከ እንቅስቃሴ ላይየሚፈጥሩትን አላስፈላጊ ተፅዕኖ ለመቀነስ የሞተር ብስክሌት ፈቃድና ቁጥጥር መመሪያ 04/2011 ተግባራዊ ሲደረግ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በአገልግሎቱ መቋረጥ ምክንያት ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር መዳረጋቸውን በጊዜ ሂደት በመረዳት የቁጥጥር ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ አገልግሎቱ ህጋዊ አደረጃጀትና ፍቃድ ኖሮት ማስቀጠል የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
በዚሁ መሠረት ማሻሻያ የትግበራ ጥናት ግኝቶች ማረጋገጥ በመቻሉ፤ እንዲሁም የኤሌክትሪከ ሞተር ሳይክልን በተመለከተ የተካተቱ ድንጋጌዎች በመኖራቸው እና ከሁለት ዓመት በኋላ ማንኛውም ሞተር ሳይክል ወደ ኤሌክትሪከ እንደሚቀየርና አዲስ ፈቃድ ለኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክ ብቻ እንደሚሰጥ የሚደነግግ በመሆኑ፤
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርአስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 84/2016 አንቀጽ 16 ንዑስ አንቀጽ 2 ተራ ፊደል (ሠ) መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡