የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንብረት የሆኑትን የመንግሥት የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ትክክለኛ መረጃዎችን በማደራጀት በተገቢው በማስተዳደር ዝቅተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል፣ ወጣቶችን፣ ሴቶችንና ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የአካል ጉዳተኞችን ከቤት አስተዳደር ሥርዓቱ ይበልጥ ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥ አሠራር መፍጠር በማስፈለጉ፤
የከተማው አስተዳደር ቤቶች እድሳት ሳያገኙ በመቆየታቸውና በከተማ ማደስ ፕሮግራም አማካይነት እየፈረሱ ያለበት ሁኔታ በአግባቡ በመለየትና መረጃቸውን በመያዝ ቀጣይ የቤት ግንባታ ዕቅዶችና አቅጣጫዎችን ለመቀየስ የሚያስችል አቅም እንዲኖር ማድረግ በማስፈለጉ፤
የከተማው አስተዳደር ቤቶች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አያያዝና አጠባበቅ ሁኔታ ለክትትልና ቁጥጥር አመቺ እንዲሆን በማድረግ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የመንግሥት ቤቶችን ያለአግባብ መጠቀምና ወደ ግል ይዞታ የማዞር ሕገ ወጥ ተግባራትን በመግታት የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ በማስፈለጉ፤
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈጻሚ አካላትን እንደገና ለማደራጀት፣ ሥልጣንና ተግባራቸውን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 64/2011 አንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ (3) (ሠ) በተሠጠው መሠረት ይህን መመሪያ አውጥቷል፡፡