አዲስ አበባ የሀገራችን ርዕሰ ከተማና የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማዕከል ብሎም የአፍሪካ እና የተለያዩ ኣገራት ኢምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ ናት። በመሆኑም በከተማችን ያለው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ የተሳለጠ እንዲሆን የከተማው ትራንስፖርት ጉልህ ሚና አለው። ሰለሆነም የከተማችን የትራንስፖርት ስርዓት ከተማዋ ላለችንበት እድገትና ላላት ዓለም አቀፍ ቦታ በሚመጥን ደረጃ እያደገ ያለ ሲሆን በየጊዜዉ ለሚነሱ ማህበረሰባዊ ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችሉ አሰራሮች መዘርጋትም ያስፈልጋል።
በአሁኑ ሰዓት በከተማችን ካለው የትራንፖርት ፖሊሲ በተቃራኒ እያደገ የመጣዉ የሞተረ ብስከሌት ትራንስፖርት ስርዓት የተለያዩ ማህበረሰባዊ ችግሮች እያስከተለ ይገኛል። በከተማችን ያለዉ መሰረተ ልማት ከሞተር ብስክሌቶች ፈጣንና ተለዋጭ እንቅስቃሴ ኣንፃር አመቺ ያልሆነና ለአደጋ የተጋለጠ ነው። በመሆኑም ከሞተር ብስክሌቶች ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የትራፊክ አደጋዎች መጨመር በተለይም ተገቢውን የመንገድ ደኅንነት መርሆዎች እና ሕግ ተከትለው ስለማያሽከረከሩ እንዲሁም ከፍላጎታቸው እና ከመጠናቸው ማነስ የተነሳ በሌሎች ተሸከርካሪዎች እይታ ስር ስለማይወድቁ ለአደጋ እየተጋለጡ ይገኛሉ። አደጋ ሲከሰትም የመትረፍ እድላቸው ዝቅተኛ ከመሆኑም ባለፈ ቢተርፉም ለከፍተኛ የአካል ጉዳት ስለሚዳረጉ ለከፍተኛ ስነልቦናዊና ማኅበራዊ ጉዳት ይዳረጋሉ። የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች እራሳቸውን ለአደጋ ያጋለጡ ከመሆናቸውም ባለፈ ከዋናው የተሽከርካሪ መንገድ በመውጣት በእግረኛ መንገዶች ላይ እየተሽለኮለኩ ለማሽከርከር በሚያደርጉት ሀገ ወጥ ተግባር እግረኞችን ለአደጋ እያጋለጡ በመሆኑ፤
ሞተር ብስክሌቶች ለግል አገልግሎት ከመዋል ያለፈ በሕዝብ ትራንስፖርት ለመሰማራት የሚስችል አሠራር የሌለ ቢሆንም በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች በህገወጥ ትራንስፖርት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን በመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ ቁጥጥር ሂደትም በመጠን ትንሽ ከመሆናቸው በከፍተኛ ፍጥነት የሚንቀሳቀሱና በፍጥነት መቆጣጠሪያ ራዳርም ጭምር በቀላሉ የማይያዙ በመሆናቸው እንዲሁም ሕግን አክብረው ለተቆጣጣሪው አካል ለመታዘዝ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የተነሳ አርምጃ ለመውሰድ ችግር እየፈጠሩ በመገኘታቸው፤
በከተማችን ውስጥ ምንም እንኳን የኮድ 2 ሞተር ብስክሌቶች ምዝገባ ማካሄድ የተቋረጠ ቢሆንም ከሌሎች ክልሎች ምዘገባ በማካሄድ ወደ ከተማችን የሚገቡ የሞተር ብስክሌቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆኑ ከሌሎች ተሸከርካሪዎች እደጎት አንፃር ሲታይ በሁለት አጠፍ እድገት እያሳየ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህም በከተማዋ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ ስጋቶችን እና ተጨባጭ ችግሮችን እየፈጠረ በመሆኑ፤
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሞተር ብስክሌቶች በመጠቀም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በገበያ ማዕከላት፣ በትምህርት ቤቶችና የመንግሰትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት አካባቢ የሚደረግ ዘረፋና ስርቆት እንዲሁም ህገ ወጥ ድርጊቶችን የመፈፀም ዝንባሌ እየተበራከተ በመምጣቱ የተነሳ በዜጎች ላይ እተፈጠረ ያለውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ-ልቦናዊ መታወክ ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎች በመንግሥት በኩል መሠራት ያለባቸው በመሆኑ፤
የከተማችን የትራንስፖርት አገልግሎት የበለጠ ተወዳዳሪ ደህንነቱ የተጠበቀና ብቃት ያለው ሆኖ እንዲራመድ ተገቢው ክትትልና ድጋፍ የሚጠይቅ በመሆኑ እንዲሁም የከተማውን የትራንስፖርት አገልግሎት በማዘመን የትራፊክ ማኔጅመንት ስራውን ለማቀላጠፍ እንዲቻል በአዲስ አበባ ከተማ የሞተር ብስከከሌቶች እንቅስቃሴን በመወሰን የፈቃድና ቁጥጥር አሠራርን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
በትራንስፖርት እዋጅ ቁጥር 468/1997 አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 3 ፊደል ተራ (ረ) እና (ሰ) ድንጋጌዎች መሠረት የሕዝብን ደኅንነት የሚጎዱ ተሸከርካሪዎችን እንቅሰቃሴ በተመለከተ ማገድ እንዲሁም ከተሞቹ የትራንስፖርት አገልግሎት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሌሎች ተግባራት ማከናወን እንዲችሉ የፌደራል የትራንስፖርት ባለሥልጣን የውክልና ሥልጣን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰጠው በመሆኑ፤
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአስፈፃሚ አካላትን እንደገና ለማደራጀት፣ ሥልጣንና ተግባራቸውን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 64/2011 አንቀጽ 15 ንዑስ እንቀፅ 3(14) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል።