በአዲስ አበባ ከተማ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓታት ላይ የሚታየው የትራፊክ መጨናነቅና አደጋ እንዲሁም የአካባቢ አየር ብከለት የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች እንዲሁም የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ ማንሳት አገልግሎት እና የውበትና መናፈሻ ቦታዎችን ውሃ የሚያጠጡ ተሽከርካሪዎች አስተዋጽኦ የጎላ በመሆኑና ይህንን መፍታት አስፈላጊ በመሆኑ እና የእነዚህን ተሽከርካሪ ወደ ከተማዋ መግባት የሚችሉበትንና በከተማው ውስጥ የሚንቀሳቀሱበትን ሰዓት በመወሰን ችግሮቹን መቅረፍ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
የተሽከርካሪዎችን እንቅሰቃሴ በሰዓት መገደቡ ፍስቱን ከማሻሻሉም በተጨማሪ በዚህ መመሪያ እንቅስቃሴያቸው የተወሰነላቸው ተሸከርካሪዎችም አገልግሎታቸውን በተቀላጠፈ ሁኔታና ሎጂስቲክስ ወጪን በሚቀንስ መልኩ ማከናወን እንዲችሉ አዎንታዊ ሚና የሚኖረው በመሆኑ፤
በትራንስፖርት አዋጅ ቁጥር 468/1997 አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 3 ፊደል ተራ (ረ) እና (ሰ) ድንጋጌዎች መሠረት የሕዝብን ደኅንነት የሚጎዱ ተሸከርካሪዎችን እንቅስቃሴ በተመለከተ ማገድ እንዲሁ ከተሞቹ የትራንስፖርት አገልግሎት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሌሎች ተግባራት ማከናወን እንዲችሉ የፌደራል የትራንፖርት ባለሥልጣን የውከልና ሥልጣን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰጠው በመሆኑ፤
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአስፈፃሚ አካላትን እንደገና ለማደራጀት፣ ሥልጣንና ተግባራቸውን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 64/2011 አንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ 3(ሠ) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል።