በሀገራችን የግንባታ ዘርፍ ማደግን ተከትሎ የሲሚንቶ ገበያ በተለያዩ ምክንያቶች በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ እና ሥርጭቱ እየተስተጓጎለና የዋጋ ንረቱ እየተባባሰ በመሄዱ የሲሚንቶ ገበያውን ለማረጋጋት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሲሚንቶ ግብይትን በተመለከተ መመሪያ ቁጥር 908/2014ን አውጥቶ ተግባራዊ ሲያደርግ ከቆየ በኋላ መመሪያው በተግባር ሲፈተሽ ሲሚንቶን በቀጥታ ከፋብሪካው የመግዛት እድል ያገኙ አካላት በዋጋም ሆነ በአቅርቦት ተጠቃሚ መሆን የቻሉ ቢሆንም በተመረጡ አቅራቢዎች ለህብረተሰቡ እንዲደርስ የተደረገው የሲሚንቶ ሥርጭት የተጠቃሚውን ፍላጎት ያላሟላ ከመሆኑም በላይ ለተለያዩ ህገወጥ አሠራሮች የተጋለጠ መሆኑን በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል ከተካሄደው የአፈፃፀም ፍተሻ ጥናት እንዲሁም ከህብረተሰቡና በዘርፉ ከተሰማሩ ባለድርሻ አካላት የቀረቡ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን በግብዓትነት በመውሰድ የቀድሞውን መመሪያ የተካውን አሁን በሥራ ላይ ያለውን የሲሚንቶ ግብይት መመሪያ ቁጥር 940/2015 አውጥቶ ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ሆኖም በአሁኑ ጊዜ የተሻለ አቅም ያላቸው የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወደ ማምረት ሥራ እየገቡ በመሆኑ ዘርፉን ለገበያው መተው አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በሥራ ላይ ያለውን የሲሚንቶ ግብይት ለመቆጣጠር የወጣውን መመሪያ ቁጥር 940/2015 መሻር አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ይህ የመሻሪያ መመሪያ ተዘጋጅቶ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ባለሙያዎች ከዳበረ በኋላ ለበላይ አመራሩ ቀርቦ ይሁንታ ተሰጥቶበት እንዲጸድቅ ተደርጓል፡፡
ስለሆነም የሚኒስቴር መ/ቤቱ የመመሪያውን አስፈላጊነት ተገንዝቦ በአስተዳደር ሥነሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 መሠረት እንዲመዘግብልን በአክብሮት አቅርበናል፡፡