የኮንትሮባንድ ወንጀል ማለት ምን ማለት ነው? ከሀገራችን የህግ ማዕቀፍ እንዴት ይታያል?

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

ሰላም ጤና ይስጥልን ውድ የኢ.ፌ.ድ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ገጽ ተከታታዮቻችን ብዙውን ጊዜ በተለያዩ የኤሌክትሮንክስና የዲጂታል ሚዲያዎች የኮንትሮባንድ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ክስ ተመሰረተባቸው በእስራትና በመቀጮም ተቀጡ ሲባልም እንሰማለን፡፡

ለመሆኑ የኮንትሮባንድ ወንጀል ሲባል ምን ማለት ነው? ከሀገራችን የሕግ ማዕቀፍ አኳያስ እንዴት ይታያል? በሚሉት ጉዳዮች ላይ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የጉምሩክ ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ቡድን መሪ ከሆኑት ከአቶ ደምሰው አሰፋ ጋር ቆይታ አድርገን ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥተውናል እንደሚከተለው ይቀርባል፡-

ኮንትሮባንድ ማለት ምን ማለት ነው? ብለን በዝግጅት ክፍላችን ላቀረብንላቸው ጥያቄ

ትርጓሜው የሕግ (የአዋጅ) ድንጋጌ መቃረን ማለት ነው ሲሉ አቶ ደምሰው ማብራሪያቸውን ይጀምራሉ፡፡

በሕግ ወደ ሀገር እንዳይገባ ወይም እንዳይወጣ የተከለከለ ዕቃ ፣ ከሀገር እንዳይወጣ ወይም ወደ ሀገር እንዳይገባ ገደብ የተደረገበት ዕቃ፣ የጉምሩክ ሥነ-ስርዓት ያልተፈፀመበት ዕቃን ማስገባት፣ በህጋዊ መንገድ ከሀገር የወጡ ዕቃዎችን በህገ-ወጥ መንገድ መልሶ ማስገባት፣ ከቀረጥና ታክስ ቅናሽ የገቡ ዕቃዎችን መልሶ ከሀገር ማስወጣት፣ እንዲሁም እነዚያን ህገ-ወጥ ዕቃዎች ማከማቸት፣ ማዘዋወር፣ ይዞ መገኘት የኮንትሮባንድ ወንጀሎች ሲሆኑ እነዚህም በሕግ የሚያስጠይቁ ጉዳዮች ናቸው ሲሉ ቡድን መሪው ስለወንጀሉ ምንነትና በሕግ የሚያስጠይቅ ጉዳይ መሆኑን በማብራሪያቸው ላይ አንስተዋል፡፡፡

በአጠቃላይ ኮንትሮባንድ ከእንቅስቃሴው አኳያ ወጪ ኮንትሮባንድ እና ገቢ ኮንትሮባንድ ተብሎ ይጠቀሳል የሚሉት አቶ ደምሰው

ገቢ ኮንትሮባንድ ማለት፡-

የእንቅስቃሴ መነሻው ከውጭ ሀገር ወይም ከጎረቤት ሀገር ሆኖ በተለያየ ስልትና መተላለፊያ መስመር አቆራርጠው ወደ ሀገራችን የሚገቡ ህገ-ወጥ ዕቃዎች ናቸው ይላሉ፡፡

ወጪ ኮንትሮባንድ ማለት፡-

የእንቅስቃሴ መነሻው ከሀገር ውስጥ ሆኖ በሀገር ውስጥ የተመረቱ እና በውጭ ምንዛሪ ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ የገቡ ምርቶች ተመልሰው በኮንትሮባንድ መልክ ወደ ጎረቤት አገሮች የሚወጡበት ህገ-ወጥ ዕቃ መሆኑንም አክለው ያነሳሉ፡፡

እኛም አስከትለን የተከለከለ ዕቃ ማለት ምን ማለት ነው ብለን ጥያቂያችን ያነሳን ሲሆን ፡-

የተከለከለ ዕቃ ማለት በኢትዮጵያ ሕግ ወይም ኢትዮጵያ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት ወደ ሀገር እንዳይገባ፣ ከሀገር እንዳይወጣ ወይም እንዳይተላለፍ የተከለከለ ማንኛውም ዕቃ ማለት ነው ሲሉ አጠር አድርገው ምላሻቸውን ሰጥተውናል፡፡

ወንጀሉ በሀገራችን የሕግ ማዕቀፍ አኳያ እንዴት ይታያል? የሚያስከትለው የሕግ ተጠያቂነት ምንድን ነው? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም፡-

ወንጀሉ ከሀገራችን የሕግ ማዕቀፍ አኳያ ዓለም ዓቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ከደረሰበት የእድገት ደረጃ ጋር የማጣጣም ህጋዊ ንግድንና የጉምሩክ ሕግ ማዕቀፍ በማስፈለጉ ሀገሪቱ የፈረመቻቸውን ዓለም ዓቀፋዊ፣ አህጉራዊና አካባቢያዊ የንግድ ስምምነት በወቅታዊ ሕግና የአሠራር ስርዓት እንዲኖር የሚያስገድዱ በመሆናቸው፣ ኮንትሮባንድና ሌሎች የንግድ ማጭበርበር ወንጀሎች በህጋዊ የንግድ እንቅስቃሴ፣ በሕዝብ ደኅንነት፣ በመንግሥት ገቢና በሌሎችም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገቶች ላይ የሚያስከትሉትን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን አሉታዊ ተፅኖ ለመከላከል የተጠናከረ የሕግ ማስከበር ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ የተለያዩ የአዋጅ ድንጋጌዎች ሀገራችን በስራ ላይ አውላ በህጉ መሠረት እያስተገበረች ትገኛለች ሲሉ አቶ ደምሰው ገልጸዋል፡፡

የሚያስከትለው የሕግ ተጠያቂነት በተመለከተ የኮንትሮባንድ ወንጀል ፈጽሞ የተገኘ ማንኛውም ሰው ከትንሹ ቅጣት ከአምስት ዓመት እስከ አስር ዓመት ጽኑ እስራት እና ከብር 50,000 በማያንስና 200,000 በማይበልጥ መቀጮ የሚያስቀጣ ሲሆን ከፍተኛው ከአስር ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ነው ሲሉ ያለውን የወንጀል ተጠያቂነት አብራርተዋል፡፡

እኛም አቶ ደምሰውን ከኛ ለነበራቸው ቆይታ እንዲሁም ለሰጡን ማብራሪያ እያመሰገንን ቀጣይ በሌላ ጥንቅር እስክንገናኝ ቸር ጊዜ ተመኝን፡፡