በሰው መነገድ ወንጀል ምንነት

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

ሰላም ጤና ይስጥልን ውድ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ተከታታዮች አሁን አሁን በሰዎች የመነገድ ወንጀል በሀገራችን ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳትን እያደረሰ የሚገኝ ወንጀል ሲሆን፤ በተለይም በወጣቱ ወይም በአምራቹ ኃይል ላይ ሞትን እንዲሁም አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳትን እያስከተለ ይገኛል፡፡ ሰዎች የህይወትን ውጣ ውረድ ለማሸነፍ የተሻለ ስራ ፍለጋ በህገ-ወጥ ደላላዎች አማካኝነት የጎረቤት ሀገራትን ድንበር በህገ-ወጥ መንገድ በማቋረጥ ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚሄዱ መሆኑ ደግሞ ለዚሁ ጉዳት መጋለጫ ምክንያት ነው፡፡

ለመሆኑ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወይም በሰው መነገድ ወንጀል ሲባል ምን ማለት ነው? ከሀገራችን የሕግ ማዕቀፎች አኳያ ወንጀሎቹ በምን መልኩ ተደንግገዋል? በሚሉ ርዕሰ-ጉዳዮች ዙሪያ በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ዐቃቤ ሕግ ከሆኑት አቶ ዮሐንስ ሲሳይ ጋር ቆይታ አድርገን ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥተውናል እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

በሰዎች የመነገድ ወንጀል ምንነትን እና የአፈጻጸም ሁኔታን በተመለከተ ላቀርብንላቸው ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል

በሰው መነገድ ድርጊት በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም የወንጀል ድርጊት ሲሆን በሀገራችንም ይሁን በመላው አለም ስልቱን እና መልኩን በመቀያየር ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመር ላይ የሚገኝ አስከፊ ወንጀል ነው ሲሉ አቶ ዮሐንስ ማብራሪያቸውን ይጀምራሉ፤ ለችግሩ መስፋፋት በርካታ ምክንያቶችን ማንሳት የሚቻል ቢሆንም በዋናነት ግን ድህነትና ሥራ አጥነት፣ የአመለካከት ወይም የግንዛቤ ችግር፤ የተሻለ ሥራና ገቢ ፍለጋ፤ የቤተሰብና የጓደኛ ግፊት ተጠቃሾች ስለመሆናቸው በጉዳዩ ዙሪያ የተከናወኑ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመላክቱም ዐቃቤ ህጉ ይናገራሉ፡፡ ወንጀሉ በአብዛኛው አምራች ኃይል የሆኑ ወጣቶች፣ ሴቶችና እንዲሁም ሕፃናትን ሰለባ በማድረግ እስከ ሞት ለሚያደርስ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚዳርግ መሆኑ ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል ያሉት ዐቃቤ ህጉ አስከትለውም ወንጀሉ በሰው ልጆች መብቶችና ክብር ላይ የሚፈጸም እና የሁሉም ሀገራት ችግር መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እንዲሁም በየለቱ የሚፈጸም ውስብስብና አስቸጋሪ ገጽታ ያለው መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

አያይዘውም አቶ ዮሐንስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለወንጀሉ ትኩረት መሰጠት የጀመረው በ20ኛ ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ጀምሮ መሆኑን አንስተው ሁሉንም ዓይነት በሰው የመነገድ ድርጊቶች ያካተተ የሕግ ትረጉም የተሰጠው ግን እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በወጣው በሰዎች በተለይም በሴቶችና ሕፃናት መነገድን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የወንጀሉን ፈፃሚዎች ለመቅጣት በወጣው ፕሮቶኮል ነው፡፡ በዚህም መሠረት በፕሮቶኮሉ አንቀጽ 3(ሀ) ላይ በሰው የመነገድ ወንጀል ማለት “ለብዝበዛ ዓለማ ሲባል ሰዎችን በዛቻ ፣ ኃይል በመጠቀም፣ በማገት፣ በመጥለፍ፣ በማስፈራራት ወይም ሌላ የማስገደጃ ዘዴ በመጠቀም፣ በተንኮል፣ በማታለል ወይም የተስፋ ቃል በመስጠት፣ ሥልጣንንን አላግባብ በመጠቀም ፣የሰዎችን ለጥቃት ተጋላጭነት በመጠቀም ወይም ስለሌላው ሰው ኃላፊነት ያለበትን ሰው ፈቃድ ለማግኘት መደለያ ወይም ጥቅም በመስጠት ሰዎችን መመልመል ፣ማጓጓዝ፣ ማዘዋወር፣ ማስጠለል ወይም መቀበል ነው” የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል ሲሉ ስለጉዳዩ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጠውናል፡፡

በዚህም መሠረት በሰው የመነገድ ወንጀል ድርጊት ተፈጽሟል ለመባል ሦስት መሠረታዊ ነገሮች መሟላት እንዳለባቸው ዐቃቤ ህጉ ያነሱ ሲሆን እነዚህም በወንጀል ፈጻሚዎቹ የሚፈጻመው ግዙፋዊ ድርጊት ማለትም መመልመል ፣ማጓጓዝ፣ ማዘዋወር፣ ማስጠለል ወይም መቀበል፣ድርጊቱን ለመፈጸም ጥቅም ላይ የዋለ ዘዴ ይህ ሲባል ዛቻ፣ ኃይል መጠቀም፣ ማገት፣ መጥለፍ ማስፈራራት ወይም ሌላ የማስገደጃ ዘዴ መጠቀም፣ ተንኮል፣ ማታለል ወይም የተስፋ ቃል መስጠት፣ ሥልጣንንን አላግባብ መጠቀም ፣ሰዎችን ለጥቃት ተጋላጭነት መጠቀም ወይም ስለሌላው ሰው ኃላፊነት ያለበትን ሰው ፈቃድ ለማግኘት መደለያ ወይም ጥቅም መስጠት እና በዝበዛ ናቸው ሲሉ ያነሳሉ፡፡ ነገር ግን ይላሉ አቶ ዮሐንስ የወንጀል ድርጊቱ በህጻናት ላይ በሚፈጸም ጊዜ ህጻናት ከሚገኙበት ልዩ የተጋላጭነት ሁኔታ ነገሮችን ከማመዛዘን እና የውጭ ጫናን ከመቋቋም አንጻር ያለባቸውን ውስንነት ግምት ውስጥ በማስገባት ግዙፋዊ ድርጊቱ እና ድርጊቱን የተፈጸመው ለብዝበዛ ዓላማ መሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ አጥፊው ድርጊቱን ለመፈጸም የተጠቀመው ልዩ ዘዴ ባይኖርም ወንጀሉን ግን እንደሚያሟላ ገልጸዋል፡፡

ከወንጀሉ ማቋቋሚያ ፍሬ ነገሮች መካከል አንዱ ዓላማ ነው ብለውናል፡፡ በሰው የመነገድ ወንጀል መሠረታዊ መገለጫው እና ይህው ዓላማስ ምንድን ነው ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ፡-

በሰው የመነገድ ወንጀል መሠረታዊ መገለጫው እና ዓላማው ተጎጂዎችን መበዝበዝ ሲሆን ለአብነት ያህል ሴቶችን ለዝሙት አዳሪነት ማቅረብ፣ በሴቶች የዝሙት አዳሪነት መጠቀም ፣ ሰውን ለግዳጅ ስራ ወይም አገልግሎት ማሠማራት፣ በባርነት ወይም ባርነት መሰል ተግባር መያዝ፣ አገልጋይ ማድረግ ወይም በዕዳ መያዣነት መያዝ ወይም ማቅረብ፣ የሰውን ልጅ አካል ማውጣትና መወስድ፣ ሰውን ለልመና ወይም ለወንጀል ተግባር ማሰማራት፣ ሰውን ለግዳጅ ጋብቻ ወይም የማህጸን ኪራይ ማሰማራት ከብዘብዛ ዓይነቶች ውስጥ ተጠቃሾች መሆናቸውን የገለጹት ዐቃቡ ህጉ ብዝበዛው አንዴ ብቻ ተፈጽሞ የሚያቆም ሳይሆን ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚፈጸም ነው ብለዋል፡፡

ከተል አድርገውም ለዚህም ዓላማ ተጎጂዎችን በቁጥጥር ሥር ማድረጊያ መነገዶችም መካከል

  • የተጎጂውን ፓስፖርት መያዝ (መቀማት)
  • ከሥር ቦታ ወይም ከመኖሪያ ቤት እንዳይወጡ መከልከል
  • ቤተሰብ ላይ ጉዳት አደርሳለሁ ብሎ ማስፈራራት ወይም ቤተሰብን ማስፈራራት
  • ደመወዝን መያዝ (መከልከል)
  • ህጋዊ የጉዞ እና የመኖሪያ ፈቃድ ሰነድ የሌላቸውን ተጎጂዎችን ለፖሊስ ወይም ለባለስልጣናት አሳውቅብሀለው/አሳውቅብሻለሁ ማለት
  • ሌላ ሥራ እንዳታገኝ/ እንዳያገኝ ማድረግ…ወዘተ ተጠቃሾ ናቸው ሲሉ ያነሳሉ፡፡

ከሀገራችን የሕግ ማዕቀፍ እና ከሚያስከትለው የቅጣት ውሳኔ አኳያ ላነሳንላቸው ጥያቄ ተከታዩን ማብራሪያ ሰጠውናል፡-

ሀገራችንም ከላይ የተገለጸውን ስምምነት ፈራሚ እንደመሆኗ ስምምነቱን በአዋጅ ቁጥር 737/2004 በማጽደቅ ከዚህ በፊት አዋጅ ቁጥር 909/2007 በማውጣት ስትተገበር የቆየች ሲሆን አዋጁ በነበሩበት አንዳንድ ክፍቶች ምክንያት በ2012 ዓ.ም በአዲስ አዋጅ በአዋጅ ቁጥር 1178/2012 እንዲተካ መደረጉን ማብራሪያቸው ላይ አንስተዋል፡፡

በአዋጁ ቁጥር 1178/2012 መሠረትም ማንኛውም በሰው የመነገድ ወንጀል ፈጽሞ የተገኘ ሰው ከሰባት ዓመት እስከ አስራ ሁለት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከአርባ ሺህ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚቀጣ በአንቀጽ 3/2 ( በማረሚያ ቁጥር 11/2013 እንደተስተካከለው) ተደግንግጓል ያሉት አቶ ዮሐንስ ወንጀሉ በህጻናት፣ በአዕምሮ ህመምተኞች ወይም በአካል ጉዳተኞች ላይ ከተፈጸመ፣ አደንዛዥ መድሀኒት፣ የጦር መሳርያ በመጠቀም ከተፈጸመ ወይም ኃላፊነቱን መከታ በማድረግ በባለሥልጣን ወይም በመንግሥት ሠራተኛ ከተፈጸመ እንዲሁም ፈቃዱን ሽፋን በማድረግ በውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት ፈቃድ ባለው ሰው የተፈጸመ ከሆነ ከ10 እስከ 20 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከ30, 000 እሰከ 100, 000 ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ የሚያስቀጣ ይሆናል ብለዋል፡፡በተጨማሪም ወንጀሉ የተደራጀ የወንጀል ቡድን አባል በመሆን ከተፈጸመ ወይም በተጎጂው ላይ የማይድን በሽታ ካስከተለ ወይም የተጎጂውን ደኅንነት አደጋ ላይ የጣለ ከሆነ በተጎጂው ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ያስከተለ ከሆነ ወይም ተጎጂው ለኢሰብዓዊ አያያዝ የተዳረገ ከሆነ ቅጣቱ ከ15 እስከ 25 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከ50,000 እስከ 150,000 ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ የሚያስቀጣ መሆኑን አቶ ዮሐንስ አንስተዋል፡፡ ነገር ግን ይላሉ አቶ ዮሐንስ ወንጀሉ በተጎጂው ላይ ሞትን አስከትሎ ከሆነ ደግሞ ቅጣቱ እንደ ወንጀሉ አፈጻጸም ሁኔታ እስከ እድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም የሞት ቅጣት የሚያስቀጣ ይሆናል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ማንኛውም በሰው የመነገድ ወንጀልን የመደግፍ፣ በሰው የመነገድ ወንጀልን መፈጹሙን ወይም እየተፈጸመ መሆኑን ወይም ሊፈጸም መሆኑን እያወቀ ለሚመለከተው ሕግ አስከባሪ አካል ወዲያውኑ አለማሳወቅ፣ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት ያለውን ንብረትን መሰወር፣ ማስረጃን በማጥፋት እና ተጠርጣሪን እንዳይከሰስ በመርዳት ፍትሕን ማስተጓጎል በአዋጁ መሠረት በወንጀል የሚያስጠይቁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

አዋጅ ቁጥር 1178/2012 ከዓለም አቀፉ የሕግ ማዕቀፍ ልዩ የሚያደረግ በአንቀጽ 3(1) እንተመለከተው የብዝበዛ ተግባር መፈጸሙ እስከተረጋገጠ ድረስ ሌሎች በሰው የመነገድ ወንጀልን የሚያቋቁሙ ፍሬ ነገሮች ማለትም ድርጊትና ዘዴ ባይኖሩም አጥፊውን በሰው የመነገድ ወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ የሚቻል መሆኑ ነው ሲሉም አዋጅ ቁጥር 1178/2012 ከዓለም አቀፉ የሕግ ማዕቀፍ የሚለይበትን ሁኔታ የገለጹት ፡፡

በመጨረሻም ይላሉ አቶ ዮሐንስ ወንጀሉን በመከላከል፣ አጥፊዎችን ለሕግ በማቅረብ እና የተጎጂዎችን መብት መጠበቅና በመንከባከብ ረገድ በፌዴራልና በክልል ደረጃ ሰፊ ሥራዎች በመሠራት ላይ የሚገኙ ሲሆን የታሰበውን ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የህበረተሰቡ ተሳትፎ እና የባለርሻ አካላት ትብብርና ቅንጅታዊ ሥራ ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ያሉ ሲሆን በተጨማሪም ለወንጀሉ ተጋላጭ የሆኑ ወጣቶችም ማንኛውንም የውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት መንግሥት በዘረጋው ሥርዓት መሠረት ቢሰማሩ ተጋላጭ ሳይሆኑ ሰብዓዊ መብታቸው እና ከብራቸው ተጠብቆ ያሳቡትን ማሳካት ይችላሉ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ ከእኛ ጋር ለነበራቸው ቆይታ እያመሰገንን በቀጣይ በህገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር የማሻገር ወንጀል እና ፈቃድ ሳይኖር ሰዎችን ለስራ ወደ ውጭ መላክ ወንጀሎች ምንነትን በተመለከተ ጥንቅር ይዘን እንቀርባለን፡፡ ሰላም!