ፍርድ ቤትን መድፈር

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

ፍርድ ቤቶች ፍትሕ የሚሰጥባቸው የፍርድ አደባባዮች ናቸው፡፡ ማንኛው የተበደለ ሰው ጉዳዩ በፍርድ ቤት የሚታይ ከሆነ ፍርድ አቅርቦ ፍትሕ ሊያገኝ ይችላል፡፡ ይህ በመሆኑ ፍርድ ቤቶች ሊከበሩ ይገባቸዋል፡፡ ፍርድ ቤትን መድፈር በሕግ የተካተተበት ዓላማ፤ የፍርድ ቤቱን ክብር ለመጠበቅ፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ሕልውና ለመጠበቅ፤ እንዲሁም ኅብረተሰቡ በዳኝነት አካሉ ላይ ያለውን መተማመን ለመጠበቅ ታስቦ ነው፡፡ ለፍርድ ቤት ህልውና መሠረት በሕዝብ መታመን ሲሆን ሥራውን በአግባቡ እንዲያከናውን ሕዝቡ እገዛ ያደርግለታል፡፡ በዚህ መነሻነት ፍርድ ቤቱ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን መተማመን የሚቀንስ ተግባር በሙሉ በሕግ ሊቀጣ ይገባል፡፡ ፍርድ ቤትን የመድፈር ድርጊቶች በዚህ ሥር የሚወድቁ ናቸው፡፡

ስለዚህ ፍርድ ቤትን መድፈር ዳኛውን በግለሰብ ማንነቱ ለመጠበቅ ታስቦ ሳይሆን የዳኝነት ተቋሙን ክብር ለመስጠት ታስቦ ነው፡፡ የቅጣቱ ዓላማም ተመሳሳይ ነው፡፡ የፍርድ ቤቱን ክብር ያዋረደው ግለሰብ እንዲቀጣ፣ ሌሎች ከተቀጣው ሰው ድርጊት ተምረው ለፍርድ ቤቶች ክብር እንዲሰጡ ማድረግና የፍርድ ቤቱን የሕዝብ ታማኝነት ማስቀጠል ነው፡፡ ይህም ጹሁፍ የፍርድ ቤት መድፈር ምንነት እና ፍርድ ቤትን መድፈር የሚያስከትለው የሕግ ተጠያቂነት በአጭሩ ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡

የፍርድ ቤት መድፈር ምንነት

ፍርድ ቤት መድፈር በሕገ ወጥነት ወይም ባለመታዘዝ የፍርድ ቤትን ክብር፣ ሞገስ ወይም ሥልጣን የመተላለፍ፣ የመጣስ፣ ያለማክበር ድርጊትን የሚያሳይ ነው፡፡ ፍርድ ቤት መድፈር የፍርድ ቤትን ሥልጣንና ክብር ዝቅ ለማድረግ ወይም የፍትሕ አስተዳደሩን ለማደናቀፍ፣ ለማወክ ወይም ክብሩን ለማዋረድ ታስቦ የሚፈጸም ድርጊት ነው፡፡ ፍርድ ቤትን መድፈር እነዚህን ድርጊቶች የሚያካትት ሲሆን በችሎት ሂደት ውስጥ በዳኛው የሚተላለፉ ትዕዛዞችን አለማክበር ወይም በመተላለፍ ለፍርድ ቤት አለመታዘዝን፤ፍርድ ቤት ማኅበረሰብ ፍትሕ የሚያገኝበት ስፍራ በመሆኑ ሊሰጠው የሚገባውን አክብሮት ለተቋሙና ለዳኛው ባለመስጠት ለችሎት ክብር መንፈግን፤ የዳኝነት ሂደቱ ሊካሄድ በማይችልበት ሁኔታ እንዲቋረጥ ማድረግ ወይም ለማቋረጥ መሞከር አልያም ደግሞ ዳኛው በነጻነት ተግባሩን እንዳያከናውን ጣልቃ በመግባት ፍርድ ቤትን ማወክን ይጨምራል፡፡ ፍርድ ቤትን መድፈር በሁለት ሁኔታዎች የሚፈጸም ሲሆን ይህም፡-

ፍትሐ ብሔራዊ ችሎት መድፈር (Civil contempt)

ይህ አይነቱ ፍትሐብሔራዊ ችሎት መድፈር በብዛት የሚፈጸመው በፍትሐብሄር ክርክር ጊዜ ሲሆን በፍርድ ቤቱ የተሰጠ ትእዛዝን ባለማክበር የሚመጣ ፍትሐብሔራዊ ይዘት ያለው ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ድርጊት ፍርድ ቤቱ የመጥሪያ፣ የእግድ፣ የምስክርነት ወዘተ. ትእዛዝ እንዲያከብር የላከለት ሰው ወይም በፍርድ ቤት ቀርቦ ሊፈጽመው የሚገባውን ፍትሐ ብሔራዊ ግዴታን ያልተወጣ ሰው የፍርድ ቤትን ትዛዝ ባለማክበሩ ፍርድ ቤትን እንደመድፈር የሚቋጠር ሲሆን ለዚህም ድርጊት የሚጠየቅ ይሆናል፡፡ በእንዲህ ዓይነት መድፈር የሚጠየቅ ሰው በአብዛኛው በተከራካሪ ወገን ጠያቂነት በፍርድ ቤት የሚታይ ሲሆን ዋና ዓላማውም ግለሰቡን መቅጣት ሳይሆን የፍርድ ቤቱን ትእዛዝ እንዲፈጽም ማስቻል ነው፡፡

ፍርድ ቤትን የመድፈር የወንጀል ተግባር (Criminal Contempt)

ይህ የፍርድ ቤቱ ክብርና ሥልጣን በግለሰቡ ድርጊት ማለትም ፍርድ ቤቱን ወይም የዳኝነት ሥራ በማከናወን ላይ ያለውን ዳኛ በማናቸውም መንገድ በመስደብ፣በማወከ፣ በችሎቱ ላይ በማፌዝ፣ በመዛት፣ የፍርድ ቤቱን ሥራ በማናቸውም ሌላ መንገድ በማወክ እና በሌሎች ድርጊቶች በሚጥስበት ጊዜ የፍርድ ቤቱን ክብር ለማስጠበቅ በፍርድ ቤቱ የሚፈጸም ሥርዓት ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ ፍርድ ቤትን የመድፈር ወንጀልን መቅጣት ለፍርድ ቤቱ ክብር ለመጠበቅ ግለሰቡን ለመቅጣት ዓላማ ያደረገ ነው፡፡

ሌላው የፍርድ ቤትን መድፈር ከአፈጻጸም አንፃርም ፍርድ ቤትን መድፈር ቀጥታ (direct) ወይም ቀጥታ ያልሆነ(indirect) ሊሆን ይችላል፡፡ ቀጥታ የሚባለው ፍርድ ቤቱ ወይም ዳኛው ችሎት እያስቻለ፣ ዳኛው ባለበትና እየሰማው የሚፈጸም ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ወንጀል በአብዛኛው ለተከሳሹ መጥሪያ ሳይደርሰው ወዲያውኑ የሚፈጸም ሲሆን ዳኛው ከሳሽ፣ ምስክር እና ዳኛ በመሆን ጥፋተኝነቱንና ቅጣቱን ይወስናል፡፡ ቀጥተኛ ያልሆነው ግን የመድፈር ድርጊቱ የሚፈጸመው ዳኛው በማይመለከተውና በማይሰማው ሁኔታ ነው፡፡ ለምሳሌ በፍርድ ቤት የተከናወኑትን የችሎት ሒደቶች ተገቢ ባልሆነ መንገድ የዘገበ፣ የተቸ ወይም ተገቢ ያልሆነ መደምደሚያ በጋዜጣ ወይም በሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ዘዴዎች ለሕዝብ ያቀረበ ጋዜጠኛ ደግሞ ችሎትን በመድፈር ወንጀል ከተጠየቀ ድርጊቱ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የተፈጸመ ስለመሆኑ መረዳት ይቻላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ዳኛው እያየው ወይም እየሰማው የተፈጸመ ባለመሆኑ ተከሳሹ መጥሪያ ደርሶት ሊቀጣ ይችላል፡፡

ፍርድ ቤትን መድፈር የሚያስከትለው የሕግ ተጠያቂነት

ፍርድ ቤት መድፈርን የተመለከተው የኢትዮጵያ ሕግ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ፤ በወንጀል ሕጉ እና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1234/13 ላይ ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡

በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ

የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ዘጠነኛ መጽሐፍ ከአንቀጽ 480-482 ፍርድ ቤትን ለማስከበር ፍርድ ቤቶች የተሰጣቸውን ሥልጣን በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት የማንኛውም ፍርድ ቤት ችሎት ዳኛ ፍርድ ቤቱንና የዳኝነት ሥራ አካሄድ ሥነ ሥርዓትን ለማስከበር ማናቸውንም አስፈላጊ መስሎ የታየውን ዕርምጃ እንዲወስድ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ይህንን ለማስፈጸም ለፍርድ ቤቱ ችሎት ክብር ወይም ለዳኝነቱ ሥነ ሥርዓት መልካም አመራር ተቃራኒ የሆነ ጠባይ የሚያሳየውን ማንኛውንም ተከራካሪ ወገን ወይም ጠበቃ ወይም በችሎት ውስጥ የሚገኘውን ማንኛውንም ሰው ተቃራኒ ተግባር በሚሠራበት ጊዜ በያዘው መዝገብ ላይ የገንዘብ መቀጮ ሊወስንበት ይችላል፡፡

በወንጀል ሕግ

ፍርድ ቤትን መድፈር በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ የተካተተ በወንጀል የሚያስጠይቅ ጥፋት ነው። በወንጀል ሕግ አንቀጽ 449 መሠረት ችሎት መድፈርን፡-

  1. ማንም ሰው በፍርድ ቤት ምርመራ በሚደረግበት ወይም የፍርድ ሥራ በሚከናወንበት ጊዜ ፍርድ ቤቱን ወይም የዳኝነት ሥራ በማከናወን ላይ ያለን ዳኛ በማናቸውም መንገድ የሰደበ፣ያወከ ወይም በእነዚሁ ላይ ያፌዘ ወይም የዛተ እንደሆነ ወይም የፍርድ ቤቱን ሥራ በማናቸውም ሌላ መንገድ ያወከ እንደሆነ ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እሥራት ወይም ከሦስት ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ የሚቀጣ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሳያደርግ ወድያውኑ በጥፋተኛው ላይ ቅጣት ሊወስን ይችላል፡፡
  2. ወንጀሉ የተፈፀመው ከችሎት ውጭ ሆኖ ዳኛው ሥራውን እያከናወነ ባለበት ጊዜ ከሆነ ቅጣቱ ከስድስት ወር የማይበልጥ ቀላል እሥራት ወይም ከአንድ ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮይሆናል።
  3. ወንጀሉ የተፈፀመው በችሎት ወይም በማናቸውም ቦታ የዳኝነት ሥርዓት በሚካሄድበት ጊዜ ሆኖ በኃይል ወይም በማስገደድ እንደሆነ አግባብ ያለው ድንጋጌ ማለትም በወንጀል ህጉ አንቀጽ 441 መሠረት የኃይልና የማስገደድ ድርጊት ወንጀል በተደራቢነት ተፈፃሚ ይሆናል በማለት ይደነግጋል።

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1234/13

አዋጁ የፍርድ ቤት ውሣኔዎችንና ትዕዛዞችን ስለ መፈጸም እና ይህንኑ ትእዛዝ አለመፈጸም የሚያስከትለውን የወንጀል ቅጣት ያስቀመጠ ሲሆን ይህም በአዋጁ አንቀጸ 51 ላይ የፍርድ ቤት ውሣኔዎችንና ትዕዛዞችን በተመለከተ፤በማንኛውም የፌዴራል ፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ እና ትእዛዝ በሕግ እስካልተለወጠ ድረስ የፀና ሆኖ ተፈፃሚ መሆን እንደለበት፤የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚሰጧቸዉን ዉሳኔዎች ወይም ትዕዛዞች በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ዉስጥ ተፈጸጻሚ እንደሚሆኑ፤በማንኛዉም ክልል ዉስጥ የሚገኝ የመንግሥት አካል፣ ተቋም ወይም መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ወይም ማንኛዉም ሰው ውሳኔዎቹን ወይም ትዕዛዞቹን የመፈጸም እና የማስፈጸም ግዴታ እንዳለበት እና ማንኛዉም ሰዉ የፍርድ ቤት ውሣኔዎችንና ትዕዛዞችን የማይወጣ ከሆነ የወንጀል ተጠያቂነት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ አዋጁ በአንቀጽ 52 ስር የወንጀል ተጠያቂነት ያስቀመጠ ሲሆን ይህም፤-

  1. የፍርድ ቤት ወይም የዳኞችን በነጻነት መሥራት የሚጋፋ ወይም በዳኞች ላይ ተጽእኖ የሚያደርግ ወይም ለማድረግ የሞከረ ማንኛውም ሰዉ በሌላ ሕግ ከፍ ያለ ቅጣት ከሌለ በቀር ከሦስት ወር እሥራት ባላነሰ ከሁለት ዓመት ባልበለጠ ጽኑ እስራት እንደሚቀጠ እንዲሁም፤
  2. የፍርድ ቤትን ትእዛዝ ወይም ዉሳኔ የማይፈጽም ወይም ለመፈፀም መሰናክል የሚፈጥር ወይም ሲጠየቅ ለመፈፀም ተባባሪ የማይሆን ማንኛዉም ሰዉ በሌላ ሕግ ከፍ ያለ ቅጣት ከሌለ በቀር ከሁለት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከአምስት ሺህ ብር በማይበልጥ ገንዘብ እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡

ፍርድ ቤት ሰዎች ሕግን መከታ አድርገው መብታቸውን የሚያስከብሩበት እንደመሆኑ የፍርድ ቤቱን ክብር መጠበቅ የፍትሕ ሥርዓቱን ሕልውና ለመጠበቅ ፤እንዲሁም ኅብረተሰቡ በዳኝነት አካሉ ላይ ያለውን መተማመን ለመጠበቅ ፍርድ ቤትን ማክበር ወሳኝ ነው፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና የተዘጋጀ