በኢትዮጵያ ህግ የይቅርታ አሰጣጥ ስርዓት

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

በወንጀል ሕግ ውስጥ ይቅርታ ማለት የቅጣት ፍርድ በሙሉ ወይም በከፊል ቀሪ እንዲሆን ወይም የቅጣት ፍርዱ አፈፃፀምና አይነት ቀለል ተደርጎ እንዲፈፀም ማድረግ ማለት ነው፡፡ ይቅርታ መብት ሳይሆን እድል ሲሆን በሀገራችን ይቅርታ የሚገዛው በይቅርታ አሰጣጥና አፈፃፀም ስነሥርዓት አዋጅ ቁጥር 840/2006 ነው፡፡

የይቅርታ ዓላማ የሕዝብ፣ የመንግሥትና የታራሚዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል መንግሥት የወንጀል ጥፋተኞች በጥፋታቸው የተፀፀቱና የታረሙ መሆኑን በማረጋገጥ ወደ ህብረተሰቡ ተቀላቅለው አምራች እና ሕግ አክባሪ ዜጋ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ በአጠቃላይም የወንጀል ሕግ ዓላማ የሆት የጠቅላላውን ሰላም፣ ደኅንነት፣ ሥርዓት፣ መብትና ጥቅም ያስጠብቃል፡፡

ይህ የይቅርታ አዋጅ የተፈፃሚነት ወሰኑ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች እና በወታደራዊ ፍርድ ቤቶች በተሰጡ የመጨረሻ የወንጀል ቅጣቶች ላይ እንዲሁም በማናቸውም የፌዴራል ወይም የክልል ፍርድ ቤት የሞት ቅጣት ውሳኔ ላይ ነው፡፡

ይህም ማለት የክልል ፍርድ ቤቶች በህገመንግስታችን በውክልና የተሰጣቸው የፌዴራል ፍርድ ቤት ሥልጣን ስር በሚወድቁ ጉዳዮችን ላይ የሚሰጡዋቸውን የመጨረሻ ውሳኔዎች ይጨምራል፡፡ የይቅርታ አይነቶችን ስንመለከት ይቅርታ ለተጣለው ቅጣት በሙሉ ወይም ከፊል ሊሰጥ የሚችል ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በቅድመ ሁኔታ የተመሰረተ ወይም ያለቅድመ ሁኔታ የሚሰጥ ይቅርታ ናቸው፡፡ በቅድመ ሁኔታ የሚሰጥ ይቅርታ ማለት ቅጣቱ ቀሪ ተደርጎ የሚቆየው ተቀጪው ተወስነው የተገለፁለትን ቅድመ ሁኔታዎች (በአብዛኛው የመልካም ጠባይ አመራር) እንዲያከብር ሲጠበቅበት ነው፡፡

ይቅርታ ለማግኘት በቅድሚያ የተጣለበት የፍርድ ቅጣት የመጨረሻ መሆን ያለበት መሆኑ ሲሆን ይህም ማለት በይግባኝ እየታየ ከሆነ ይህው እልባት ማግኘቱ ወይ ይግባኝ ያልተባለ ወይም የማይባል ከሆነ የይግባኝ ጊዜው ያለፈ መሆኑ ናቸው፡፡ አንድ የይቅርታ ጥያቄ የቅጣት ውሳኔው የመጨረሻ እንደሆ መቅረብ የሚችል ሲሆን ጥያቄው ታይቶ በተለያየ ምክንያት ውድቅ ከተደረገ ደግሞ ከስድስት ወር በኋላ በድጋሚ ሊቀርብ ይችላል፡፡

ይቅርታው በከፊል ከተሰጠ ደግሞ ለቀሪው ቅጣት ከአንድ ዓመት በኋላ በድጋሚ ጥያቄ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ይህ ጊዜ ሳይጠበቅ የይቅርታ ጥያቄ እንዲታይ ካስፈለገ የይቅርታ ቦርዱ በ¾ኛ ድምፅ በማናቸውም ጊዜ እንዲታይ ሊፈቅድ ይችላል፡፡

በአዋጁ መሠረት ይቅርታ የሚሰጠው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፕሬዚዳንት ብቻ ነው፡፡ ለእርሳቸው ጥያቄዎችን አደራጅቶ እና ከአስተያየት ጋር ለውሳኔ የሚያቀርብላቸው በአዋጁ የተደራጀው የይቅርታ ቦርድ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የይቅርታ ቦርድ 11 አባላት ያሉት ሲሆን የፍትሕ ሚኒስትሩ ሰብሳቢ፣ የፍትሕ ሚኒስቴር ዴኤታ ምክትል ሰብሳቢ ሲሆኑ አባላቱ ደግሞ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዴኤታ፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ፣ የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ፣ የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ፣ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ዴኤታ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል እና አብዛኛውን ህብረተሰብ ክፍል ከሚወክሉ አደረጃጀቶች በፍትሕ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፕሬዚዳንት የሚሰየሙ ሁለት አባላት ናቸው፡፡ ይህ ቦርድ የይቅርታ ጥያቄዎችን መርምሮ የውሳኔ ሀሳብ ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፕሬዚዳንት የሚያቀርብ ነው፡፡

የቦርድ አባላት ከግማሽ በላይ ከተገኙ ምልአተ ጉባኤ የሚሟላ ሲሆን፣ ውሳኔ በተገኙ አባላት አብላጫ ድምፅ ያልፋል፣ ድምፅ እኩል በኩል በተከፈለ ጊዜ ሰብሳቢው ያለበት ውሳኔ ያልፋል፣ ቦርዱ የራሱን የስብሰባ ደንብ ስነሥርዓት የሚያወጣ ሲሆን፣ በወር አንድ ጊዜና እንደአስፈላጊነቱ ይሰበሰባል፣ በየስድስት ወሩ ሪፖርት ለክብርት ፕሬዚዳንት ያቀርባል፡፡

የይቅርታ ቦርዱ ደግሞ በፍትሕ ሚኒስቴር ውስጥ የተደራጀ የይቅርታ ቦርድ ጽ/ቤት አስተዳደራዊ ስራው የሚታገዝ ነው፡፡ ጽ/ቤቱ የይቅርታ ማመልከቻዎችን ይቀበላል፣ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ያሰባስባል፣ ለቦርድ ውሳኔ ሀሳብ ያቀርባል፣ የቦርድ መዛግብት ይይዛል፣ ውሳኔዎች ይይዛል፣ ይቅርታዎችን በመዝገብ ያሰፍራል፣ አግባብነት ባለው ሕግ መሠረት ለሕዝብ ክፍት ያደርጋል፣ ስታትስቲክስ ያዘጋጃል፣ ውሳኔዎችን ያሳውቃል፣ የይቅርታ ምስክር ወረቀት ይሰጣል፣ አፈፃፀሙን ይከታተላል፣ ይቅርታ ውሳኔ ዋጋ ማጣትና የቅጣት ፍርድ አፈፃፀም መቀጠል በሚመለከት የቦርድ ውሳኔ ለሚመለከታቸው አካላት ያስተላልፋል፡፡

የይቅርታ ጥያቄ በአንድ የፍርድ ተቀጪ በራሱ፣ በወኪሉ፣ በጠበቃው በኩል ሊያቀርብ ይችላል፡፡ በባለቤቱ ወይም በቅርብ ዘመዱ ደግሞ እርሱ የፈረመበትን ጥያቄ ሊያቀርቡለት ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል እንደ አስፈላጊነቱ የፍትሕ ሚኒስቴር ወይም ማረሚያ ቤቱ ለታራሚዎች የይቅርታ ጥያቄ ለቦርዱ ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ በስሙ የቀረበለት የይቅርታ ጥያቄ ለታራሚው በቅድሚያ መድረስ ያለበት ሲሆን፣ እርሱም በ15 ተከታታይ የስራ ቀን ውስጥ በጽሑፍ ካልተቃወመ እንደተስማማ ይቆጠራል፡፡

አለመስማማቱን ለመግለፅ ከአቅም በላይ ችግር ከገጠመው ይህ ችግር እንደተወገደ በ15 የስራ ቀን ውስጥ ተቃውሞ ካለው ማስታወቅ አለበት፡፡

የይቅርታ ጥያቄ የሚከተሉትን የያዘ መሆን አለበት፡-

  • የአመልካች ሙሉ ስም፣ የእናት ሙሉ ስም፣ እድሜ፣ ጾታ፣ ዜግነት፣ ብሔር፣ የበፊት ስራ፣ አድራሻ፣ ከመታሰሩ ቀድሞ ያለ አምስት ዓመት የመኖሪያ አድራሻ፣ የተከሰሰበት ወንጀል፣ ጥፋተኛ የሆነበት ወንጀል፣ የተወሰነበት ቅጣት፣ የፈረደው ፍርድ ቤት፣ የፍርድ መዝገብ ቁጥሩ፣ የፍርዱ አፈፃፀም ደረጃ፣
  • ቀድሞ ተፈርዶበት ከሆነ የወንጀሉ አይነት፣ የተወሰነው ቅጣት፣ የፍርዱ አፈፃፀም ደረጃ፣ የፈረደው ፍርድ ቤት፣
  • ያለበት ማረሚያ ቤት ስም፣ የይቅርታ ጥያቄው ምክንያት፣ የስነምግባር አስተያየት ከማረሚያ ቤቱ፣ ከቅጣት ፍርዱ በፊት ስላለው ስነምግባር ሊመሰክሩ የሚችሉ የስጋ የጋብቻ ወይም የጥቅም ግንኙነት የሌላቸው 3 ምስክሮች ሙሉ ስምና አድራሻ፣
  • የወኪሉ ውክልና ወይም የዝምድና ማስረጃ፣
  • የማረሚያ ቤት አስተያየት ከምክንያት ጋር፣
  • መቀጮ ወይም ካሳ እንዲከፍል ተወስኖበት ከሆነ ስለመክፈሉ፣ ካልከፈለ ምክንያቱ፣
  • ቀደም ሲል ይቅርታ ተደርጎለት ከነበረ ወይም ጥያቄ ቀርቦ ውድቅ ተደርጎበት ከነበረ ውሳኔው የተሰጠበት ቀንና ዓመተ ምሕረት፣
  • ለጥያቄው ደጋፊ ማስረጃውን፣ ሰነዶች ካሉ፣ በእጁ የሌሉ ደጋፊ ሰነዶች ካሉ የሚገኙበት ቦታ የሚያለክት ሊሆን ይገባል፡፡

በዚህ መሠረት ጥያቄ የቀረበለት የይቅርታ ቦርድ ምስክር ሊሰማ ይችላል፣ የዓቃቤ ሕግ እና የፍርድ ቤት መዝገብ ሊመለከት ይችላል፡፡ የይቅርታ ጥያቄዎችን ከመንግሥትና ሕዝብ ጥቅም አንፃር ይመዝናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቦርዱ ባወጣው የይቅርታ አሠራር ስነስረአት መመሪያ መሠረት የሚከተሉት ጉዳዮች ከግምት እንደሚገቡ ይጠበቃል፡-

  • የአመልካቹ አደገኛነት፣
  • የወንጀሉ ክብደት፣
  • የማረሚያ ቤት ቆይታ ጊዜ፣
  • ከቀድሞ መስሪያ ቤት፣ ከመኖሪያ አካባቢ ማኅበረሰብ፣ ከቤተሰብ፣ ከሕክምና፣ ከሌሎች የተሰበሰቡ መረጃዎች፣
  • ለወደፊት በሰላም ለመኖር የሚያሳየውን ባህሪ፣
  • ጥፋተኝነቱን አምኖ በመቀበል የተፀፀተ መሆኑ፣
  • ከተጎጂ/ቤተሰብ ጋር ለመታረቅና ለመካስ ያደረገው ጥረት፣ የተወሰነበትን ካሳ ለመክፈል ያለውን አቅምና ፍላጎት፣ (ማኅበራዊ ፍርድ ቤት ድህነት ማስረጃ)
  • ተጎጂ/ቤተሰብ ለማግኘት ከተቻለ በጥያቄው ላይ ያላቸው አስተያየት፣
  • የማረሚያ ቤት ፀባይና ስነምግባር፣
  • የአመልካች የቤተሰብ፣ የጤንነት (ለመታረም አስቸጋሪ ያደረገ በቦርድ የተረጋገጠ)፣ እድሜ ሁኔታ፣
  • የሕዝብና መንግሥት ጥቅም ልዩ ሁኔታ፣
  • እድሜ ልክ ፍርደኛ ከሆነ 12 ዓመት እስር መጨረሱን፣ ሌሎች ፍርደኞች 1/3ኛ እስር መጨረሳቸውን፣ የግዴታ ስራ ካለበት ይህን መጨረሱን፣ ናቸው፡፡

ቦርዱ የሙስና፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሽብር፣ በወንጀል የተገኘ ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ፣ ሀሰተኛ ገንዘብ መሥራት ማዛወር፣ አደገኛ እፅ፣ ሴቶችና ሕፃናት መድፈር ወይም መጥለፍ፣ መሰረተ ልማት ላይ የሚፈፀም ወንጀል የፈፀሙ ፍርደኞችን ጉዳይ በጥንቃቄ በልዩ ሁኔታ ካልሆነ እደሌሎች ወንጀሎች አያይም፡፡

በዚህ መልክ ታይቶ የሚፈቀድ የይቅርታ ውሳኔ ውጤትን ስንመለከት ውሳኔው በግልፅ በከፊል መሆኑ ካልተመለከተ በቀር ይቅርታው የፍርድ ቅጣቶችን በሙሉ ያስቀራል፡፡ ሆኖም ይቅርታ ከወንጀል ፍርዱ የሚመነጩ የፍትሐብሔር ሀላፊነቶችን አያስቀርም፡፡ በተጨማሪም በፍትሐብሔር የጠፋውን እንደነበር ለመመለስ እና በተበዳይ ላይ ለደረሰ ጉዳት የሚከፈል ካሳና ኪሳራ አያስቀርም፡፡ ሆኖም በተለይ ካልተገለፀ በቀር ለመንግሥት ሊከፈል የሚገባ ወይም ያልተከፈለ ኪሳራ ቀሪ ይሆናል፡፡ ይቅርታው ከመሰጠቱ ቀድሞ የተፈፀሙ ቅጣቶች ደግሞ የፀኑ ይሆናሉ፡፡ ይቅርታ በተሰጠበት ወንጀል በአጥፊው ላይ የተያዘው የወንጀል ሪከርድ በወንጀለኞች መዝገብ ላይ ተመዝግቦ ይኖራል፡፡

ይቅርታ የተሰጠው በሀሰተኛ ወይም በተጭበረበረ ማስረጃ ተመስርቶ ከሆነ ይቅርታው ዋጋ አይኖረውም፡፡

በቅድመ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ የተሰጠ ይቅርታ ቅድመ ሁኔታው ከተጣሰ ዋጋ ያጣል፡፡ በዚህም መሠረት አጥፊው ቀሪ ቅጣቱን እንዲፈፅም ለማድረግ እንዲቻል ቦርዱ ይቅርታው እንዲሰረዝ ክብርት ፕሬዚዳንት ትእዛዝ እንዲሰጡ የውሳኔ ሀሳብ ያቀርባል፣ ይህ ተቀባይነት እንዳገኘ ትእዛዙ ለአጥፊው እንዲደርሰው ይደረግና ቅሬታ ካለው ትእዛዙ በደረሰው በአስራ አምስት ቀን ለቦርዱ ማቅረብ አለበት፡፡ ቅሬታው ተቀባይነት ካጣ የይቅርታ ምስክር ወረቀቱን እንዲመልስ ይደረጋል፣ በዚህም መሠረት የመያዣ ትእዛዝ እንዲሰጥ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጥያቄ ቀርቦ ቀሪ ቅጣቱን እንዲፈፅም ይደረጋል፡፡

በአጠቃላይ የይቅርታ ዓላማ ከላይ እንደተመለከትነው አጥፊዎች ከጥፋታቸው ታርመውና ተፀፅተው ሕግ አክባሪና መልካም ዜጋ ሆነው መኖር እዲችሉ ለማድረግ የሚሰጥ እድል ነው፡፡ የወንጀል ቅጣታቸው የመጨረሻ የሆነ፣ አንድ ሶስተኛ እስራታቸውን የጨረሱ፣ በማረሚያ ቤት በመልካም ባህሪ የቆዩ፣ ከጥፋታቸው የተፀፀቱና በቀጣይም ሕግን አክብረው ለመኖር የሚችሉ ሰዎች የሚያገኙት ሁለተኛ እድል ሲሆን ይቅርታ የህብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ብሎም ከወንጀል የተጠበቀ ለማድረግ ይረዳል፡፡ ይቅርታ የሚሰጣቸው ሰዎችም ይህን ተገንዘበው ህብረተሰቡን በመካስ በሕግ አክባሪነትና በመልካም ስነ ምግባር መመራት ይጠበቅባቸዋል፡፡