ከስሙ መረዳት እንደሚቻለው ዐቃቤያነ ሕግ ሀገራት የሚያወጧቸው ሕግጋት በአግባቡ ተፈፃሚ እንዲሆኑ ሕግን የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ዐቃቤያነ ሕግ ሙያዊ ብቃት ያላቸውና በጥብቅ ሥነ ምግባር የሚመሩ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡
በሀገራችንም በፌደራል ደረጃ በፍትሕ ሚኒስቴር እና በክልል ፍትሕ ቢሮዎች ሥር የሚያገለግሉ ዐቃቤያነ ሕግ ያሉ ሲሆን የሚተዳደሩበት የየራሳቸው ደንብ አላቸው፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ በፌደራል ዐቃቤያነ ሕግ መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር 443/2010 መሠረት የዐቃቤያነ ሕግ በሥራ ላይ ያለባቸውን ግዴታ የምንመለከት ይሆናል፡፡
የዐቃቢያነ ሕግ ምንነት
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 2 (መሠረት ዐቃቤ ሕግ ማለት በዐቃብያነ ሕግ መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር 443/2011 አንቀጽ 9 መሠረት በጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ተሹሞ በዚሁ ደንብ መሠረት የሚተዳደር የሕግ ባለሙያ ሲሆን በአዋጁ አንቀጽ 7(1) መሠረት የሚሾም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤያነ ሕግን ይጨምራል፡፡
በዐቃብያነ ሕግ መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር 443/2011 መሠረት የተሾመ ዐቃቤ ሕግ ሥራውን በሚያከናውንበት ጊዜ የሚከተሉት ግዴታዎች አሉበት፡፡
የሥራ ነጻነት እና ገለልተኛነት
በዐቃብያነ ሕግ መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር 443/2011 አንቀጽ 15 መሠረት ዐቃብያነ ሕግ ከማናቸውም ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆነው ተግባራቸውን ማከናወን አለባቸው፡፡ ሥራቸውን ሲያከናውኑ ከሕግ በስተቀር በሌላ ሁኔታ መመራት የለባቸውም፡፡ በተጨማሪም በደንብ አንቀጽ 72 መሠረት የፖለቲካ ድርጅት አባል መሆን ወይም በፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መሳተፍ ወይም በሥራቸው ላይ ፖለቲካዊ አመለካከታቸውን መግለፅ ወይም በማናቸውም መንገድ ማሳየት እንዲሁም በማናቸውም ሁኔታ በሥራቸው ላይ የግል እምነታቸውን ወይም ኃይማኖታቸውን የሚያንፀባርቅ ተግባር መፈፀም የለባቸውም፡፡
ዐቃቢያነ ሕግ ያለፍራቻ፣ ያለአድሎ ወይም ያለምንም ጥላቻ በተለይም ከግለሰባዊና ከወገናዊ ጥቅም ወይም ከሕዝባዊና ከመገናኛ ብዙሀን ግፉት ተፅዕኖ ሳያድርባቸው የሕዝብን ጥቅም ብቻ በማስቀደም ተግባራቸውን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል (አንቀጽ 73)፡፡ ስለሆነም ማንኛውም ሰው በሕግ ፊት አኩል መሆኑን እና እኩል ፍትሕ የማግኘት መብት እንዳለው በመገንዘብ ዐቃብያነ ሕግ ሥራቸውን በዚህ መርህ የመፈፀም ሙያዊ ግዴታ አለባቸው፡፡
በሥራ ላይ ስለመገኘት
የዐቃብያነ ሕግ የሥራ ቀንና ሰዓት ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሥራ ቀንና ሰዓት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ማንኛውም ዐቃቤ ሕግ በሥራ ሠዓት ተገኝቶ ሥራውን ማከናወን ይኖርበታል፡፡ በሥራው ዘግይቶ የሚመጣ ከሆነ፣ ቀደም ብሎ ከሥራው የሚወጣ ከሆነ ወይም በአንድ ምክንያት ከሥራው የሚቀር ከሆነ ወይም ለመሚለከተው የቅርብ ሀላፊ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ ሆኖም ዐቃቤ ሕግ ሊደረግለት የሚገባው ጥንቃቄና ድጋፍ ሁሉ ሳይጓደልበትና ሥራው በመደበኛ የሥራ ሰዓት ሊፈፀም የማይችል ሆኖ በተገኘ ጊዜ ሥራው በሚመለከተው የበላይ ሀላፊ ትእዛዝ ከመደበኛ የሥራ ሰዓት በላይ የሚሰራበት ሁኔታ እንደሚኖር ከደንቡ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜም የትርፍ ሰዓት ሥራ ክፍያ የሚፈቀድባቸው ሁኔታዎች፣ ስለክፍያው መጠን እና የማካካሻ እረፍት ስለሚሰጥበት ሁኔታ በተመለከተ ተቋሙ መመሪያ መሠረት የሚስተናገዱ ይሆናል፡፡
ታማኝነት፣ ታዛዥነት እና መልካም ፀባይ
ደንብ ቁጥር 443/11 አንቀጽ 69 መሠረት ዐቃቤያነ ሕግ በሥራ ነፃነታቸው የተጣለባቸውን እምነትና አደራ መጠበቅ እንዲሁም ሙሉ ጉልበታቸውን፣ ሀሳባቸውንና ችሎታቸውን በታማኝነት ለመንግሥትና ለሕዝብ አገልግሎት ጥቅም ማዋል ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ዐቃቤያነ ሕግ ህጋዊ ትእዛዞች ሲኖሩ በመቀበል ለሕግ ታዛዥነታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡
ዐቃቤያነ ሕግ በመሥሪያ ቤትም ሆነ ከመሥሪያ ቤት ውጭ በማናቸውም ጊዜ የሕዝብን አክብሮትና እምነት ለማግኘት የሚያስችል መልካም ጠባይና ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው ያስፈልጋል (አንቀጽ 70)፡፡ በማናቸውም ሁኔታ የሙያውን ክብር የማይመጥን ተግባር ከመፈፀም መታቀብም ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተጨማሪም በአንቀጽ 80 መሠረት ለመሥሪያ ቤቱ የሚያበረክቱትን አገልግሎት የሚያጓድል ወይም ለሥራና ኃላፊነታቸው ተቃራኒ የሆነ ወይም ከሙያ ሥነ-ምግባር ጋር የማይጣጣም ማናቸውንም የውጭ ሥራ መሥራት አይችሉም፡፡
ስለሆነም ከፈጠራ፣ ከኪነ ጥበብ፣ ከጥናትና ምርምር፣ ከሕግ ረቂቆች ዝግጅት፣ ከሳይንሳዊና ትምህርታዊ ስራዎች ውጪ ያሉ ከሥራ ሰዓት ውጭ የሚሰሩ ሥራዎችን ለመሥራት በሚኒስትሩ ፍቃድ ማግኘት አለበት፡፡
ምስጢር መጠበቅ
ማንኛውም ዐቃቤ ሕግ በሥራ አጋጣሚ ያገኘውን መረጃ ወይም ምስጥር መጠበቅ አለበት፡፡ የሚያውቀው መረጃ ተራ ወይም በሕዝብ ዘንድ የታወቀ ካልሆነ ወይም መደበኛ ሥራውን በሕጋዊ መንገድ ለመፈፀም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር በሥራው አጋጣሚ ወይም ምክንያት ወይም በሌላ አኳኋን ያገኘውን መረጃ መግለፅ የለበትም፡፡
በሥራና በግል ጉዳዮች ወይም ጥቅሞች መካከል የሚፈጠር ግጭትን ማስወገድ
ማንኛውም ዐቃቤ ሕግ የራሱ፣ የዘመዶቹ ወይም የወዳጆቹ የግል ጉዳይ ወይም ጥቅም ከሥራው ወይም በሥራው ምክንያት ከያዘው የሕዝብ ወይም የግለሰብ ጉዳይ ጋር የሚጋጭ ከሆነ የጥቅም ግጭት የሚፈጥር በመሆኑ ወዲያውኑ ለቅርብ ሀላፊው የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ ይህ በሆነበት ጊዜ ጉዳዩ በሌላ ዐቃቤ ሕግ እንዲታይ እንደሚደረግ በደንቡ አንቀጽ 77 ተመልክቷል፡፡
በተጨማሪም ዐቃቤያነ ሕግ በሥራ ምክንያት ከሚያጋጥማቸው ባለጉዳይ ገንዘብ ለመበደር መሞከር ወይም መበደር ፈፅሞ ተከለከለ ከመሆኑም በላይ ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ለሰጡት ወይም ወደፊት ለሚሰጡት አገልግሎት ከማንኛውም ሰው ማናቸውንም ዓይነት ዋጋ ያለውንም ሆነ የሌለውን ስጦታ መጠየቅ ወይም መቀበል እንደሌለባቸው በደንቡ አንቀጽ 75 እና 76 ተደንግጓል፡፡
በአጠቃላይ ዐቃብያነ ሕግ ሀገር የምታወጣቸውን ሕግጋት በማክበር እና በማስከበር ረገድ ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህን ሀላፊነታቸውን ለመወጣት እና በሕዝብ ዘንድ ቅቡልነት ለማግኘት በሕግ የተቀመጡ የሙያ ግዴታዎችን በአግባቡ መወጣት እና መልካም ሥነ ምግባር መላበስ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ተዘጋጀ