የጊዜ ቀጠሮ ምንነት እና የፖሊሰ፣ የዐቃቤ ሕግና የፍርድ ቤት ሚና

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

ሰላም ጤና ይስጥልን የፍትሕ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታዬቻችን እንደምን አላችሁ! ዛሬ የጊዜ ቀጠሮ ምንነት እና የፖሊሰ የዐቃቤ ሕግና የፍርድ ቤት ሚና በሚል አርዕስት አንድ አጠር ያለ ጽሑፍ ወደናንተ ልናደርስ ወደናል! በፅሁፋችን የጊዜ ቀጠሮ ምንነት፣የጊዜ ቀጠሮ ዓላማ፣የጊዜ ቀጠሮ ርዝማኔና መሰል ተያያዥ ጉዳዮች የሚዳሰሱ ሲሆን ፅሁፉን በፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ፣ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ የሆኑትን አቶ አበበ ጌታሁን አነጋግረን አዘጋጅተንላኋል፤አንብባችሁ ንቃተ ህጋችሁን ከፍ ታደርጉበትና ታተርፉበት ዘንድ ጋብዘናችኋል፡፡

ወንጀል በተለያዩ ምክንያቶች በቸልተኝነት ወይም ሆን ተብሎ ሊፈጸም ይችላል፡፡ አንድ ወንጀል ተፈጽሞ ሲገኝ ፖሊስ ወንጀሉ በተፈጸመበት ስፍራ በመድረስ ወንጀል ፈጻሚውን የመለየት ስራ ያከናውናል፡፡ የወንጀል ድርጊቱን ፈጽመሀል ተብሎ ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው በአርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት የኢ.ፌ.ድ.ሪ ሀገ-መንግሥት አንቀጽ 19 እና የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 59 ላይ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ አንድ ተጠርጣሪ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ ፍርድ ቤቱ በእስር እንዲቆይ ወይም በዋስትና እንዲለቀቅ ውሳኔ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ተጠርጣሪው በእስር እንዲቆይ ውሳኔ ሲሰጥ በሁለት ምክንያቶች ሲሆን እነዚህም አንደኛ የተጠረጠረበት ወንጀል ዋስትና የሚከለክል ሲሆንና ሁለተኛ ደግሞ ፖሊስ ምርመራውን ባለመጨረሱ ምክንያት ተጨማሪ የምርመራ ቀን እንዲሰጠው ሲጠይቅ ብቻ ነው፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍም ለፖሊስ የሚሰጠው ተጨማሪ ጊዜ ምንነትና የዐቃቤ ሕግና የፍርድ ቤት ሚና ምንድን ነው የሚሉትን ጉዳዮች ይዳሰሳሉ፡፡

የጊዜ ቀጠሮ ምንነት

የጊዜ ቀጠሮ ትርጉሙ በቀጥታ በየትኛውም ሕግ ላይ የተቀመጠ ባይሆንም በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 59 ላይ የተቀመጠውን በመመልከት ትርጉም መስጠት ይቻላል። ከላይ በተገለጸው አንቀጽ ላይ እንደተቀመጠዉ አንድ በወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው በዐቃቤ ሕግ በኩል የወንጀል ክስ ከመቅረቡ በፊት በወንጀል ምርመራ ወቅት ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት ቀርቦ መርማሪ ፖሊስ ምርመራውን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ጊዜ እዲሰጠውና ምርመራውን እስኪጨርስ ተጠርጣሪው ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ሲጠይቅ ፍርድ ቤቱም ተጠርጣሪው ምርመራው እሰኪያልቅ ድረስ ለተወሰነ ጊዜ ማረፊያ ቤት እንዲቆይ የሚደረግበት ስነ ሥርዓት የጊዜ ቀጠሮ ይባላል።

የጊዜ ቀጠሮ ዓላማ

ማንኛውም የተያዘ ሰው ፍርድ ቤት ቀርቦ በዋስትና የመፈታት መብት እንዳለው በኢ.ፌ.ድ.ሪ ህገ-መንግሥት የተረጋገጠ ቢሆንም በልዩ ሁኔታ ዋስትና የሚከለከልበት ሁኔታ አለ፡፡ የጊዜ ቀጠሮ ዋና ዓላማው ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ የሚያካሂደውን ምርመራ ባለማጠናቀቁ ተጨማሪ ጊዜ ተሰጥቶት ምርመራውን በተገቢ ሁኔታ ማጣራት እንዲችል ማድረግ ነው፡፡ በሌላ በኩል የጊዜ ቀጠሮ ዓላማ ማስረጃ እንዳይጠፋ ከማድረጉም በተጨማሪ ተጠርጣሪው በፈጸመው ወንጀል ምክንያት ለመበቀል የሚፈልጉ አካላት ካሉ እነዚህ አካላት ከሚያደርሱበት አደጋ ይጠበቃል፡፡

የጊዜ ቀጠሮ አሰጣጥና ርዝማኔ

በወንጀል የተጠረጠረ አንድ ሰው በአርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት የኢ.ፌ.ድ.ሪ ህገ-መንግሥት የደነገገ በመሆኑ ፖሊስ የያዘውን ተጠርጣሪ በተባለው የጊዜ ገደብ ውስጥ አቅራቢያ ባለው ፍ/ቤት ማቅረብ አለበት፡፡ ልብ ልንለውና ከግምት ውስጥ ማስገባት ያለብን ነገር ተጠርጣሪውን ፍ/ቤት ለማቅረብ የሚወስደው ጊዜ በአርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ አይካተትም፡፡ በፍትሐ ብሔር ስነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 29 እንደተቀመጠው ፖሊስ የያዘውን ተጠርጣሪ ፍርድ ቤት ካቀረበ በኋላ ፍርድ ቤቱም ተይዞ የቀረበውን ተጠርጣሪ በማረፊያ ቤት እንዲቆይ ወይም በዋስትና እንዲለቀቅ ውሳኔ መስጠት እንዳለበት በፍትሐ ብሔር ስነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 59 ላይ ተቀምጦ ይገኛል፡፡

ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ የወንጀል ምርመራውን ካላጠናቀቀ ፍርድ ቤቱን በተጠርጣሪው ላይ የወንጀል ምርመራውን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ይጠይቃል፤ ፍርድ ቤቱም የቀረበለትን የጊዜ ቀጠሮ የሚፈቅድ ከሆነ ይህን በመግለጽ በጽሁፍ ማሳወቅ አለበት፡፡ ፍ/ቤቱ ለሚሰጠው የጊዜ ቀጠሮ ከአስራ አራት ቀን መብለጥ እንደሌለበት በስነ- ሥርዓት ሀጉ አንቀጽ 59 ላይ ተደንግጓ ይገኛል፡፡

የጊዜ ቀጠሮ አስፈላጊነት እና የዐቃቤ ሕግና የፍርድ ቤት ሚና

የጊዜ ቀጠሮ ዋና ዓላማውና አስፈላጊነቱ በምርመራ ወቅት ፖሊስ ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ ሰፊ ጊዜ እንዲያገኝ ከማገዙም በላይ ማስረጃዎች እንዳይጠፉና እንዳይሰወሩ ያግዛል፡፡ በአብዛኛው በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው የሚመሰክሩባቸውን ሰዎች በጥቅምና በማታለል ማስረጃ እንዲጠፋ የሚያደርጉ በመሆኑና ምስክሮችንም በማስፈራራት እንዳይመሰክሩ የሚያደርጉ ስለሆነ የጊዜ ቀጠሮ እነዚህን ችግሮች ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

በአብዛኛው የጊዜ ቀጠሮ ሲጠይቅ የሚታየው መርማሪ ፖሊስ ሲሆን ነገር ግን ዐቃቤ ሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የምርመራ ዘርፉን የሚመራና የሚቆጣጠር ስለሆነ የጊዜ ቀጠሮ በሚጠየቅበት ወቅት ከፖሊስ ጋር በመነጋገር የተጠርጣሪን መብት በጠበቀ ሁኔታ የጊዜ ቀጠሮ እንዲጠየቅ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

ዉድ ተከታዮቻችን በዛሬዉ ፅሁፋችን ስለ ጊዜ ቀጠሮ ምንነትና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ግንዛቤያችሁን የሚያሳድግ መረጃ እንዳገኛችሁበት ያለንን እምነት እየገለፅን ማብራሪያ የሰጡንን ዐቃቤ ሕግ አቶ አበበ ጌታሁንን በእናንተ በአንባቢዮቻችን ስም እጅግ አድርገን እናመሰግናለን