መግቢያ
ሰዎች በተለያዩ መስኮች እውቀት ሊኖራቸው ይችላል። ይህን እውቀታቸውን እንደ ሞያ ወይም እንደመተዳደሪያ ሊጠቀሙበት የሚችሉ ሲሆን ከሞያቸው ውጪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸው እውቀት ደግሞ እንደ ጠቅላላ እውቀት ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ስለአንዳንድ ጉዳዮች ማወቅ በምርጫ ሊወሰን የሚችል ቢሆንም ሌሎቹን ማወቅ ግን ግድ የሚሆንባቸው ሁኔታዎች ይታያል። ከነዚህም ውስጥ በባለሞያ ደረጃ ባይሆንም ሕግን ማወቅ ግድ የሚሆንበትን ሁኔታ ከተለያዩ ህጎች መገንዘብ እንችላለን። በዚህ አጭር ጽሑፍ የሕግን ምንነት፣ ሕግን የማወቅ ጠቀሜታ እና ሕግን አለማወቅ በህጉ የሚታይበትን ሁኔታ በአጭሩ እንመለከታለን።
የሕግ ምንነት
ሕግ የሚለው ቃል በማህበረሰቡ ዘንድ በስፋት የሚታወቅ ቃል ሲሆን አስገዳጅ መሆኑን የሚገነዘብ ለመሆኑ ቀደም ባለው ጊዜ በየዕለት ኑሮ ፀብ ሲገጥመው እንኳን “በሕግ አምላክ” ብሎ ፀብ የማብረድ ልምድ የነበረው መሆኑ ማሳያ ነው፡፡ ሆኖም ማህበረሰቡ ሕግን የሚረዳው በተለምዶአዊው ሁኔታ እንጂ የዘርፉ ባለሞያዎች በሚረዱበት መልኩ አይደለም፡፡
በእርግጥ ሕግ ለሚለው ቃል ትርጓሜ መስጠት ቀላል ሥራ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የቃሉ ፅንሰ ሀሳብ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚለዋወጥ በመሆኑ እና የተለያዩ ምሁራን ቃሉን በተለያየ መንገድ የሚገልፁት በመሆኑ ነው፡፡ እንዲሁም የቃሉ ፍቺ ሊደረስባቸው በሚፈለጉት የተለያዩ ዓላማዎች ምክንያት ሊለያይ ይችላል። ለሕግ ቃላት ትርጉም በመስጠት የሚታወቀው ብላክስ ሎው የሕግ መዝገበ ቃላት በተሻሻለው ስድስተኛ እትሙ (Black’s Law Dictionary, 6th ed.,) ለሕግ ትርጉም ሲሰጥ law is “a body of rules of action or conduct prescribed by controlling authority, and having binding legal force, which must be obeyed and followed by citizens subject to sanctions or legal consequence is a law.” ወደ አማርኛ በግርድፉ ሲመለስ ሕግ ሥልጣን ባለው አካል የተደነገገው አስገዳጅ ኃይል ያለው እና ዜጎች አክብረው ሊተገብሩት የሚገባ፤ አለመከበሩ ደግሞ ተጠያቂነት የሚያስከትል የተግባር ወይም የምግባር ድንጋጌ ነው።
ሕግን የማወቅ ጠቀሜታ
ሕግ የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ፣ የግለሰብ መብቶችን ለማስጠበቅ፣ ማኅበራዊ ፍትሕን ለማስፈን (promote social justice) እና ሌሎች አገልግሎቶች ያሉት እንደመሆኑ ሕግን ማወቅ በዋናነት
- መብትን ለመጠቀም እና ግዴታ ለመወጣት
- ለሕግ ተገዢ ለመሆን
- የሌሎችን መብት ለማክበር
- እራስን ከሀላፈነት ወይም ከተጠያቂነት ለማዳን ጠቀሜታ አለው።
ሕግን አለማወቅ/ስህተት ከተጠያቂነት የማያድን መሆኑ
የወንጀልም ሆነ የፍትሐብሔር ህጎቹ በሕግ አውጪው አካል ወጥተው ከፀደቁበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንደሚውሉ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ዜጎች የህጎቹን መኖር ወይም መውጣት የማወቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህንም ሕግን አለማወቅ ወይም የሕግ ስህተት ከተጠያቂነት አያድንም የሚለው የሕግ መርህ በላቲን Ignorantia juris non excusat ወይም በእንግሊዘኛ “ignorance of the law has no excuse” ከሮማውያን ሕግ የተወሰደ ሲሆን ሕግን የማያውቅ ሰው ይዘቱን ባለማወቅ ብቻ ህጉን በመተላለፍ ከተጠያቂነት ሊያመልጥ እንደማይችል የሚገልፅ የሕግ መርህ ነው። ይህ ማለት አንድ ሰው ሕግ ከጣሰ ህጉን ስለመጣሱ ምንም እውቀት ባይኖረውም ተጠያቂ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በዚህም ሰዎች ህጉን አላውቀውም በማለት ድርጊታቸውን ሊከላከሉ አይችሉም፡፡ የዚህ መርህ ምክንያት ሰዎች የህጉን መኖር ቢያውቁም ህጉን አላወኩም በሚል ሰበብ ከተጠያቂነት ለማምለጥ እድል ሊያገኙ የማይገባ መሆኑ ነው፡፡
በኢትዮጵያም ሕግ አለማወቅ ወይም የሕግ ስህተት ከተጠያቂነት እንደማያድን መሆኑ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 81 ስር ሕግን አለማወቅ ወይም በሕግ ላይ መሳሳት መከላከያ ሊሆን እንደማይችል እና በፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 2035/1 እና 2 ስር አንድ ሰው በሕግ ላይ በትክክል የተገለፀውን ድንጋጌ፣ ልዩ ደንብና ሥርዓት የጣሰ እንደሆነ ጥፋተኛ እንደሆነ እና ሕግን አለማወቅ ይቅርታ ሊያስገኝ የማይችል መሆኑ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ መንግሥትም ማህበረሰቡ ሕግን አውቆ እንዲያከብር ህጎችን በተያዩ ዘዴዎች ማሳወቅ ያለበት ሲሆን በሀገራችን ዋነኛው መንገድ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እንዲወጣ በማድረግ ነው።
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ ሕግ የሀገርን እና የዜጎችን ሰላም ከማረጋገጥ አንፃር ጉል ሚና ያለው እንደመሆኑ እና ሕግን አለማወቅም ከተጠያቂነት የማያድን በመሆኑ ዜጎች በሕግ ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ