መግቢያ
ቴክኖሎጂ ለሰው ልጆች ይዞ የመጣው በጎ አስተዋጽኦ እንዳለ ሁሉ ችግሮችንም ይዞ መጥቷል። ከነዚህ ችግሮች መካከል የቴሌኮም ስነ ምህዳርን በመጠቀም የሚፈጸሙ የማጭበርበር ወንጀሎች ይጠቀሳሉ።
ኢትዮጵያም የዚህ ዓለም ዓቀፍ ችግር ተጠቂ ከሆኑ አገራት አንዷ ነች። የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል ግለሰቦችን፣ ኩባንያዎችንና የአገርን ኢኮኖሚ በእጅጉ እየጎዳ የሚገኝ ወንጀል ነው። ዓለም ከደረሰችበት የዘመነ ቴክኖሎጂ ጎን ለጎን ለዚህ እንቅፋት የሆኑ ተግዳሮቶችን ለመከላከል እና አጥፊዎችን ለመቅጣት ሕጋዊ ማዕቀፍ ማበጀት ግድ የሚልበት ዘመን ላይ ደርሰናል። በመሆኑም ይህ ጽሑፍ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል በኢትዮጵያ ያለውን ገጽታ፣ የኢትዮጵያ ሕግ ስለነዚህ ወንጀሎች የሚያስተላልፋቸውን የቅጣት ድንጋጌዎች ያብራራል።
የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል ምንነት
የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል ማለት ማንኛውም ግለሰብ፣ ቡድን ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል የቴሌኮሙኒኬሽን መሠረተ ልማቶችን (እንደ ስልክ፣ ኢንተርኔት፣ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ያሉትን) በመጠቀም ሌሎችን በማታለል፣ የሐሰት መረጃ በመስጠት ወይም ማንነትን በመደበቅ ህገ-ወጥ ጥቅም ለማግኘት የሚፈጽመው ድርጊት ነው። ይህ ወንጀል ቀላል ከሚመስሉ የሐሰት የጽሑፍ መልዕክቶች ጀምሮ እስከ ውስብስብ የኮልባክ (Call-back) ማጭበርበር ድረስ ሰፊ መገለጫዎች አሉት። ከላይ የተገለፀው ምንነት በቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 761/2004 ከተደነገጉ አንቀጾች ይዘት የምንረዳው ነጥብ ነው።
የዚህ ወንጀል ሰለባዎች ገንዘባቸውን ከማጣታቸውም በላይ ለከፍተኛ ማኅበራዊና ስነ-ልቦናዊ ቀውስ ይዳረጋሉ። በአገር ደረጃ ደግሞ መንግሥት ከዓለም ዓቀፍ የስልክ ጥሪዎች ሊያገኝ የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ እንዲያጣ በማድረግ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል። በተጨማሪም ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርንና ሌሎች ተያያዥ ወንጀሎችን በማመቻቸት ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ይፈጥራሉ።
የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 761/2004 (Telecom Fraud Offence Proclamation No. 761/2012)
ይህ አዋጅ የወጣው በየጊዜው አድማሱን በማስፋት እየተበራከተ የመጣውን የቴሌኮም ማጭበርበር ለመከላከልና በአገሪቱ ሰላም፣ ልማት፣ ኢኮኖሚ እና ደኅንነት ላይ የደቀነውን ከባድ አደጋ ለመቆጣጠር ታልሞ ነው። ስለሆነም በዚህ አዋጅ የተካተቱ የወንጀል ድርጊቶችንና የሚያስከትለዉን ቅጣት እናያለን።
ከቴሌኮም መሳሪያዎች ጋር የተያያዙ ወንጀሎች
በአዋጁ አንቀጽ 3(1) ስር ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር (በቀድሞ አጠራሩ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር) ፈቃድ ውጪ ማንኛዉንም ዓይነት የቴሌኮም መሳሪያ ማምረት፣ መገጣጠም፣ ከውጪ አገር ማስገባት ወይም መሸጥ ከ10 እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራትና ከብር 100 ሺ እስከ 150 ሺ በሚደርስ መቀጮ እንደሚያስቀጣ ተደንግጎ እናገኛለን። በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 ስር ከሚኒስቴሩ ፈቃድ ውጪ ማንኛውም አይነት የቴሌኮም መሳሪያ መጠቀም ወይም ይዞ መገኘት ከ1 እስከ 4 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከብር 10 ሺ እስከ ብር 40 ሺ በሚደርስ መቀጮ እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል፡፡
የቴሌኮም አገልግሎት ከመስጠት ጋር የተያያዙ ወንጀሎች
አግባብ ባላቸው ህጎች መሠረት የተሰጠ የፀና ፈቃድ ሳይኖር የቴሌኮም አገልግሎት በመስጠት ሥራ ላይ መሠማራት ከ7 እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ፈጻሚው ያለፈቃድ በሚሠራበት ጊዜ ሊያገኝ ይችላል ተብሎ የሚገመተውን ገቢ ሦስት እጥፍ የሚሆን መቀጮ ይቀጣል ሲል በአንቀጽ 4 ስር ተደንግጓል፡፡
የቴሌኮም አገልግሎትን ለህገ ወጥ ዓላማ ስለማዋል
በአንቀጽ 6 ስር እንደሰፈረው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ድርጅት የሚሰጠውን አገልግሎት ወይም የቴሌኮም መሰረተ ልማትን ለሕገ ወጥ ዓላማ ያዋለ ወይም እንዲውል ያስደረገ እንደሆነ በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ከ3 እስከ 8 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከብር 30ሺ እስከ ብር 80ሺ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡
የአገልግሎት ዋጋን ማጭበርበር
አዋጁ በአንቀጽ 7 ስር የቴሌኮም አገልግሎት ዋጋን ማጭበርበር ላይ ክልከላ የሚጥል ሲሆን ይኸውም ማንኛውም ሰው፡-
• ላገኘው የቴሌኮም አገልግሎት መክፈል የሚገባውን ትክክለኛ ዋጋ በተጭበረበረ መንገድ ሳይከፍል የቀረ እንደሆነ ወይም
• ለቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ድርጅቱ መክፈል የሚገባውን የአገልግሎት ዋጋ በተጭበረበረ መንገድ በሌላ ሰው እንዲፈፀምለት በማድረግ የቴሌኮም አገልግሎት ያገኘ እንደሆነ ከ5 እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ተጭበርብሯል ተብሎ የሚገመተውን የቴሌኮም አገልግሎት ዋጋ ሦስት እጥፍ የሆነ መቀጮ ይቀጣል፡፡
የኮልባክ አገልግሎት ክልክል ስለመሆኑ
በአዋጁ አንቀጽ 8 ስር የኮልባክ አገልግሎትን ይከለክላል። የኮልባክ አገልግሎት ማለት በአዋጁ አንቀጽ 2(3) ስር እንደሰፈረዉ የሀገር ውስጥ የቴሌኮም ድርጅት ሳያውቀው የሌላ ሀገር የቴሌኮም ድርጅት ጥሪ ቶንን ለዓለም አቀፍ ግንኙነት መጠቀም ወይም ዓለም ዓቀፍ የስልክ ጥሪዎችን የሀገር ውስጥ ማስመሰል ሲሆን በዓለም ዓቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት ኮልባክ ተብለው የሚታወቁ አገልግሎቶችንም ይጨምራል፤ ዓለም አቀፍ ጥሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ጥሪነት መቀየር መንግሥትና የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢው ከዓለም አቀፍ ጥሪ ሊያገኙት የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ ያሳጣል። ለደዋዩም የሀገር ውስጥ ቁጥር ስለሚታየው ጥሪው ከየት እንደተጀመረ ለማወቅ ያዳግታል። ይህ ድርጊት ለብሔራዊ ደኅንነትም ትልቅ ስጋት ነው። ስለሆነም፡-
- ማንኛውም ሰው የኮልባክ አገልግሎት የሰጠ እንደሆነ በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ከ5 እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና የኮልባክ አገልግሎቱን በሰጠበት ጊዜ ውስጥ ሊያገኝ ይችላል ተብሎ የሚገመተውን ገቢ አምስት እጥፍ የሚሆን መቀጮ ይቀጣል፡፡
- ማንኛውም ሰው አስቦ ወይም በቸልተኝነት የኮልባክ አገልግሎት ያገኘ እንደሆነ በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ከ3 ወር እስከ 2 ዓመት በሚደርስ እስራት እና ከብር 2ሺ500 እስከ ብር 20ሺ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡
ሕገ ወጥ የቴሌኮም ኦፕሬተርን ስለሚመለከቱ ወንጀሎች
በአዋጅ አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 1/ሀ/ እና/ለ/ እንዲሁም 3 ስር እንደቅደምተከተላቸው ከተፈቀደው የቴሌኮም ኦፕሬተር ውጪ መዘርጋት፣ አገልግሎት መስጠት ወይም ማግኘትን ይከለክላል፤ በመሆኑም ማንኛውም ሰው፡-
- የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ድርጅቱ ከዘረጋው የቴሌኮም መሰረተ ልማት ውጪ ማንኛውንም የቴሌኮም መሰረተ ልማት የዘረጋ እንደሆነ፤ ወይም
- የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ድርጅቱ የዘረጋውን የቴሌኮም መሰረተ ልማት ወደ ጐን ትቶ የአገር ውስጥም ሆነ ዓለም ዓቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት የሰጠ እንደሆነ ከ10 እስከ 20 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና አገልግሎቱን በሰጠበት ጊዜ ውስጥ ሊያገኝ ይችላል ተብሎ የሚገመተውን ገቢ አስር እጥፍ የሚሆን መቀጮ የሚቀጣ ሲሆን፣
- ማንኛውም ሰው አስቦ ወይም በቸልተኝነት በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ከተመለከተው ሕገ ወጥ የቴሌኮም ኦፕሬተር የቴሌኮም አገልግሎት ያገኘ እንደሆነ በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ከ3 ወር እስከ 2 ዓመት በሚደርስ እስራት እና ከብር 2ሺ500 እስከ ብር 20ሺ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡
ሌሎች ተያያዥ ወንጀሎች
በአዋጁ አንቀጽ 10 ንዑስ አንቀር 1 እስከ 4 ስር ሌሎች የቴሌኮም ማጭበርበር ጋር ተያያዥነት ያላቸው ድርጊቶች ላይ ክልከላ የሚጥል ሲሆን እነዚህም፡-
በሕገ ወጥ መንገድ ሲም ካርድ፣ ክሬዲት ካርድ፣ የደንበኞችን መለያ ቁጥር ወይም ዳታ የሚሰራ ወይም የሚያባዛ ወይም በሕገ ወጥ መንገድ የተባዙትን ሲም ካርዶች፣ የደንበኞች መለያ ቁጥሮች ወይም ዳታዎች የሚሸጥ ወይም በማናቸውም መንገድ የሚያሰራጭ ማንኛውም ሰው በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ከ10 እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከብር 100ሺ እስከ ብር 150ሺ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡
ማንኛውም ሰው፡-
- ማንኛውንም አይነት መሳሪያ ከሕዝብ ቴሌፎን ጋር በማገናኘት ወይም ማንኛውንም ሌላ መንገድ በመጠቀም በሕዝብ ቴሌፎን አማካኝነት በመደበኛ ሁኔታ ሊገኝ የማይችልን አገልግሎት ያገኘ እንደሆነ፤ ወይም
- የተሳሳተ ወይም የተጭበረበረ የደንበኝነት ስምምነት በማቅረብ፣ የሌላ ሰው የማንነት መለያ ኮድን በመጠቀም ወይም በሌላ ማንኛውም የተጭበረበረ መንገድ የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነ ወይም ሌሎች እንዲጠቀሙ ያደረገ እንደሆነ ከ3 እስከ 8 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከብር 30ሺ እስከ ብር 80ሺ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡
- ኢንተርኔትን በመጠቀም የስልክ ጥሪ ወይም የፋክስ አገልግሎት የሚሰጥ ማንኛውም ሰው በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ከ3 እስከ 8 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ሊያገኝ ይችላል ተብሎ የሚገመተውን ገቢ አምስት እጥፍ የሚሆን መቀጮ ይቀጣል፡፡
- ማንኛውም ሰው አስቦ ወይም በቸልተኝነት በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (3) የተመለከተውን አገልግሎት ያገኘ እንደሆነ በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ከ3 ወር እስከ 2 ዓመት በሚደርስ እስራት እና ከብር 2ሺ500 እስከ ብር 20ሺ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡
በሕግ የሰውነት መብት በተሰጠው አካል የሚፈፀም ወንጀል
ሌላዉ በአዋጁ በግልጽ የተደነገገዉ በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ተጠያቂ የሚሆንበት መንገድ በአንቀጽ 11 ስር ተደንግጎ የሚገኝ ሲሆን ህጋዊ ሰውነት ያለው ድርጅት በአዋጁ የተደነገጉትን ወንጀሎች ፈጽሞ ሲገኝ ለወንጀሉ የተደነገገው መቀጮ በአስር ተባዝቶ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
ንብረት ስለመውረስ
ሌላኛው በአዋጁ የተካተተው ነጥብ ንብረት የሚወረስበት ሂደት ሲሆን ይህም በአንቀጽ 12 ስር እንደተደነገገው ፍርድ ቤት በዚህ አዋጅ መሠረት በጥፋተኛ ላይ ቅጣት ሲወስን ወንጀሉን ለመፈጸም በጥቅም ላይ የዋለ ማንኛውም የቴሌኮም መሣሪያ በመንግሥት እንዲወረስ በተጨማሪነት ያዛል፡፡
ማጠቃለያ
የቴሌኮም ማጭበርበርን መከላከል የአንድ አካል ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የመንግሥት፣ የኩባንያዎች በተለይም የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እና የእያንዳንዱ ዜጋ የጋራ ርብርብ የሚጠይቅ ዘመቻ ነው። በመሆኑም ሁሉም አካላት ዘመኑ ካመጣቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር ራስን በማላመድ እና እነዚህ ያመጧቸው ተግዳሮቶችን በመከላከል የወንጀሎችን መበራከት መቀነስ ያስፈልጋቸዋል።