በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ውስብስም ከሆኑ የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ከሚባሉ ወንጀሎች የሚመደብ ሲሆን እንደ ወንጀል መቆጠር የጀመረው ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ነዉ፡፡ ይህ ወንጀል አገራችን ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጉዳት እያደረሱ ከሚገኙ ግንባር ቀደም ወንጀሎች አንዱ ነው፡፡ ወንጀሉን ለመከላከል የተለያዩ አለምአቀፍ እና አገራዊ ሕግጋት የወጡ ሲሆን በዚህ አጭር ጽሁፍ እነዚህኑ ሕግጋት መሠረት በማድረግ የወንጀሉን ምንነት፣ ወንጀሉ የሚፈጸምበትን ዓላማ፣ የአፈጻጸም ደረጃውንና ስልቶቹን እንዲሁም ስለሚያደርሰው ጉዳት እና የወንጀሉን መከላከያ መንገዶች ለማብራራት እንሞክራለን፡፡
የወንጀሉ ምንነት
በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ማለት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን የተገኘበትን ሁኔታ በመደበቅ ወይም በመሰወር ህጋዊ እንዲመስል የመቀየር ሂደት ነው፡፡ ሀገራችን ይሄንኑ ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ወጥቶ አሁን በስራ ላይ ያለው አዋጅ ቁጥር 780/2005 በአንቀጽ 29(1) ላይ እንዳስቀመጠው ማንኛውም ሰው ንብረቱ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው፡-
የንብረቱን ህገ ወጥ ምንጭ ለመደበቅ ወይም ለመሸፈን ወይም አመንጪዉን ወንጀል የፈጸመው ሰው ከሕግ ተጠያቂነት እንዲያመልጥ ለማድረግ ንብረቱን የለወጠ ወይም ያስተላለፈ እንደሆነ፤
ንብረቱን፣ የንብረቱን ትክክለኛነት፣ ምንጩን፣ ቦታውን፣ ዝውውሩን ወይም የባለቤትነት መብቱን የደበቀ ወይም እንዳይታወቅ ያደረገ እንደሆነ፤
ንብረቱን የተረከበ፣ በይዞታዉ ያደረገ ወይም የተጠቀመ እንደሆነ፣
ከላይ በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ወንጀልን የሚያቋቋሙት ተግባራትን በመፈጸም የተሳተፈ፣ ለመፈጸም ያደመ፣ የሞከረ፣ የረዳ፣ ያመቻቸ ወይም እንዲፈጸም ያማከረ እንደሆነ ይሄንኑ ወንጀል መፈጸም መሆኑን ደንግጓል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ሀገራችን አባል የሆነችበት የፓሌርሞው የተደራጁ እና ድምበር ተሻጋሪ የሆኑ ወንጀሎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው ስምምነት በአንቀጽ 6 እላይ ካነሳነው አዋጅ ቁጠር 780/2005 ድንጋጌ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ትርጉም ሰጥቶታል፡፡ በዚህ መልኩ ይህን ወንጀል መፈጸም በመደበኛነት በአዋጅ 780/05 አንቀጽ 29 እና 35 መሠረት የወንጀሉ መፈጸሚያ የሆነው፣ የወንጀሉ ፍሬ ወይም ይሄው ንብረት ያፈራው ንብረት የሚወረስ ሆኖ በተጨማሪም ወንጀለኛው ከ10-15 ዓመት ጽኑ እስራት እና እስከ 100,000 ብር የሚደርስ መቀጮ የሚቀጣ ሆኖ በተለየ ሁኔታ በዚሁ ሕግ አንቀት 29 ንዑስ አንቀጽ 2 ስር የተዘረዘሩት የቅጣት ማክበጃዎች ተሟልተው ሲገኙ ቅጣቱ ከ15-25 ዓመት ጽኑ እስራት እና እስከ 150,000 የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይሆናል፡፡
አመንጪ ወንጀል
በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ሊኖር የሚችለው ከመሰረቱ ሌላ ወንጀል በቅድሚያ ተፈጽሞ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ ተፈጥሮአዊ ባህሪው ቀድሞ በተፈጸመ ወንጀል ላይ ተመስርቶ ያለ ሲሆን በራሱ ሊቆም የሚችለው አስቀድሞ በተፈጸመ ወንጀል ላይ ተመስርቶ በሚፈጸም ተግባር እንደሆነ የሚወሰድ ሲሆን ይህም በወንጀል ላይ እንደተመሰረተ ወንጀል የሚቆጠር ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የመጀመሪያው ወንጀል አመንጪ ወንጀል ወይም (predicate offence) የሚባል ሲሆን ይህም የመጀመሪያ ጥፋት ገንዘብ ወይም ንብረት የተገኘበት መሆን የሚገባው ይሆናል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 780/05 አንቀጽ 2/4/ ላይ አመንጪ ወንጀል ማለት ማንኛውም የወንጀል ፍሬ ምንጭ የሆነና ቢያንስ አንድ ዓመት ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ወንጀሉ የሚነሳው ከአመንጪ ወንጀል ሲሆን ከአመንጪው ወንጀል ተለይቶ ሁለተኛ ሌላ ወንጀል የሚሆንበት ምክንያት በአዲስ የወንጀል ማድረግ ሀሳብ አመንጪ ወንጀሉን ተከትሎ በወንጀል ተግባር የተገኝውን ንብረት ህገወጥ ምንጭ ለመደበቅ ወይም ለመሸፈን ወይም አጥፊውን ከሕግ ተጠያቂነት ለማስመለጥ የሚፈፀም አዲስ የወንጀል ድርጊት ነው፡፡
የወንጀሉ ሂደቶች
ወንጀለኞች ከወንጀል ተግባራቸው ያገኙትን ንብረት ህጋዊ ለማስመሰል የሚሞክሩት በዋነኛነት ከወንጀል ክስ እና ከንብረት መወረስ ለማምለጥ ነው፡፡ እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት ደግሞ የወንጀል ፍሬውን ሕጋዊ አስመስለው ለማቅረብ የተለያዩ የሂደት ደረጃዎችን ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህን ሂደቶች ስናይ፡-የመጀመሪያው ሂደት ወደ ኢኮኖሚ ውስጥ ማስገባት (Placement) ይባላል፡፡ ይህ እንደመጀመሪያ ደረጃ ሂደት የሚወሰድ ሲሆን በወንጀል የተገኘው ፍሬ ወደ ህጋዊ ኢኮኖሚ የሚቀላቀልበት የመጀሪያው ሂደት ነው፡፡ ዓላማውም በወንጀል የተገኘው ገንዘብ/ንብረት ከመጣበት እውነተኛ ተፈጥሮው ወይም ምንጩ፣ ከተገኘበት አካባቢ እና ባለቤት እየተላቀቀ የሚሄድበት ሁኔታ እንዲኖር ወደ ኢኮኖሚ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያርፍበት ደረጃ ነው፡፡ ሁለተኛው ደረጃ መሸፋፈን (Layering) የሚባል ሲሆን የወንጀል ፍሬው ይበልጥ እንዳይደረስበት ህጋዊ የማስመሰል ሂደቱ እየተደራረበ እንዲሄድ የሚደረግበት ነው፡፡ በዚህ ሂደት በርካታ የመሸፋፈኛ ተግባራት የሚፈጸሙበት ሲሆን በርካታ ግብይቶችም /multiple layers of transactions/ ሊፈጸምበት የሚችል የወንጀሉ መፈጸሚያ ደረጃ ነው፡፡ ሶስተኛው እና የመጨረሻው ማዋኃድ (Integration) በመባል የሚጠቀስ ሲሆን የወንጀል ፍሬው በተለያየ ዘዴ እና በተደራረበ ተግባር አልፎ በመጨረሻም ኢኮኖሚ ውስጥ ተቀላቅሎ የህጋዊ ውጤት እንደሆነ የሚመስልበት ነው፡፡ ይህ ሕጋዊ የማስመሰል ሂደት ሁል ጊዜ ሶስቱን ደረጃዎ በጠበቀ መልክ ላይከሰት የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ አንደኛው ደረጃ ሳይኖር ሁለተኛው ደረጃ ሊከሰት ይችላል:: ከአዋጁ አንቀጽ 29 መረዳት እንደሚቻለው በየትኛውም ደረጃ ቢሆን የህጉን ወንጀል ማቋቋሚያ ካሟላ የሚያስጠይቅ ይሆናል፡፡
በወንጀል ድርጊት የተገኘን ግንዘብ/ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ተቀጽላ ወንጀሎች
ይህ ወንጀል በህጉ የተለየ ኃላፊነት የተጣለባቸውን ሰዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት እና ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ የተሰየሙ የንግድ እና የሙያ ስራዎችን የሚመለከት ወንጀል ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት እና ሰዎች በአዋጁ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ በማስመሰል ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን በመከላከል ሂደት ኃላፊነት የተጣለባቸው ናቸው፡፡ተቋማቱ ደንበኞቻቸውን የመለየት፣ መረጃ የመያዝ፣ አጠራጣሪ ግብይቶችን ወይም ጥሬ ገንዘብ ዝውውሮችን ሪፖርት የማድረግ፣ የሚሰጡ ትእዛዞችን እና የቁጥጥር ትእዛዞችን ተግባራዊ የማድረግ፣ መረጃ እንዲሰጥ ሲጠየቅ የመተባበር ግዳታ እንዳለባቸው በአዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 30 ከተዘረዘሩት ግዴታዎች ለመረዳት ይቻላል፡፡ ይህን ግዴታ አለመወጣት እንደተባለውም አለመፈፀም የተቀፅላ ወንጀል ሆኖ ቅጣት የሚያስከትል ነው፡፡ ቅጣቱም ከ3-5 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት እና እስከ 10ሺ ብር መቀጮ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ለ5 ዓመት ወይም ለዘለቄታው ከሞያ ስራ መታገድ እና ድርጅትን እስከ ማፍረስ የሚደርስ አስተዳደራዊ አርምጃ ያስከትላል፡፡
ወንጀሉ የሚያደርሰው ጉዳት
ወንጀሉ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጉዳቶች የሚደርስ ሲሆን ጥቂቶቹን ለማንሳት፡-
- የገበያ ወድድር መርህን ማበላሸት እና በህጋዊ ነጋዴዎችን ከገበያው ማስወጣት፣
- የሀገሪቱን ሀብት የመዘረፍና የመሰወር ብሎም ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍልን ማዛባት፣
- በፋይናንስ ተቋማት መልካም ስም፣ በህጋዊነታቸው ላይ ወይም በገንዘብ ክምችታቸው ላይ ያልተጠበቀ ጉዳት ያደርሳል፣
- ለወንጀል መስፋፋት መንስዔ ይሆናል፡፡ ለወንጀለኞች የማስፈጸሚ አቅም በመሆን
- ሀገራዊ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሳል፡፡ የመሸጫ ዋጋን በማዛባት ያልተረጋጋ የፋይናንስ ግብይት፣ ኢንቨስትመንትን በመቀነስ ዘላቂ የሆነ ልማት እንዳይኖር ያደርጋል፣
- መንግሥት ሊሰበስበው የሚችለውን ገቢም በማሳጣት፣ በተለይ ለግብር ስወራ እና ለህገ ወጥ ምንዛሪዎች የተጋለጥ ይሆናል፣
- ወንጀሉ በስፋት የሚፈፀም ከሆነና የመቆጣጠር አቅም አናሳ ሲሆን ሀገርን አለምአቀፍ የፋይናንስ ማእቀብ ማዕቀፍ ውስጥ ይጨምራል፣
- የሕግ የበላይነት እና መልካም አስተዳደር እንዳይሰፍን ያደርጋል፣ በህገ ወጥ መንገድ ሀብት ማፍራት እንደሚቻል አመለካከትን ያሰፍናል፡፡
ወንጀሉን መከላከያ መንገዶች
ወንጀሉን ለመከላከል በዋናነት ለወንጀሉ መፈጸም እንደ ምቹ መሸጋገሪያ ሆነው የሚያገለግሉ የፋይናንስ እና ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ ተቋማት የሚከተሉትን የወንጀሉን መከላከለያ እርምጃ በተግባር መውሰዳቸውን እያረጋገጡ መሄድ ያስፈልጋል፡፡
- የሚያጠራጥር ግብይት ሲያጋጥም ለፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ሪፖርት ማቅረብ፣
- የደንበኞችን ማንነት በሚገባ ማጣራት እና መመዝገብ፣
- የግብይት ሰነዶችን በሥርዓት መያዝ፣
- በሕግ ከተወሰነው ዝቅተኛ መጠን በላይ ገንዘብ በግለሰብ እጅ እንዳይገባ መቆጣጠር
- ደምበኞቻቸው ለፖለቲካ ተጽኖ የተጋለጡ ግለሰቦች መሆን አለመሆናቸውን ለማጣራት እና የግብይቶች የመጨረሻ ተጠቃሚ ማን እንደሆነ ለማወቅ በሚያስችል መልኩ የስጋት መቀነሻ ዘዴ ተግባራዊ ማድረግ አለበት፡፡
- በተቋሞቻቸው በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ/ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ የሚከላከሉ መዋቅሮች እና አሰራሮች መዘርጋት፣
በየጊዜው የሚታደስ የተቋም የውስጥ የህገወጥ የገንዘብ ዝውውር በተመለከተ ያለውን ተጋላጭነት ማጥናት እና ለመከላከል የሚያስችል በቂ የፖሊሲ አቅጣጫ ማስቀመጥና መተግበር አለባቸው፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ