ወንጀል ህብረተሰብን የሚጎዳ ተግባር በመሆኑ ወንጀል ፈፃሚዎች ከመጥፎ ተግባራቸው እንዲታቀቡ እና እንዲታረሙ በሕግ የተቀመጠ ቅጣት ይጣልባቸዋል፡፡ ተቀጪዎች የተወሰነባቸውን ቅጣት ለማስፈፀም ሥልጣን በተሰጣቸው ማረሚያ ቤቶች አማካኝነት እንዲፈፅሙ ይደረጋል፡፡ ሆኖም የወንጀለኛውን ጠባይ ለማረምና ለማሻሻል ወደ መደበኛ ማኅበራዊ ኑሮው ለመመለስ አስፈላጊ መሆኑን ፍርድ ቤት ባመነበት ጊዜ በጥፋተኛው ላይ የተወሰነውን ቅጣት ለጊዜው በገደብ እንዲታገድ ሊደረግ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ በሕጉ መሠረት የሚሰጡት ውሳኔዎች የወንጀለኛውን የመታረም መልካም ፈቃድ የሚፈልጉ ስለሆነ መልካም ውጤትን ለመስጠት አለመቻላቸው ሲታወቅ በማናቸውም ጊዜ የሚሻሩ ናቸው። በዚህ ጽሑፍ የቅጣት ገደብን ምንነት፣ ገደብ (የፈተና ጊዜ) የሚሰጥባቸው ሁኔታዎች እና የገደብ ፍሬ አለማስገኘት የሚያስከትለው ውጤት እንመለከታለን።
የቅጣት ገደብ ምንነት
የቅጣት ገደብ ፍርድ ቤት አንድ ጥፋተኛ የተባለን ሰው ለጥፋቱ መነሻ የሆኑትን ምክንያቶችን በጠቅላላው በመመልከት ጥፋተኛው ቅጣቱን ከመፈፀሙ በፊት ፅኑ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠው እና ለተወሰነ ጊዜ ቅጣቱ ታግዶለት አመሉ ቢፈተን ሁለተኛ ጥፋት ከማድረግ የሚታገድ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ባመነበት ጊዜ ቅጣቱ እንዳይፈፀም አግዶ የጥፋተኛው አመል የሚፈተንበት ሂደት ነው፡፡
ቅጣት የሚገደብባቸው እና ገደብ የሚከለከልባቸው ሁኔታዎች
ፍርድ ቤቱ በወንጀል አድራጊው ላይ የተወሰነበት ቅጣት የሚያግድለት ጥፋተኛው በመልካም ጠባይ እንደሚመራ፣ እንዲፈፅም የተሰጠውን ግዴታ እንደሚቀበል እንዲሁም በሚቻለው መንገድ ሁሉ በጥፋቱ ያደረሰውን ጉዳት እንደሚክስ ወይም ለተበዳዩ እንደሚከፍልና ለዚሁ ጉዳይ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ የፍርድ ቤቱን ወጪ እንደሚከፍል ማረጋገጫ ከሰጠ በኋላ ነው (አንቀጽ 197)። ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛው ለገባበት ግዴታ አፈፃፀም መተማመኛ ዋስትና እንዲሰጥ ያስገድደዋል። ፍርድ ቤቱ መተማመኛውን የሚወስነው እንደነገሩ ሁኔታና እንደ ጥፋተኛው ችሎታ መጠን ሲሆን መተማመኛው በሰው ዋስትና ወይም በንብረትና በገንዘብ መያዣ ሊሰጥ ይችላል።
በአንፃሩ የወንጀል ህጉ ቅጣት እንዳይገደብ የሚከለክልባቸው ምክንያቶችን የደነገገ ሲሆን እነዚህ ሁኔታዎች በተገኙ ጊዜ ቅጣት ሊገደብ አይችልም፡፡ ይኸውም ፡-
- ሀ. ስለደጋጋሚነት የተፃፉት ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆኖ ጥፋተኛው ከዚህ በፊት የፅኑ እስራት ቅጣት ወይም ከ3 ዓመት የሚበልጥ የቀላል እስራት ቅጣት ተፈርዶበት እንደሆነና እንደገናም በተከሰሰበት ወንጀል ከእነዚህ ቅጣቶች አንዱ የሚወሰንበት እንደሆነ ወይም
- ለ. ከዚህ ቀደም ያልተቀጣ ሆኖ አሁን በተከሰሰበት ወንጀል ከ5 ዓመት የበለጠ የፅኑ እስራት ቅጣት የሚፈረድበት እንደሆነ ነው (አንቀጽ 194) ።
እንዲሁም፡-
- የቅጣቱ አፈፃፀም ከመታገዱ በፊት ጥፋተኛው ሌላ ወንጀል ፈፅሞ እንደነበረ የተደረሰበት ሲሆንና በዚሁ ወንጀል ምክንያት የሚፈረድበት የቅጣት ዓይነትና መጠን ከዚህ በላይ በፊደል ሀ የተመለከተውን ሁኔታ የሚያሟላ ሲሆን ወይም
- ወንጀለኛው ቅጣቱ ታግዶለት ለፈተና በተለቀቀበት ጊዜ ውስጥ አስቦ አንድን ወንጀል ያደረገ እንደሆነ ወይም
- የቅጣት አፈፃፀሙ በታገደለት ጉዳይ የተሰጠው የፈተና ጊዜ መልካም ፍሬ የሚያስገኝ አለመሆኑን ፍርድ ቤቱ ሲረዳው
ቅጣት ሊገደብ አይችልም፡፡
ለገደብ የሚሰጥ ጊዜ
በወንጀል ህጉ አንቀጽ 196(2) መሠረት ፍርድ ቤቱ ለጥፋተኛው የሚሰጠውን የፈተና ጊዜ የሚወስነው የወንጀሉን ከባድነት፣ በወንጀል ድርጊት መደጋገም ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት እና በተጥፋተኛው ላይ ሊጥልበት የሚቻለውን እምነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።
የፈተናው ጊዜ ከ2 ዓመት ሊያንስ ከ5 ዓመት ሊበልጥ አይችልም። ይህ ጊዜ የሚታሰበውም የመጨረሻ ፍርድ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ ነው ይሆናል።
የቅጣት ገደብ አሰጠጥ እና የሚያስከትለው ውጤት
ፍርድ ቤቱ ማስረጃ ሰምቶ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ከሰጠ እና ግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ከሰማ በኋላ ቅጣት የሚወስን ሲሆን የቅጣት አፈፃፀሙን በተመለከተ በዛው መዝገብ ላይ ይወስናል። በተለይም የተከሳሽን አጠቃላይ ሁኔታና የመታረም እድሉን በማገናዘብ የተጣለን ቅጣት በመገደብ የተወሰነ የፈተና ጊዜ በመስጠት የቅጣቱ አፈፃፀም ታግዶ እንዲቀይ ሊያዝ ይችላል። ፍርድ ቤቱ የወሰናቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች ግን አያግድለትም። ፈተናው መልካም ፍሬ ያስገኘ እንደሆነ ጥፋተኛው የተወሰነበትን ቅጣት አይፈፀምም፡፡ የፍርዱ ውሳኔ ግን በወንጀለኞች መዝገብ ላይ ተመዝግቦ ከሌላው ውጤት ጋር ተመዝግቦ ይቀመጣል (አንቀጽ 192)።
የፈተናው (ገደቡ) ፍሬ አለማስገኘት የሚያስከትለው ውጤት
ፍርዱ የታገደለት ጥፋተኛ ለፈተኛ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ በግዴታ እንዲከተላቸው ከተሰጡት የጠባይ አመራር ደንቦች አንዱን የጣሰ፣ ከአሳዳሪው ጥበቃ ወይም ከቁጥጥር ለማምለጥ የሞከረ፣ በቸልተኛነት ወንጀል ያደረገ ወይም የተጣለበትን እምነት ያጓደለ እንደሆነ ላደረገው ወንጀል መከሰሱ እንደተጠበቀ ሆኖ ፍርድ ቤቱ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል። አስፈላጊም ሲሆን በሕጉ ዕቅድና ወሰን ውስጥ እንደተመለከተው በፊት ተወስኖ የነበረውን የፈተና ጊዜ ለማራዘም ወይም አዲስ የጠባይ አመራር ደንብ አንዲከተል ሊማስገደድ ይቻላል።
ጥፋተኛው ማስጠንቀቀያ ከተሰጠው በኋላ በመጥፎ የጠባይ የቀጠለ እንደሆነ ወይም ለፈተና በተወሰነለት ጊዜ ውስጥ አስቦ አዲስ ወንጀል ያደረገ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ የፍርዱን ማገድ ትእዛዝ ይሽራል። ነገር ግን ጥፋተኛው የሚያቀርበው ሀሳብ በቅድሚያ የመሰማት መብት አለው። ጥፋተኛው ለፈተና በተሰጠው ጊዜ ውስጥ አስቦ አዲስ ወንጀል ሰርቶ የተፈረደበት እንደሆነ ዳግመኛ የፍርድ ማገድ ትእዛዝ ሊሰጠው አይችልም፡፡ በእንደዚህ ባለ ጊዜ ፍርድ ቤት አግዶት የነበረውን የቅጣት ገደብ በመሻር ቅጣት ወስኖ እንዲፈፀም ወይም ተወስኖ የነበረው ቅጣት እንዲፈፀምበት ያደርጋል።
የቅጣቱ እግድ የሚሻረው ጥፋተኛው አዲስ ወንጀል አስቦ በማድረጉ ምክንያት እንደሆነ ስለደጋጋሚነት የተመለከቱት ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው አስቀድሞ ለተፈረደበት ወንጀል ከተወሰነው ቅጣት ጋር የአዲሱ ወንጀል ቅጣት ተደምሮ ተፈፃሚ ይሆናል።
በአጠቃላይ ወንጀል የፈፀመ ተከሳሽን ፍርድ ቤቱ ጥፋተኝነቱ አረጋግጦ የወንጀል ቅጣት የሚወሰንበት ሲሆን በህጉ የተደነገጉት ሁኔታዎች ተሟልተው ሲገኙ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባለ ሰው ቅጣቱ ተገድቦለት ጠባዩ እንዲፈተን ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህም በቀላሉ ሊታረም የሚችል ጥፋተኛ ሰው ቅጣቱ ሳይፈፀም የመታረም እድል እንዲያገኝ ከማድረጉም በተጨማሪ በእስራት ምክንያት በጥፋተኛው ቤተሰብም ሆነ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚደርስን ጫና ለማቃለል ጠቀሜታው የጎላ ነው።
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ