የበቀል እርምጃ በህግ ያስጠይቃል

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

ማንኛውንም ተሿሚ ወይም ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ ሀብቱን ያላስመዘገበ መሆኑን የሚያውቅ ማንኛውም ሰው ጥቆማ መስጠት የሚችል ሲሆን ጠቋሚው ላይ የሚደርስ ማንኛውም የበቀል እርምጃ በሕግ የሚያስጠይቅ ተግባር ነው።

ይህ ‘ከነጋሪት ገጾች’ በሚል በአገራችን ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ህጎችን የምናጋራበት አምድ ነው፡፡

በዛሬው የነጋሪት ገጾች አምዳችን ‘የሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅ ቁጥር 668/2002 ስር ስለ ሀብት ማስመዘገብ ግዴታ እና ግዴታቸውን ባለወተወጡ ሰዎች ላይ የሚቀርብን ጥቆማ ተከትሎ በጠቋሚ ላይ የበቀል እርምጃ መውሰድ የሚያስከትለውን ተጠያቂነት ተመልክተናል፡፡

አዋጅ ቁጥር 668/2002 በፌዴራል መንግሥት እና በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደሮች ተሿሚዎች፣ ተመራጮችና የመንግሥት ሠራተኞች ላይ ተፈጻሚ የሚሆን ሲሆን ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ በራሱና በቤተሰቡ ባለቤትነት ወይም ይዞታ ሥር የሚገኝ ሀብትን፣ እና የራሱንና የቤተሰቡን የገቢ ምንጮች፣ የማሳወቅና የማስመዝገብ ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

ማንኛውም ሰው ‘‘የሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅ ቁጥር 668/2002”ን ጥሷል በሚለው ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ ላይ ጥቆማ ማቅረብ ይችላል።

ጥቆማው እስከተቻለ ድረስ ከደጋፊ ማስረጃ ጋር በጽሑፍ ለሥነ-ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ወይም አግባብ ላለው የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል ይቀርባል፡፡

ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ ማንኛውም ሰው ለኮሚሽኑ ወይም ለሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል ጥቆማ አቅርቧል ወይም ምስክርነት ሰጥቷል ወይም ጥቆማ ለማቅረብ ወይም ምስክርነት ለመስጠት ተዘጋጅቷል በሚል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የበቀል እርምጃ የወሰደ እንደሆነ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 444 ላይ ስለ ጠቋሚዎች እና ምስክሮች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የሚደነግገው ሕግ ተፈጻሚ ይሆንበታል።

የአዋጅ ቁጥር 668/2002ን ሙሉ ይዘት ለማንበብ የተቋማችንን ድረ ገጽ www.eag.gov.etን ይጎብኙ ወይም በበየነ መረብ አማካኝነት የተጋሩ ቅጂዎችን ወይም ከብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ገዝታችሁ ማንበብ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻን፡፡

ሕግን ለማወቅ ተገቢውን ጥረት በማድረግ መብት እና ግዴታውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ትውልድ አካል እንሁን!