መግቢያ
በአንድ አገር ውስጥ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን፣ የወንጀል ድርጊትን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የህብርተሰቡ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ የወንጀል ድርጊት ሲፈፀም ጥቆማ መስጠት እና ምስክር መሆን ድግሞ ህብረተሰቡ ወንጀልን በመከላከል ረግድ ከሚያበረክተው አስተፅኦ ዋነኛው ነው፡፡ በአንፃሩም ጠቋሚዎችና ምስክሮች ጥቆማና ምስክርነት በሚሰጡበት ጊዜም ሆነ ከሰጡም በኋላ ጠቋሚ ወይም ምስክር በመሆናቸው ምክንያት በእነርሱ እና በቤተሰቦቻቸው ላይ ሊደርስ ከሚችል ጉዳት መጠበቅ አለባቸው፡፡ በዚህም ምክንያት የተለያዩ የአለማችን ሀገራት ለወንጀል ጠቋሚዎችና ምስክሮች ጥበቃ የሚያደርጉ ሲሆን ይህን የሚያደርጉትም ከባድ እና የተደራጁ ወንጀሎችን በሚመለከት ለሚቀርቡ ጠቋሚዎችና ምስክሮች ነው፡፡ ሀገራችንም ይህንኑ በመረዳት የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አውጥታ በሕግ በተመለከቱ ወንጀሎች ላይ ምስክሮችና ጠቋሚዎች ለሆኑ ሰዎች ጥበቃ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ ጽሑፍ የምስክር እና ጠቋሚዎችን ጥበቃ ምንነትና የጥበቃ ስምምነት፣ የጥበቃ እርምጃ ዓይነቶችን እና ጥበቃ የሚደረግባቸውን ወንጀሎች በአጭሩ እንዳስሳለን፡፡
የጠቋሚዎችና ምስክሮች ጥበቃ ምንነት እና የጥበቃ ስምምነት
የጠቋሚዎችና ምስክሮች ጥበቃ ማለት አንድን ወንጀል በተመለከተ የሚያውቀውን ለፍርድ ቤት ወይም ለፖሊስ ለመግለፅ የተስማማ ጠቋሚ ወይም ምስክር ቃሉን ወይም መረጃውን በመስጠቱ ምክንያት በራሱ ወይም በቤተሰቡ ላይ ከሚቃጣበት ጉዳት የሚጠበቅበት በሕግ የተዘረጋ ሥርአት ነው፡፡ ይህም በጥበቃ ስምምነት መሠረት የሚፈፀም ሲሆን ስምምነቱ በጥበቃ ተጠቃሚው እና በፍትሕ ሚኒስቴር መካከል የሚደረግ ነው፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 2(2) መሠረት የጥበቃ ተጠቃሚ ከሚኒስቴሩ ጋር የጥበቃ ስምምነት የተፈራረመ ጠቋሚ ወይም የምስክር ወይም የጠቋሚ ወይም የምስክር ቤተሰብ አባል ነው፡፡ የጥበቃ ተጠቃሚው አካለ መጠን ያላደረሰ ወይም በፍርድ የተከለከለ ሰው ከሆነ የጥበቃ ስምምነቱ ከወላጆቹ ወይም ከአሳዳሪው ጋር የሚፈረም ሲሆን ነገር ግን የጥበቃ ተጠቃሚው አካለ መጠን ከደረሰ ወይም የሕግ ችሎታውን መልሶ ካገኘ በኋላ ጥበቃው የሚቀጥል ከሆነ ስምምነቱን የጥበቃ ተጠቃሚው ራሱ መፈረም እንዳለበት በአዋጁ አንቀጽ 8(3) ተደንግጎ ይገኛል፡፡
የጥበቃ ተጠቃሚ የሆነው አካለ መጠን ያላደረሰ ልጅ መረጃ ወይም ምስክርነት የሚሰጠው በወላጁ ወይም በአሳዳሪው ላይ ሲሆን፣ ወላጅ ወይም አሳዳሪ የሌለው ሲሆን፣ አስፈላጊው ጥረት ተደርጎ ወላጁን ወይም አሳዳሪውን ማግኘት ያልተቻለ እንደሆነ፣ ወላጁ ወይም አሳዳሪው በቂ ባልሆነ ምክንያት ፈቃዱን ሳይሰጥ ሲቀር ወይም በማናቸውም ምክንያት ፈቃዱን መስጠት ሳይችል ሲቀር ሚኒስቴሩ ከልጁ ጋር ልዩ የጥበቃ ስምምነት ሊፈራረም እንደሚችል ከአዋጁ አንቀጽ 9(1) መረዳት ይቻላል፡፡ ሆኖም አካለ መጠን ካላደረሰ ልጅ ጋር የተደረገ ልዩ የጥበቃ ስምምነት ከተፈረመበት ዕለት ጀምሮ ባሉት አስር ቀናት ውስጥ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ መጽደቅ አለበት፡፡ ፍርድ ቤቱም አካለ መጠን ያላደረሰው ልጅ ጥቅምና ደኅንነት ይበልጥ ሊረጋገጥ የሚችልበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የጥበቃ ስምምነቱን መሻር፣ ማጽደቅ ወይም ማሻሻል እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 9(4) ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡
የጥበቃ እርምጃ ዓይነቶች
ለወንጀል ጠቋሚዎችና ምስክሮች የሚደረጉ የጥበቃ እና የጥንቃቄ እርምጃዎች በአዋጁ አንቀጽ 4 ስር ተዘርዝረው ይገኛሉ፡፡ የጥበቃ እና የጥንቃቄ እርምጃዎች እንደ ሁኔታው በተናጠል ወይም በጣምራ ለጥበቃ ተጠቃሚ ተፈጻሚ የሚደረጉ ሲሆን ይህም ፡-
- የአካልና ንብረት ደኅንነት ጥበቃ
- የመኖሪያ ስፍራ መቀየርን ጨምሮ ደህንነቱ የተጠበቀ የመኖሪያ ቦታ መስጠት
- ማንነትንና ባለንብረትነትን መደበቅ
- ማንነትን መቀየር
- ለራስ መጠበቂያ የነፍስ ወከፍ መሳሪያ መስጠት
- መረጃ በተሰጠበት የወንጀል ድርጊት ያለመከሰስ
- መረጃ በሚሰጥበት የወንጀል ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊትም ሆነ በኋላ ተከሳሽ በጥበቃ ተጠቃሚው መኖሪያ ወይም የሥራ ቦታ ወይም ትምህርት ቤት አካባቢ እንዳይደርስ ማገድ
- የፍርድ ሂደት ተጀምሮ ምስክርነት እስከሚሰጥ ድረስ የምስክር ማንነት እንዳይገለጽ ማድረግ
- ምስክርነት በዝግ ችሎት እንዲሰጥ ማድረግ
- ምስክርነት በአካል ሳይታይ ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆኖ ወይም ማንነትን በመሸፈን እንዲሰጥ ማድረግ
- ማስረጃ በኤሌክትሮኒክስ ወይም በሌላ የተለየ ዘዴ እንዲቀርብ ማድረግ
- በሚስጥር መያዝ ያለበት ካልሆነ በስተቀር ለጠቋሚ ጥቆማ ባቀረበበት ጉዳይ ላይ ወቅታዊ መረጃና ምክር መስጠት
- እንዲመሰክር ለተጠራ ምስክር የጉዞና የውሎ አበል መስጠት
- የጥበቃ እርምጃው የመኖሪያ ስፍራን ለውጥ ካስከተለ የጓዝ ማንሻ ወጪን መሸፈን
- በበቀል የተወሰደ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲታገድ ወይም እንዲሻር ማድረግ ወይም ተመጣጣኝ የሆነ የማካካሻ እርምጃ መውሰድ
- በበቀል እርምጃ ለደረሰ ጉዳት የህክምና አገልግሎት በመንግሥት ሆስፒታል በነጻ መስጠት
- በጥበቃ እርምጃው ምክንያት ለደረሰ የገቢ ማጣት ወይም በበቀል እርምጃ ለደረሰ የመሥራት ችሎታ ማጣት የመሠረታዊ ፍላጎት ማሟያ ወጪን መሸፈን
- በጥበቃ ሥር እያለ ለደረሰ ሞት የቀብር ማስፈጸሚያ ወጪ መሸፈንና ለቤተሰብ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ
- የጥበቃ ተጠቃሚው የሥራና የትምህርት ዕድል እንዲያገኝ መርዳት
- ለምስክሩ ወይም ለጠቋሚው የምክር አገልግሎት መስጠት ወይም እንዲያገኝ ማድረግን የሚያካትት ነው፡፡
ለምስክር ወይም ጠቋሚዎች ጥበቃ የሚደረግባቸው ወንጀሎች
የምስክር እና ጠቋሚዎች ጥበቃ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ጊዜ እና ወጪን የሚጠይቁ በመሆኑ ከአገራችን እድገት እና የኢኮኖሚ አቅም አኳያ ለሁሉም ምስክሮች እና የወንጀል ጠቋሚዎች ከለላ እና ጥበቃ ማድረግ አይቻልም፡፡ ስለሆነም ለምስክሮች ወይም ለጠቋሚዎች ጥበቃ የሚደረገው በህጉ ለተመለከቱት ወንጀሎች ሲሆን በወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ 3 መሠረት የጥበቃ እና የጥንቃቄ እርምጃዎች ማግኘት የሚቻለው የፅኑ እስራት መነሻው ግምት ውስጥ ሳይገባ 10 (አስር ዓመት) እና ከዚያ በላይ በሆነ ፅኑ እስራት ወይም በሞት ሊያስቀጣ በሚችል ወንጀል ምስክርነት ወይም ጥቆማን የተመለከተ ሆኖ
- የወንጀል ድርጊቱ ያለምስክሩ ወይም ያለጠቋሚው ምስክርነት ወይም ጥቆማ በሌላ ማናቸውም መንገድ ሊረጋገጥ ወይም ሊደረስበት የማይችል ሲሆን እና
- በምስክሩ፣ በጠቋሚው ወይም በቤተሰቡ ህይወት፣ አካላዊ ደህንነ፣ ነጻነት ወይም ንብረት ላይ ከባድ አደጋ ያደርሳል ተብሎ ሲታመን እንደሆነ ከአዋጁ አንቀጽ 3(1) መረዳት ይቻላል፡፡
ለአብነትም በኢትዮጵያ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 16 እና በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀጽ 25 የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች በአዋጅ ቁጥር 699/2003 መሠረት ለወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ስለሚደረግ ጥበቃ ደንግገው ይገኛሉ፡፡
ነገር ግን አዋጁ ይህንን መስፈርት ቢያስቀምጥም የፍትሕ ሚኒስቴሩ የጥበቃ ተጠቃሚ ላልሆኑ ለማንኛቸውም ምስክሮችና ጠቋሚዎችም በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4 ስር ከተቀመጡ አንዳንድ ጥበቃዎችን እንደአስፈላጊነቱ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህም
- በሚስጥር መያዝ ያለበት ካልሆነ በስተቀር ለጠቋሚ ጥቆማ ባቀረበበት ጉዳይ ላይ ወቅታዊ መረጃና ምክር መስጠት
- እንዲመሰክር ለተጠራ ምስክር የጉዞና የውሎ አበል መስጠት
- በበቀል የተወሰደ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲታገድ ወይም እንዲሻር ማድረግ ወይም ተመጣጣኝ የሆነ የማካካሻ እርምጃ መውሰድ
- በበቀል እርምጃ ለደረሰ ጉዳት የህክምና አገልግሎት በመንግሥት ሆስፒታል በነጻ መስጠት
- ለምስክሩ ወይም ለጠቋሚው የምክር አገልግሎት መስጠት ወይም እንዲያገኝ ማድረግን የሚያካትት ነው፡፡
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ የሕግ የበላይነትን በማስፈን ሂደት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ሲሆን የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ወንጀል ጠቆሚዎች እና ምስክሮች ወንጀልን በማጋለጣቸው ምክንያት ጉዳት እንዳይደርስባቸው ተገቢውን የሕግ ጥበቃ ማድረግ እና ህጉን ተፈፃሚ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ