መግቢያ
የወንጀል ድርጊትን ለመቆጣጥር እና ለመከላከል እንዲሁም ወንጀለኞች የወንጀል ድርጊት ከፈፀሙ በኋላ ተደብቀው እንዳይቀሩና ሕግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ የወንጀል ምስክሮች እና ጠቋሚዎች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ይህን ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በምስክርነታቸው ወይም በጠቋሚነታቸው ምክንያት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ከሚደርስባቸው አደጋና ጥቃት መከላከል አስፈላጊ ነው፡፡ ሀገራችንም ይህንኑ በመረዳት የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ ሕግ አውጥታ ሥራ ላይ ውሏል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ የምስክር እና የጠቋሚዎች ምንነት፣ በአዋጁ የተካተቱ የጥበቃ እርምጃ ዓይነቶችን እና የጥበቃ ስምምነት እንዳስሳለን፡፡
የምስክር እና ጠቋሚዎች ምንነት
ጠቋሚ ወይም ምስክር ማለት በወንጀል ምርመራ፣ በወንጀል ክስ ወይም በወንጀል ማጣራት ሒደት መረጃ ወይም ምስክርነት የሰጠ ወይም ለመስጠት የተስማማ ሰው እንደሆነ በአዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ 2(1) ላይ ትርጓሜ ተሰጥቶታል፡፡
የጥበቃ ተጠቃሚነት እና ተፈፃሚነቱ
በአዋጁ አንቀጽ 2(2) የጥበቃ ተጠቃሚ ማለት ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር የጥበቃ ስምምነት የተፈራረመ ምስክር፣ ጠቋሚ ወይም የምስክር ወይም የጠቋሚ ቤተሰብ አባል ነው፡፡ በዚህ መልኩ ስምምነት የገባ ምስክር ወይም ጠቋሚ በአዋጅ ላይ የተቀመጡት የጥበቃ እና የጥንቃቄ እርምጃዎች ይደረጉለታል፡፡ ሆኖም እነዚህ የጥበቃ እና የጥንቃቄ እርምጃዎች ከፍተኛ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ጊዜ፣ ገንዘብ እና ወጪን የሚጠይቁ በመሆኑ ከአገራችን እድገት እና የኢኮኖሚ አቅም አኳያ ለሁሉም ምስክሮች እና የወንጀል ጠቋሚዎች ከለላ እና ጥበቃ ማድረግ አይቻልም፡፡ በመሆኑም የጥበቃ እና የጥንቃቄ እርምጃዎች ማግኘት የሚቻለው በአዋጁ ላይ የተቀመጡት መስፈርቶች ተሟልተው ሲገኙ እንደሆነ በአዋጁ አንቀጽ 3 ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት የሚደረጉ የጥበቃ እና ጥንቃቄ እርምጃዎች ተፈፃሚ የሚሆኑት፡-
- በሕግ የተደነገገው የፅኑ እስራት መነሻ ከግምት ሳይገባ አስር ዓመትና ከዚያ በላይ በሆነ ፅኑ እስራት ወይም በሞት ሊያስቀጣ በሚችል የወንጀል ድርጊት ተጠርጣሪ ላይ የሚሰጥ ምስክርነትን ወይም ጥቆማን ወይም የሚካሄድ ምርመራን በሚመለከት ሆኖ:-
- የወንጀል ድርጊቱ ያለምስክሩ ወይም ያለጠቋሚው ምስክርነት ወይም ጥቆማ በሌላ ማናቸውም መንገድ ሊረጋገጥ ወይም ሊደረስበት የማይችል ሲሆን እና
- በምስክሩ፣ በጠቋሚው ወይም በምስክሩ ወይም በጠቋሚው ቤተሰብ ህይወት፣ አካላዊ ደኅንነት፣ ነጻነት ወይም ንብረት ላይ ከባድ አደጋ ይደርሳል ተብሎ ሲታመን ነው፡፡
ነገር ግን አዋጁ ይህንን መስፈርት ቢያስቀምጥም ፍትሕ ሚኒስቴር እና የፌዴራል የሥነምግባርና የጸረ-ሙስና ኮሚሽን የጥበቃ ተጠቃሚ ላልሆኑ ምስክሮችና ጠቋሚዎችም በአዋጁ አንቀጽ 4 ስር የተቀመጡ አንዳንድ ጥበቃዎችን እንደአስፈላጊነቱ ሊያደርግ እንደሚችል ይገልፃል፡፡
ይህም በሚስጥር መያዝ ያለበት ካልሆነ በስተቀር ለጠቋሚ ጥቆማ ባቀረበበት ጉዳይ ላይ ወቅታዊ መረጃና ምክር መስጠት እንዲመሰክር ለተጠራ ምስክር የጉዞና የውሎ አበል መስጠት
በበቀል የተወሰደ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲታገድ ወይም እንዲሻር ማድረግ ወይም ተመጣጣኝ የሆነ የማካካሻ እርምጃ መውሰድ በበቀል እርምጃ ለደረሰ ጉዳት የህክምና አገልግሎት በመንግሥት ሆስፒታል በነፃ መስጠት ለምስክሩ ወይም ለጠቋሚው የምክር አገልግሎት መስጠት ወይም እንዲያገኝ ማድረግን የሚያካትት ነው፡፡
የጥበቃ እርምጃ ዓይነቶች
ለወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች የሚደረጉ የጥበቃ እና የጥንቃቄ እርምጃዎች በአዋጁ አንቀጽ 4 ስር ተዘርዝረው ይገኛሉ፡፡ የጥበቃ እና የጥንቃቄ እርምጃዎች እንደ ሁኔታው በተናጠል ወይም በጣምራ ለጥበቃ ተጠቃሚ ተፈጻሚ የሚደረጉ ሲሆን ይህም ፡-
- የአካልና ንብረት ደኅንነት ጥበቃ
- የመኖሪያ ስፍራ መቀየርን ጨምሮ ደህንነቱ የተጠበቀ የመኖሪያ ቦታ መስጠት
- ማንነትንና ባለንብረትነትን መደበቅ
- ማንነትን መቀየር
- ለራስ መጠበቂያ የነፍስ ወከፍ መሳሪያ መስጠት
- መረጃ በተሰጠበት የወንጀል ድርጊት ያለመከሰስ
- መረጃ በሚሰጥበት የወንጀል ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊትም ሆነ በኋላ ተከሳሽ በጥበቃ ተጠቃሚው መኖሪያ ወይም የሥራ ቦታ ወይም ትምህርት ቤት አካባቢ እንዳይደርስ ማገድ
- የፍርድ ሂደት ተጀምሮ ምስክርነት እስከሚሰጥ ድረስ የምስክር ማንነት እንዳይገለጽ ማድረግ
- ምስክርነት በዝግ ችሎት እንዲሰጥ ማድረግ
- ምስክርነት በአካል ሳይታይ ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆኖ ወይም ማንነትን በመሸፈን እንዲሰጥ ማድረግ
- ማስረጃ በኤሌክትሮኒክስ ወይም በሌላ የተለየ ዘዴ እንዲቀርብ ማድረግ
- በሚስጥር መያዝ ያለበት ካልሆነ በስተቀር ለጠቋሚ ጥቆማ ባቀረበበት ጉዳይ ላይ ወቅታዊ መረጃና ምክር መስጠት
- እንዲመሰክር ለተጠራ ምስክር የጉዞና የውሎ አበል መስጠት
- የጥበቃ እርምጃው የመኖሪያ ስፍራን ለውጥ ካስከተለ የጓዝ ማንሻ ወጪን መሸፈን
- በበቀል የተወሰደ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲታገድ ወይም እንዲሻር ማድረግ ወይም
ተመጣጣኝ የሆነ የማካካሻ እርምጃ መውሰድ
- በበቀል እርምጃ ለደረሰ ጉዳት የህክምና አገልግሎት በመንግሥት ሆስፒታል በነጻ መስጠት
- በጥበቃ እርምጃው ምክንያት ለደረሰ የገቢ ማጣት ወይም በበቀል እርምጃ ለደረሰ የመሥራት ችሎታ ማጣት የመሠረታዊ ፍላጎት ማሟያ ወጪን መሸፈን
- በጥበቃ ሥር እያለ ለደረሰ ሞት የቀብር ማስፈጸሚያ ወጪ መሸፈንና ለቤተሰብ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ
- የጥበቃ ተጠቃሚው የሥራና የትምህርት ዕድል እንዲያገኝ መርዳት
- ለምስክሩ ወይም ለጠቋሚው የምክር አገልግሎት መስጠት ወይም እንዲያገኝ ማድረግን እንደሚያካትት በአዋጁ ላይ ተዘርዝሮ ይገኛል፡፡
የጥበቃ ስምምነት
በአዋጁ አንቀጽ 2(2) መሠረት የጥበቃ ተጠቃሚ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር የጥበቃ ስምምነት የተፈራረመ ምስክር፣ ጠቋሚ ወይም የምስክር ወይም የጠቋሚ ቤተሰብ አባል ሲሆን በአዋጁ አንቀጽ 8 መሠረት የአካልና ንብረት ደኅንነት ጥበቃ፣ የመኖሪያ ስፍራ መቀየርን ጨምሮ ደህንነቱ የተጠበቀ የመኖሪያ ቦታ መስጠት፣ ማንነትንና ባለንብረትነትን መደበቅ እና ማንነትን መቀየር ከተመለከቱት የጥበቃ ዓይነቶች አንዱን ወይም ከአንድ በላይ ተግባራዊ ለማድረግ በሚኒስቴሩ እና በጥበቃ ተጠቃሚው መካከል የጥበቃ ስምምነት መፈረም አለበት፡፡ የጥበቃ ተጠቃሚው አካለ መጠን ያላደረሰ ወይም በፍርድ የተከለከለ ሰው ከሆነ የጥበቃ ስምምነቱ ከወላጆቹ ወይም ከአሳዳሪው ጋር የሚፈረም ሲሆን ጥበቃው የጥበቃ ተጠቃሚው አካለ መጠን ከደረሰ ወይም የሕግ ችሎታውን መልሶ ካገኘ በኋላ የሚቀጥል ከሆነ ስምምነቱን የጥበቃ ተጠቃሚው ራሱ መፈረም እንዳለበት በህጉ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
የጥበቃ ተጠቃሚ የሆነው አካለ መጠን ያላደረሰ ልጅ መረጃ ወይም ምስክርነት የሚሰጠው በወላጁ ወይም በአሳዳሪው ላይ ሲሆን፣ ወላጅ ወይም አሳዳሪ የሌለው ሲሆን፣ አስፈላጊው ጥረት ተደርጎ ወላጁን ወይም አሳዳሪውን ማግኘት ያልተቻለ እንደሆነ፣ ወላጁ ወይም አሳዳሪው በቂ ባልሆነ ምክንያት ፈቃዱን ሳይሰጥ ሲቀር ወይም በማናቸውም ምክንያት ፈቃዱን መስጠት ሳይችል ሲቀር ሚኒስቴሩ በአንቀጽ 9 መሠረት ከልጁ ጋር ልዩ የጥበቃ ስምምነት ሊፈራረም ይችላል፡፡ ነገር ግን አካለ መጠን ካላደረሰ ልጅ ጋር የተደረገ ልዩ የጥበቃ ስምምነት ከተፈረመበት ዕለት ጀምሮ ባሉት አስር ቀናት ውስጥ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ መፅደቅ አለበት፡፡ ፍርድ ቤቱም አካለ መጠን ያላደረሰው ልጅ ጥቅምና ደኅንነት ይበልጥ ሊረጋገጥ የሚችልበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የጥበቃ ስምምነቱን መሻር፣ ማፅደቅ ወይም ማሻሻል ይችላል፡፡
በጠቋሚዎችና በምስክሮች ላይ ወንጀል መፈፀም የሚያስከትለው ተጠያቂነት
ምስክሮች እና ወንጀል ጠቋሚዎች ከላይ የተጠቀሱ ጥበቃዎች የሚደረግላቸው ከመሆኑም በተጨማሪ ምስክሮች በመሆናቸው ወይም ወንጀል በመጠቆማቸው ጉዳት የሚያደርስባቸው ማንኛውም ሰው በወንጀል ይጠየቃል፡፡ በ1996 በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 444 መሠረት ማንኛውም ሰው ወንጀልን በሚመለከት ለፍትሕ አካለት ጥቋማ ወይም መረጃ የሰጠ ሰው ላይ ወይም በምስክርነት በቀረበ ሰው ላይ ማናቸውንም ጥቃት፣ ተፅኖ ወይም ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ በቀላል እስራት ወይም በመቀጮ የሚቀጣ ከመሆኑም በላይ የተፈፀመው ድርጊት በምስክሩ ላይ ከባድ የአካል ወይም የጤና ጉዳት ወይም ሞት አስከትሎ ከሆነ ላስከተለው ጉዳት አግባብ ባለው የወንጀል ድንጋጌ ተጠያቂ ይሆናል፡፡
ማጠቃለያ
ወንጀል ጠቋሚዎች እና ምስክሮች ለፍትሕ ተባባሪ በመሆናቸው ጥቃት እንዳይደርስባቸው ጥበቃ ማድረግ ህብረተሰቡ ወንጀልን መካላከል ሂደት ያለስጋት ተሳታፊ እንዲሆን የሚያደርግ በመሆኑ ለህጉ ለተግባራዊነት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ