የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

በአንድ አገር ውስጥ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን እና የወንጀል ድርጊትን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የህብርተሰቡ ሚና ከፍተኛ ነው:: ህብረተሰቡ ፍትሕ እንዲሰፍን እና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም ወንጀልን በመከላከል ረግድ ከሚያበረክታቸው አስተዋጾ ውስጥ የወንጀል ድርጊት ሲፈጸም ጥቆማ ከመስጠት ጀምሮ ምስክር መሆን ይጨምራል፡፡ ነገር ግን ጥቆማ እና ምስክርነት በሚሰጡበት ጊዜ እና ከሰጡም በኋላ በእነርሱ እና በቤተሰቦቻቸው ላይ ሊደርስ ከሚችል ስጋት እና አደጋ መጠበቅ አለባቸው፡፡ የተለያዩ የአለማችን ሀገራት የምስክሮች ጥበቃ ሕግን በማውጣት በስራ ላይ ያዋሉ ሲሆን ህጎቹ በአብዛኛው ጥበቃ የሚያደርጉት ለከባድ እና የተደራጁ ወንጀሎች ነው፡፡ ሀገራችንም ይህንኑ በመረዳት የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አውጥታ ለወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃን በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህም ጽሁፍ የምስክሮች ጥበቃ ሕግ በዓለም ዓቀፍ ተሞክሮን፣ የአገራችን ህጎችን እና በአዋጁ ላይ የተገለጽውን የምስክር እና ጠቋሚዎች ምንነት፤ የህጉ ሽፋን፤ የጥበቃ ስምምነት እና የጥበቃ እርምጃ ዓይነቶችን በአጭሩ ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡

የምስክሮች ጥበቃ ሕግ በዓለም ዓቀፍ ተሞክሮ

ለወንጀል ጠቋሚዎች እና ለምስክሮች ጥበቃ በመስጠት ረገድ አሜሪካ በቀዳሚነት የምትነሳ አገር ስትሆን ይህም በ1970ዎቹ የእጽ አዘዋዋሪዎችን እና የማፍያ ቡድኖች ለማፈራረስ ጥቅም ላይ በማዋል ነው፡፡ በዚህ ወቅት የተደራጁ ወንጀሎች መቆጣጠሪያ አክት የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በምስክሮች ደኅንነት ፕሮግራም ስር በተደራጁ ወንጀሎች እና በሌሎች ከባድ ወንጀሎች ላይ ምስክርነት ለመስጠት ፍቃደኛ የሆኑ እና ደህንነታቸው በአደጋ ስጋት ስር የሆኑ ምስክሮች የመኖሪያ ቦታቸውን ወደ ማይገለጥ አዲስ አካባቢ እንዲቀይሩ እና ማንነታቸውንም እንዲቀይሩ የሚያስችል ነበረ፡፡

ሌላው የተባበሩት መንግስታት የወንጀል እና በሥልጣን አለግባብ መጠቀም ተጎጂዎችን መሠረታዊ መብት ለማስጠበቅ በ1985 የወጣ መግለጫ እና እ.አ.አ በ2000 ዓ/ም በተባበሩት መንግስታት የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል የተደረገ ስምምነት ላይ አገራት የወንጀል ጠቋሚዎች እና ምስክሮች እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደረስውን ጥቃት እና የአደጋ ስጋት እንዲከላከሉ እና አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ ይደነግጋል፡፡

በ1983 የአውስትራሊያ ሮያል ኮሚሽን በተለይ የተደራጁ ወንጀሎች ላይ መረጃ ሰጭዎችን በተሻለ ሁኔታ መጠቀምን ትኩረት በማድረግ እና ዝቅተኛ ተሳትፎ ያላቸው በዋና ወንጀል አደራጆች ላይ መረጃ እንዲሰጡ በማድረግ እስከ የመኖሪያ አካባቢ እና ማንነት መቀየር የሚደርሱ ህጎችን በማውጣት በስራ ላይ አውላለች፡፡ በጀርመን የምስክሮች ጥበቃ ለመጀመሪያ ጊዜ ስራ ላይ የዋለው በሀምቡርግ ከሞተር ሳይክል ወንበዴዎች ወንጀል ጋር በተያያዘ በ1980ዎቹ ነው፡፡ በ1998 የምስክሮች ጥበቃ አክት (Witness Protection Act) ያወጣች ሲሆን በማንኛውም የፍትሕ ሂደት የምስክሮች ግላዊ መረጃዎች በሚስጥር መያዛቸውን ማረጋገጥ፣ ለወንጀል ተጎጂዎች እና ምስክሮች የሕግ ድጋፍ መስጠት ላይ ኩረት ያደረገ ነው፡፡

በአብዛኛው እነኝህ የአለም ሀገራት ለተደራጁ ወንጀሎች ምስክሮች በፍርድ ቤቶች በስራ ላይ የሚውሉ ስነ ስርዓታዊ የጥበቃ እርምጃዎች ምስክሮች ለህይወታቸው ከሚያሰጉ ሁኔታዎች ውጪ ሆነው ያለስጋት በነጻነት እንዲመሰክሩ የሚያስችሉ ዘዴዎችን የሚጠቀሙ ሲሆን ምስክርነት ከስክሪን ወይም ከመጋረጃ ጀርባ እንዲሰጥ ማድረግ አንዱ ዘዴ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

የምስክሮች ጥበቃ ሕግ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012፤ በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1178/2012፤ የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 434/1997፤ በ2003 የወጣው የኢ.ፌ.ድ.ሪ የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ እና የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 ለምስክሮች እና ለወንጀል ጠቋሚዎች ስለሚደረግ ጥበቃ ደንግገው ይገኛሉ፡፡

የምስክር እና ጠቋሚዎች ጥበቃ

የምስክር እና ጠቋሚዎች ጥበቃ ከፍተኛ የሰለጠነ የሰው ኃይል፤ ጊዜ፤ ገንዘብ እና ወጪን የሚጠይቁ በመሆኑ ከአገራችን እድገት እና የኢኮኖሚ አቅም አኳያ ለሁሉም ምስክሮች እና የወንጀል ጠቋሚዎች ከለላ እና ጥበቃ ማድረግ አይቻልም፡፡ የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ 3 መሠረት የጥበቃ እና የጥንቃቄ እርምጃዎች ማግኘት የሚቻለው፡- በሕግ የተደነገገው የፅኑ እስራት መነሻ ከግምት ሳይገባ አስር ዓመትና ከዚያ በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ወይም በሞት ሊያስቀጣ በሚችል የወንጀል ድርጊት ተጠርጣሪ ላይ የሚሰጥ ምስክርነትን ወይም ጥቆማን ወይም የሚካሄድ ምርመራን በሚመለከት ሆኖ:-

  1. የወንጀል ድርጊቱ ያለምስክሩ ወይም ያለጠቋሚው ምስክርነት ወይም ጥቆማ በሌላ ማናቸውም መንገድ ሊረጋገጥ ወይም ሊደረስበት የማይችል ሲሆን እና
  2. በምስክሩ፣ በጠቋሚው ወይም በምስክሩ ወይም በጠቋሚው ቤተሰብ ህይወት፣ አካላዊ ደኅንነት፣ ነጻነት ወይም ንብረት ላይ ከባድ አደጋ ይደርሳል ተብሎ ሲታመን ነው፡፡

በማለት በህጉ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ነገር ግን አዋጁ ይንን መስፈርት ቢያስቀምጥም የፍትሕ ሚኒስቴሩ የጥበቃ ተጠቃሚ ላልሆኑ ምስክሮችና ጠቋሚዎችም በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4 ስር የተቀመጡ አንዳንድ ጥበቃዎችን ለማንኛውም ምስክር እና ጠቋሚዎች እንደአስፈላጊነቱ እንደሚያደርግ ይገልጻል፡፡ ይህም የጥበቃ እርምጃዎች፡-

  1. በሚስጥር መያዝ ያለበት ካልሆነ በስተቀር ለጠቋሚ ጥቆማ ባቀረበበት ጉዳይ ላይ ወቅታዊ መረጃና ምክር መስጠት
  2. እንዲመሰክር ለተጠራ ምስክር የጉዞና የውሎ አበል መስጠት
  3. በበቀል የተወሰደ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲታገድ ወይም እንዲሻር ማድረግ ወይም ተመጣጣኝ የሆነ የማካካሻ እርምጃ መውሰድ
  4. በበቀል እርምጃ ለደረሰ ጉዳት የህክምና አገልግሎት በመንግሥት ሆስፒታል በነጻ መስጠት
  5. ለምስክሩ ወይም ለጠቋሚው የምክር አገልግሎት መስጠት ወይም እንዲያገኝ ማድረግን ያካትታል በማለት በአዋጁ ላይ ተዘርዝሮ ይገኛል፡፡

የጥበቃ ስምምነት

አዋጁ የጥበቃ ተጠቃሚ ከፍትሕ ሚኒስቴሩ ጋር የጥበቃ ስምምነት የተፈራረመ ምስክር፣ ጠቋሚ ወይም የምስክር ወይም የጠቋሚ ቤተሰብ አባል ነው በማለት ይገልጻል፡፡ በመሆኑም በአዋጁ ላይ የተዘረዘሩትን አንዳንድ ጥበቃዎች ለማግኘት ከሚኒስቴሩ ጋር ስምምነት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 8 መሠረት የአካልና ንብረት ደኅንነት ጥበቃ፤ የመኖሪያ ስፍራ መቀየርን ጨምሮ ደህንነቱ የተጠበቀ የመኖሪያ ቦታ መስጠት፤ ማንነትንና ባለንብረትነትን መደበቅ እና ማንነትን መቀየር የተመለከቱት የጥበቃ ዓይነቶች አንዱን ወይም ከአንድ በላይ ለማግኘት ከሚንስቴሩ ጋር የጥበቃ ስምምነት መፈራረም እንዳለበት በህጉ ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ የጥበቃ ተጠቃሚው አካለ መጠን ያላደረሰ ወይም በፍርድ የተከለከለ ሰው ከሆነ የጥበቃ ስምምነቱ ከወላጆቹ ወይም ከአሳዳሪው ጋር የሚፈራረሙ ሲሆን ነገር ግን የጥበቃ ተጠቃሚው አካለ መጠን ከደረሰ ወይም የሕግ ችሎታውን መልሶ ካገኘ በኋላ የሚቀጥል ከሆነ ስምምነቱን የጥበቃ ተጠቃሚው ራሱ መፈረም እንዳለበት በህጉ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

የጥበቃ ተጠቃሚ የሆነው አካለ መጠን ያላደረሰ ልጅ መረጃ ወይም ምስክርነት የሚሰጠው በወላጁ ወይም በአሳዳሪው ላይ ሲሆን፤ ወላጅ ወይም አሳዳሪ የሌለው ሲሆን፤ አስፈላጊው ጥረት ተደርጎ ወላጁን ወይም አሳዳሪውን ማግኘት ያልተቻለ እንደሆነ፤ ወላጁ ወይም አሳዳሪው በቂ ባልሆነ ምክንያት ፈቃዱን ሳይሰጥ ሲቀር ወይም በማናቸውም ምክንያት ፈቃዱን መስጠት ሳይችል ሲቀር ሚኒስቴሩ ከልጁ ጋር ልዩ የጥበቃ ስምምነት ሊፈራረም ይችላል ነገር ግን አካለ መጠን ካላደረሰ ልጅ ጋር የተደረገ ልዩ የጥበቃ ስምምነት ከተፈረመበት ዕለት ጀምሮ ባሉት አስር ቀናት ውስጥ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ መጽደቅ አለበት፡፡ ፍርድ ቤቱም አካለ መጠን ያላደረሰው ልጅ ጥቅምና ደኅንነት ይበልጥ ሊረጋገጥ የሚችልበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የጥበቃ ስምምነቱን መሻር፣ ማጽደቅ ወይም ማሻሻል እንደ ሚችል በአዋጁ አንቀጽ 9 ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡

የጥበቃ እርምጃ ዓይነቶች

ለወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች የሚደረጉ የጥበቃ እና የጥንቃቄ እርምጃዎች በአዋጁ አንቀጽ 4 ስር ተዘርዝረው ይገኛሉ፡፡ የጥበቃ እና የጥንቃቄ እርምጃዎች እንደ ሁኔታው በተናጠል ወይም በጣምራ ለጥበቃ ተጠቃሚ ተፈጻሚ የሚደረጉ ሲሆን ይህም ፡-

  1. የአካልና ንብረት ደኅንነት ጥበቃ
  2. የመኖሪያ ስፍራ መቀየርን ጨምሮ ደህንነቱ የተጠበቀ የመኖሪያ ቦታ መስጠት
  3. ማንነትንና ባለንብረትነትን መደበቅ
  4. ማንነትን መቀየር
  5. ለራስ መጠበቂያ የነፍስ ወከፍ መሳሪያ መስጠት
  6. መረጃ በተሰጠበት የወንጀል ድርጊት ያለመከሰስ
  7. መረጃ በሚሰጥበት የወንጀል ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊትም ሆነ በኋላ ተከሳሽ በጥበቃ ተጠቃሚው መኖሪያ ወይም የሥራ ቦታ ወይም ትምህርት ቤት አካባቢ እንዳይደርስ ማገድ
  8. የፍርድ ሂደት ተጀምሮ ምስክርነት እስከሚሰጥ ድረስ የምስክር ማንነት እንዳይገለጽ ማድረግ
  9. ምስክርነት በዝግ ችሎት እንዲሰጥ ማድረግ
  10. ምስክርነት በአካል ሳይታይ ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆኖ ወይም ማንነትን በመሸፈን እንዲሰጥ ማድረግ
  11. ማስረጃ በኤሌክትሮኒክስ ወይም በሌላ የተለየ ዘዴ እንዲቀርብ ማድረግ
  12. በሚስጥር መያዝ ያለበት ካልሆነ በስተቀር ለጠቋሚ ጥቆማ ባቀረበበት ጉዳይ ላይ ወቅታዊ መረጃና ምክር መስጠት
  13. እንዲመሰክር ለተጠራ ምስክር የጉዞና የውሎ አበል መስጠት
  14. የጥበቃ እርምጃው የመኖሪያ ስፍራን ለውጥ ካስከተለ የጓዝ ማንሻ ወጪን መሸፈን
  15. በበቀል የተወሰደ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲታገድ ወይም እንዲሻር ማድረግ ወይም ተመጣጣኝ የሆነ የማካካሻ እርምጃ መውሰድ
  16. በበቀል እርምጃ ለደረሰ ጉዳት የህክምና አገልግሎት በመንግሥት ሆስፒታል በነጻ መስጠት
  17. በጥበቃ እርምጃው ምክንያት ለደረሰ የገቢ ማጣት ወይም በበቀል እርምጃ ለደረሰ የመሥራት ችሎታ ማጣት የመሠረታዊ ፍላጎት ማሟያ ወጪን መሸፈን
  18. በጥበቃ ሥር እያለ ለደረሰ ሞት የቀብር ማስፈጸሚያ ወጪ መሸፈንና ለቤተሰብ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ
  19. የጥበቃ ተጠቃሚው የሥራና የትምህርት ዕድል እንዲያገኝ መርዳት
  20. ለምስክሩ ወይም ለጠቋሚው የምክር አገልግሎት መስጠት ወይም እንዲያገኝ ማድረግ፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ፍትሕን ለማግኘት፤ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የህብረተሰቡ ተሳትፎ ዋሳኝ በመሆኑ እንዲሁም የወንጀል ጠቆሚዎች እና ምስክሮች ወንጀልን በማጋለጣቸው እና ለፍትሕ ትብብር በማድረጋቸው ምክንያት ጉዳት እንዳይደርስባቸው የሚመለከታቸው የመንግሥት አካልት ለወንጀል ጠቆሚዎች እና ምስክሮች ተገቢውን የሕግ ጥበቃ እና ድጋፍ በተቀናጀ መልኩ ማድርግ አለባችው::

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርት እና ሥልጠና የተዘጋጀ