መግቢያ
የፍትሕ ሥርዓቱን በማጎልበት ረገድ ሁሉም የመንግሥት አካላት እና ህብረተሰቡ የሚጫወቱት ሚና የማይናቅ ቢሆንም በዋነኛነት ግን ፍርድ ቤት፣ ዐቃቤ ሕግ እና ፖሊስ በዚህ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግሥት በግልፅ እንደተደነገገው የዳኝነት ተግባር ለፍርድ ቤቶች የተሰጠ ሥልጣን ሲሆን የአስፈፃሚ አካል የሆኑት የፍትሕ ሚኒስቴር እና ፖሊስ ሥልጣንና ተግባር የሚመነጨው ህገ መንግስቱን መሠረት አድርገው ከወጡ የአስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን ከተደነገጉ አዋጆችና ተቋማቱን ለማቋቋም ከወጡ የማቋቋሚያ አዋጆች ነው፡፡ በዚህም እያንዳንዳቸው የየራሳቸው የሆነ ሥልጣንና ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ሆኖም ብዙውን ጊዜ በተለይም ከወንጀል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከምርመራ እስከ ፍርድ ባለው ሂደት ውስጥ የሶስቱን ተቋማት ማለትም የፖሊስ፣ ፍትሕ ሚኒስቴርና ፍርድ ቤቶችን ሚና ካለመለየት የተነሳ የወንጀል ተጎጂዎችም ሆኑ ሌሎች ባለጉዳዮች ጉዳያቸውን ለማን ማቅረብ እንዳለባቸው አለማወቅ እና ከምርመራ እስከ ፍርድ ባለው ሂደት የሶስቱንም ተቋማት ሚና ቀላቅሎ የመረዳት ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ከዚህ በመነሳትም ይህ ጽሑፍ ፍትሕ ሚኒስቴር በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የተሰጡትን ዋና ዋና ሥልጣንና ተግባራት በአጭሩ ይዳስሳል፡፡
የፍህ ሚኒስቴር ሥልጣንና ተግባራት የሕግ ማዕቀፍ
በሌሎች ሕግጋት ለሚኒስቴሩ የተሰጡ ሀላፊነቶች እንደተጠበቁ ሆነው የፍትሕ ሚኒስቴር ሥልጣንና ተግባራት በዋናነት የፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመደንገግ ከወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 40 እና በዚሁ አዋጅ የስም ለውጥ ተደርጎበት የፍትሕ ሚኒስቴር ከሆነው የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 ይመነጫል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6(2) መሠረት ፍትሕ ሚኒስቴር በሕግ ጉዳዮች የፌዴራል መንግሥት ዋና አማካሪና ተወካይ ሆኖ የመሥራት ሥልጣን ያለው ከመሆኑ በተጨማሪ በወንጀልና ፍትሐብሔር ጉዳዮች፣ በሰብዓዊ መብት፣ በሕግ ማርቀቅና ማስረፅ እንዲሁም በተለያዩ ሕግ ነክ ጉዳዮች ዝርዝር ሥልጣንና ተግባራት ተሰጥተውታል፡፡ ዋና ዋናዎቹን እንደሚከተለው እንመለከታቸዋለን፡፡
የወንጀል ጉዳዮችን በተመለከተ የፍትሕ ሚኒስቴር ሥልጣንና ተግባራት
የወንጀል ሕግ በዋነኛነት የሀገርንና የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ የሚወጣ ሆኖ እንደ ወንጀል የሚቆጠሩ ድርጊቶችን የያዘ እና ድርጊቶቹ ተፈፅመው በተገኙ ጊዜም የሚያስከትሉትን ቅጣቶች የሚደነግግ ሕግ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የፍትሕ ሚኒስቴር የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ የሚፈልገውን ዓላማ እና ግብ ለማሳካት የሚያስችሉ የተለያዩ ሥልጣንና ተግባራት ተሰጥተውታል፡፡ ይህም
- በሌሎች ህጎች ለፖሊስ የተሰጠው ሥልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ በፌዴራል ፍርድ ቤት ሥልጣን ስር የሚወድቅ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር የማድረግ፣ የተጀመረ የወንጀል ምርመራ ላይ የክትትል ሪፖርት እንዲቀርብ የማድረግ
- በምርመራ ሂደት ላይ ለመርማሪ ፖሊስ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል የማድረግ
- የወንጀል ምርመራዎች በሕግ መሠረት መከናወናቸውን የማረጋገጥ፣ አስፈላጊውን ትእዛዝ የመስጠት
- የተጠናቀቁ የምርመራ መዝገቦችን ከሕግና ከማስረጃ አንፃር መርምሮ ያስከስሳል ወይም አያስከስስም ውሳኔ የመስጠት
- የጥፋተኝነት ድርድር የመወሰን፣ ድርድር የማድረግ፣ አማራጭ የመፍትሄ እርምጃ እንዲወሰድ የመወሰን እና ተግባራዊነቱን የመከታተል
- የፌዴራል መንግሥትን በመወከል የወንጀል ጉዳዮች ክስ የመመስረት፣ የመከራከር፣ ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ክስ የማንሳት፣ የተነሳ ክስ እንዲቀጥል የማድረግ
- ፍርድ ቤቶች በወንጀል ጉዳይ የሚሰጡዋቸው ውሳኔዎችና ትእዛዞች የመፈፀምና መከበራቸውን የመከታተል፣ ካልተፈፀሙ ወይም አፈፃፀማቸው ሕግን ያልተከተለ ከሆነ ለፍርድ ቤት በማመልከት የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ የማድረግ
- በፍርድ ቤት የሚወሰኑ የወንጀል ቅጣቶች በአግባቡ እንዲፈፀሙ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥርዓቶችን የማደራጀት ወይም መደራጀታቸውን የማረጋገጥ
- በፍርድ ቤት የተሰጡ የሞት ቅጣት ውሳኔዎችን ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት የማቅረብ እና አፈፃፀሙን የመከታተል ሀፊነቶችን የሚያካትት መሆኑን ከአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6(3) መመልከት ይቻላል፡፡
የሰብዓዊ መብትን በተመለከተ የፍትሕ ሚኒስቴር ሥልጣንና ተግባራት
በአዋጁ አንቀጽ 6/8/ መሠረት የሰብዓዊ መብቶች ከማክበርና ከማስከበር አንፃር ፍትሕ ሚኒስቴር
- በፖሊስ ጣቢያና በማረሚያ ቤት ቁጥጥር ስር ያሉ ሰዎችን የመጎብኘት፣ አያያዛቸውና ቆየታቸው በሕግ መሠረት መፈፀሙን የማረጋገጥ፣ ህገ ወጥ ተግባር እንዲታረም ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ወይም እንዲወሰድ የማድረግ
- ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸውን ወይም የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች አፈፃፀም የመከታተል፣ ለሚነሱ ጉዳዮች እንደ አግባብነታቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ምላሽ የመስጠት፣ የስምምነቶቹን ብሔራዊ አፈፃፀም ሪፖርት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የማዘጋጀት
- ነፃ የሕግ ድጋፍን አሰጣጥ ስትራቴጂዎችን የመቅረፅ፣ አፈፃፀሙን የመከታተል፣ በመስኩ የሚሰማሩ አካላትን የማስተባበር
- ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሀ ግብርን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የማዘጋጀት፣ አፈፃፀሙን የመከታተል፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚመለከታቸውን አካላት የማስተባበር፣ ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት የማቅረብ
- ነፃ የሕግ ድጋፍ አሰጣጥ ስትራቴጂዎችን የመቅረፅ፣ አፈፃፀሙን የመከታተል እና በመስኩ የሚሰማሩ አካላትን የማስተባበር እንዲሁም
- የሰብዓዊ መብት ትምህርት እና የንቃተ ሕግ ለማዳበር በተለያዩ ዘዴዎች ትምህርት የመስጠት እና በዘርፉ የተሰማሩ የሚመለከታቸው አካላትን የማስተባበር ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡
የፍትሐብሔር ጉዳዮችን በተመለከተ የፍትሕ ሚኒስቴር ሥልጣንና ተግባራት
በአዋጁ አንቀጽ 6(4) መሠረት በፍትሐብሔር ጉዳዮች ረገድ ፍትሕ ሚኒስቴር
- በፌዴራል የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የሕዝብ እና የፌዴራል መንግሥት መብትና ጥቅም ወኪል ሆኖ የመከራከር፣ የማስከበር፣ እንዲከበሩ የማድረግ፣ የመከታል እና የመቆጣጠር
- ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በግዙፍ የመንግሥት ፕሮጀክቶች የውል ዝግጅት እና ድርድር የማድረግ፣ የሕዝብና የፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች ጥቅም ይጎዳል ብሎ ሲያምን በሌሎች ጉዳዮች የውል ዝግጅትና ድርድር የማድረግ ወይም የሚመለከታቸውን አካላት የማማከር
- የፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤትን በመወከል የፍትሐብሔር ክስ የመመስረት፣ በከሰሱበት ወይም በተከሰሱበት የፍትሐብሔር ጉዳዮች ላይ ክርክር የማድረግ፣ በክርክር አመራር ላይ ለመስሪያ ቤቶች አቅጣጫ የመስጠትና በሕግ መሠረት ፍርድን የማስፈፀም
- የፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች እርስ በርሳቸው ያልተግባቡባቸው የፍትሐብሔር ጉዳዮች በፍርድ ቤት ወይም ከፍርድ ቤት ውጭ ባለ አማራጭ የክርክር መፍቻ መንገድ እንዲወሰን ውሳኔ የመስጠት፣ በውሳኔው መሠረት መፈፀሙን የማረጋገጥ
- በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የፍትሐብሔር ክስ ለመመስረት የገንዘብ አቅም የሌላቸውን ዜጎች በተለይም ሴቶችን፣ ሕፃናትን፣ አካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን ወክሎ የመከራከር
- የገንዘብ አቅም የሌላቸው የወንጀል ተጎጂ የሆኑ ተበዳዮች እንዲካሱ፣ መልሰው እንዲቋቋሙ እንዲሁም ከጉዳቱ የተያያዙ የፍትሐብሔር ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ እነሱን በመወከል የፍትሐብሔር ክስ የማቅረብ ወይም የመደራደር
- የኢፌዲሪ መንግሥት በዓለም ዓቀፍ የዳኝነትና ከፊል ዳኝነት አካላት በሚከስበት ወይም በሚከሰስበት ጉዳይ መንግሥትን በመወከል እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ክርክር የማድረግ፣ ድርድር የማካሄድ እና ውሳኔውንም የማስፈፀም ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡
የሕግ ማርቀቅ እና ማጠቃለል ሥራን በተመለከተ የፍትሕ ሚኒስቴር ሥልጣንና ተግባራት
ከሕግ ማርቀቅ አንፃር ሚኒስቴር መ/ቤቱ
- በፌዴራል መንግሥት የሚወጡ ህጎችን የሕግ ረቂቅ ዝግጅት መሥራት፣ የመንግሥት አካላት የሚያዘጋጁት ረቂቅ ሕግ ከህገ መንግስቱና ከፌዴራል ህጎች ጋር የተጣጣመ መሆኑን ማረጋገጥ፣ ለሚመለከታቸው ክፍሎችም አስተያየት ማቅረብ፣ በክልሎች ጥያቄ ሲቀርብለት የሕግ ረቂቆችን በማዘጋጀት መርዳት
- የሕግ ማሻሻያ ጥናቶችን እንዲሁም የኮዲፊኬሽንና የፌዴራል ህጎችን የማሰባሰብና ማጠቃለል ሥራ መሥራት፣ የክልል ህጎችን ማሰባሰብ እንደአስፈላጊነቱም እንዲጠቃለሉ ማድረግ
- ኢትዮጵያ የምትፈርመው ወይም የምትቀበለው ዓለም አቀፍ ስምምነት ህገ መንግስቱን እና የአገሪቱን ሌሎች ሕግጋት ያገናዘበና ከብሔራዊ ጥቅም አንፃር ተቀባይነት ያለው መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት የአዋጁ አንቀጽ 6(5) ተደንግጓል፡፡
- በተጨማሪም በአዋጁ አንቀጽ 6/6/ መሠረት ፍትሕ ሚኒስቴር የፌዴራል መንግስቱ ህጎች ተግባራዊ መደረጋቸውን እና አተገባበራቸውም ወጥነት ያለው መሆኑን የማረጋገጥ እና የፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች ሥራቸውን በሕግ መሠረት ማከናወናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡
የሕግ ጥናትና ሥልጠናን በተመለከተ
በአዋጁ አንቀጽ 6/9/ መሠረት ፍትሕ ሚኒስቴር
- አሰራሩን ውጤታማና ቀልጣፋ ለማድረግ ጥናትና ምርምር የማድረግ
- የወንጀል ፍትሕ መረጃዎችን ለማሰባሰብ፣ ለማደራጀት፣ ለመተንተን እና ለማሰራጨት የሚያስችል ሥርአት የመዘርጋትና የማስፈፀም
- ዐቃያነ ሕግ ስለ ሥራቸው ያላቸውን አመለካከት፣ እውቀትና ክህሎት በተከታታይ እና በየደረጃው ለማሳደግ ሥልጠና የመስጠት ወይም ሥልጠና እና ትምህርት እንዲሰጣቸው የማድረግ ኃላፊነት ያለበት ከመሆኑም በተጨማሪ
- በአዋጁ አንቀጽ 6/7/ መሠረት ለፌደራል መንግሥት ባለሥልጠናት፣ ሹመኞች፣ ተመራጮች፣ ሰራተኞች እና ለግሉ ዘርፍ ተሳታፊዎች እንደአስፈላጊነቱ የሕግ ሥልጠና የመስጠትና እንዲሰጥ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡
ሌሎች ሀላፊነቶች
ሌላው በአዋጁ አንቀጽ 6/11/ መሠረት በፌደራል ፍርድ ቤት ደረጃ የጥብቅና አገልግሎት ለሚሰጡ ጠበቆች በሕግ መሠረት ፈቃድ መስጠት፣ ማደስ፣ ማገድ፣ መሰረዝ፣ ጠበቆችንና የጥብቅና አገልግሎትን ማስተዳደርና መቆጣጠር እንዲሁም በአዋጁ አንቀጽ 6(12) መሠረት በሌሎች ህጎች ለውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰጠው ኃላፊነት እንደተጠበቀ ሆኖ በወንጀልና በፍትሐብሔር ጉዳይ ዓለም ዓቀፍ ግንኙነቶችነና ትብብሮች ማድረግ በአዋጁ ለፍትሕ ሚኒስቴር የተሰጡት ተግባራት ናቸው፡፡
በተጨማሪም ከላይ ከተጠቀሱት ሥልጣንና ተግባራት በተጨማሪ የኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በተለያየ ወቅቶች በወጡ ሌሎች ህጎች ለምሳሌ በንግድ ሕግ፣ በተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ፣ በፌደራል ጥብቅና አገለግሎት ፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር አዋጅ፣ በፌደራል አስተዳደር ሥነ ሥርአት አዋጅ እና መሰል ሌሎች ህጎች የተሰጡት ሥልጣንና ኃላፊነቶች ያሉት መሆኑን ከሕግጋቱ መረዳት ይቻላል፡፡
ማጠቃለያ
ከላይ በዝርዝር እንደተገለፀው ፍትሕ ሚኒስቴር በተለምዶ በብዙሀን ዘንድ ከሚታወቅበት የወንጀል ጉዳዮችን መከታተል በተጨማሪ የመንግሥትን የፍትሐብሔር ጥቅሞች ከማስጠበቅ፣ ከሰብዓዊ መብቶችን ከማክበርና ከማስከበር፣ ህጎችን ከማርቀቅ፣ የህጎችን በማህበረሰቡ ውስጥ እንዲሰርፁ ከማድረግ እና ተፈጻሚነታቸውንም ከመከታተል አንቀፃር ዘርፈ ብዙ ሀላፊነቶች የተጣሉበት ተቋም ነው፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ስለጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ