ዓለም አቀፍ ሕጎችን በመጣስ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት በኢትዮጵያ ሕግ

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

የሰው ልጆች የሰብዓዊነት መርሆች እንዲከበሩ የሚያስችሏቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የደረጉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አንዱ እና ዋናው ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መገለጫ (Universal Declaration of Human Rights) /UDHR/ ነው፡፡ በዚህ ዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ሰው በመሆኑ ብቻ ያገኛቸውን በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነት፣ የነጻነት መብት እና ከኢ- ሰብዓዊ አያያዝ የሚጠበቅ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ይህን ሕግ ማንኛውም የህብረቱ አባል ሀገራት የማክበርና የማስከበር ግዴታ አለባቸው፡፡

በዚህም መሠረት ሀገራችን ኢትዮጵያም ይህን ዓለም አቀፍ ሕግ ለማክበርና ለማስከበር የሚያስችሏትን ድንጋጌዎች በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ ደንግጋ ትገኛለች፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ የምንመለከታቸው የወንጀል ዓይነቶችም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰው ልጆች ላይ እንዳይፈፀሙ የተከለከሉትን ድርጊቶችን ነው፡፡

የዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግ

የዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግ ማለት ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን ለመከልከል እና መንግሥታት ወንጀሎችን እንዲከሱ እና እንዲቀጡ ግዴታ ለመጣል የተነደፈ የዓለም አቀፍ ሕጎች አካል ነው።

የዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ወንጀል የተገለጹ ድርጊቶችን ይከለክላል፤ የሀገራትን ግንኙነት እና የግለሰቦችን ኃላፊነት ይመለከታል፤ የሕግ ጥሰት ከተከሰተ የወንጀል ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው፡፡

መሠረታዊ ወንጀሎች

መሠረታዊ ወንጀሎች ተብለው በወንጀል ሕጉ ላይ ከተደነገጉት መካከል የቡድን (የማኅበረሰብ) እና የግለሰብ መብቶች የሚካትቱ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ የሰውዘር ማጥፋት፣ በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የሚፈፀም ጦርነት፣ እራሳቸውን ለመከላከል በማይችሉ ሰዎች ላይ የሚፈፀም ጦርነት፣ በታሰሩና በተጋዙ ሰዎች ላይ የሚፈፀም ጦርነት፣ በጦርነት ጊዜ የሚደረጉ ዘረፋዎችና የውንብድና ተግባራት፣ ለጠላት ሊደረግ የሚገባውን ተግባር መጣስ፣ ሕገወጥ በሆኑ የጦር መሳሪያዎች መገልገል፣ የጦር ማቆም ውልን ወይም የሰላም ስምምነትን ማፍረስ፣ በቁስለኞች፣ በበሽተኞችና በእስረኞች ላይ መጨከን ወይም የሚገባቸውን ማጓደል እና ፍትሕን መከልከል የሚሉትን የሚመለከት ነው፡፡

እነዚህ የወንጀል ዓይነቶች በአጠቃላይ በተለይም ድንበር ተሻጋሪ በሆኑ አለያም እርስ በርስ በሚደረጉ ጦርነቶች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ የሰው ልጆች ሞት እና መጎሳቆሎችን ለማስቀረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥበቃ የተሰጣቸውን የሰው ልጆች መብቶች እንደከበሩ ለማድርግ ያለሙ ናቸው፡፡ በመሆኑም ሁሉም የዓለም ሀገራት በሚባል ደረጃ የእንዲህ ዓይነት ኢ-ሰብዓዊና ጭካኔ ከተሞላበት ድርጊቶች ለመከላከል በሕጎቻቸው ላይ የእንዲህ ዓይነት ድርጊቶች ክልከላዎችን ማስቀመጣቸው የግድ ሆኗል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵም የዓለም አቀፉ ስምምነት አንድ አባል እንደ መሆኗ መጠን እነዚህን ሰብዓዊ መብቶች መከበር የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን በሀገሪቱ የበላይ ሕግ በሆነው ሕገ- መንግሥት ላይ በአንቀጽ 14 እና ተከታዮቹ ደንግጋለች፡፡

በሕገ- መንግስቱ እውቅና የተሰጣቸው መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች መከበር ለማረጋገጥ ይረዳ ዘንድ በወንጀል ሕጉም ላይ እነዚህን መሠረታዊ መብቶች ከጥሰት ለመጠበቅ የሚረዱ ድንጋጌዎችን በርዕስ ሁለት በምዕራፍ አንድ እና ሁለት ስር ከአንቀጽ 269 ጀምሮ ደንግጋ ትገኛለች፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዳዶቹን እንመለከታለን፡-

ዘርን ማጥፋት

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ በአንቀጽ 269 ላይ እንደሚደነግገው፡-

ማንም ሰው በሰላምም ሆነ በጦርነት ጊዜ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ በጎሳ፣ በዘር፣ በዜግነት፣ በቀለም፣ በሃይማኖት ወይም በፖለቲካ አንድ የሆነን ቡድን በመላ ወይም በከፊል ለማጥፋት በማሰብ የጥፋቱን ድርጊት በማደራጀት፣ ትእዛዝ በመስጠት ወይም ድርጊቱን በመፈፀም፡-

  • በማንኛውም ሁኔታ የማህበረሰቡን አባላት የገደለ፣ አካላዊ ወይም ኅሊናዊ ጤንነት የጎዳ፣ ወይም የአካል ጉዳት ያደረሰ ወይም ያጠፋ እንደሆነ ወይም
  • የማህበረሰቡ አባላት በዘር እንዳይራቡ ወይም በሕይወት እንዳይኖሩ ለማድረግ ማንኛውንም ዘዴ በሥራ ላይ ያዋለ እንደሆነ ወይም
  • የማህበረሰቡን አባላት ወይም ሕፃናት በግዴታ ከሥፍራ ወደ ሥፍራ ያዛወረ ወይም የበተነ ወይም ሊሞቱ ወይም ሊጠፉ የሚችሉበት የኑሮ ሁኔታ እንዲኖሩ ያደረገ እንደሆነ ከአምስት ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስራት ወይም የነገሩ ሁኔታ ከባድ በሆነ ጊዜ በዕድሜ ልክ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል፡፡

የዚህ ዓይነት ወንጀል በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 28 (1) ላይ በግልጽ እንደተደነገገው ምንም ዓይነት የክስ ይርጋ የለውም፡፡ በተጨማሪም በእንዲህ ዓይነት የወንጀል ተግባር ጥፋተኛ ተብሎ የተቀጣ ሰው በሕግ አውጪው የመንግሥት አካልም ይሁን በማንኛውም የመንግሥት አካል ውሳኔዎች በምሕረት ወይም በይቅርታ የማይፈታ መሆኑ ተደንግጓል፡፡

በሰላማዊ ሕዝቦች ላይ የሚፈፀም የጦርነት ወንጀል

ይህ የወንጀል ዓይነት መሠረታዊ ወንጀሎች ከሚባሉት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች አንዱ ነው፡፡ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 270 ላይ እንደተደነገገው ማንም ሰው በጦርነት፣ በጦርነት ግጭት ወይም በጠላት ወረራ ጊዜ የዓለም አቀፍ ሕግ ድንጋጌዎችን እና የዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግጋትን በመጣስ በሰላማዊ ሕዝቦች ላይ ጉዳት ለማድረስ በመደራጀት፣ በማዘዝ ወይም ድርጊቱን በመፈፀም ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ በአንቀጹ ከ ፊደል “ሀ” እስከ “አ” ያሉትን ወንጀሎች ያስፈፀመ ፣ የፈፀመ ሕገ-ወጥ ቅጣትን የወሰነ ያስፈፀመ እንደሆነ ከአምስት ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስራት፣ ወይም ነገሩ ከባድ በሆነ ጊዜ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል፡፡

ለጠላት ሊደረግ የሚገባውን ተግባር መጣስ

ማንም ሰው በጦርነት ጊዜ ዓለም አቀፍ ሕጎችንና የሰብዓዊነት አጠባበቅ ስምምነቶችን ተቃዋሚ በሆነ መንገድ፡-

  • የተማረከውን፣ መሳሪያውን ለምርኮ ያስረከበውን ወይም በማናቸውም ዓይነት ለመከላከል የተነሳውን ወይም የመከላከል ተግባሩን የተወውን ጠላት የገደለ ወይም ያቆሰለ እንደሆነ፣ ወይም
  • የሙት አካል ያጎደለ እንደሆነ፣ ወይም
  • በጦር ሜዳ ላይ በአንድ የጠላት ቁስለኛ፣ በሽተኛ፣ ወይም ሬሳ ላይ ስርቆት የፈፀመ ወይም ኃይልን ተጠቅሞ ገፈፋ የፈፀመ እንደሆነ፣ ወይም ከነዚህ ተግባሮች አንዱን ለመፈፀም በማሰብ ቁስለኛውን፣ በሽተኛውን ወይም ሬሳውን የበረበረ፣ የያዘ ወይም የኃይል ተግባር የፈመበት እንደሆነ፣ ወይም
  • ከእነዚህ ተግባራት አንዱ እንዲፈፀም ያዘዘ እንደሆነ፣

በጽኑ እስራት፣ ወይም ወንጀሉ በጣም ከባድ በሆነ ጊዜ እድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል (አንቀጽ 275) ፡፡

የጦርነት ማቆም ውልን ወይም የሰላም ስምምነትን ማፍረስ

ማንም ሰው የጦርነት ማቆም ውል ወይም የሰላም ስምምነት መፈረሙን በግልጽ እያወቀና ትእዛዝ ከተሰጠው በኋላ ውጊያው እንዲቀጥል ያደረገ ወይም በማናቸውም ሌላ አድራጎት ከውሉ ወይም ከስምምነቱ ግዴታዎች አንዱን አስቦ ያፈረሰ እንደሆነ፣

በቀላል እስራት፣ ወይም ነገሩ ከባድ በሆነ ጊዜ ከ10 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡

በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድርጅቶች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝቶ ተግባራዊ እንዲደረግ ጥረት እየተደረገ ያለው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነት ጥበቃ ከሚደረግላቸው መካከል ሰብዓዊ እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ይገኙበታል፡፡ ከእነዚህ ሰብዓዊ ደርጅቶች መካከል በጦርነት ክስተቶች ምክንያት የተፈጠረው የቀይ መስቀል ድርጅት አንዱና ዋናው ሲሆን የቀይ ጨረቃ ድርጅትም ሌላው ነው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች በተለይም በጦርነትና በተፈጥሯዊ ክስተቶች ለሚደርሱ በሰብዓዊነት ላይ የሚደርሱ ቀውሶችን ለመታደግ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው ድርጅቶች ናቸው፡፡ በተለይም በጦርነት ቀጠናዎች ላይ በመገኘት በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ማናቸውንም ሰዎች ያለአንዳች አድልኦ፣ወገንተኝነትና ነፃ ሆነው እርዳታ የሚሰጡ ተቋሞች ናቸው፡፡ በመሆኑም ሀገራት በእነዚህ ድርጅቶችም ሆነ ሠራተኞቻቸው ተገቢውን የሕግ ጥበቃ እንዲያገኙ የሚያደርጉ ሲሆን የወንጀል ሕጋችንም ይህን ተልዕኮ ግምት ውስጥ ያስገባ ክልከላን አስቀምጧል፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 281 በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድርጅቶች ላይ የሚፈፀም የጠላትነት ድርጊት በሚለው ርዕስ ስር ማንም ሰው በሰላም ጊዜ አስቦ፡-

  • በቀይ መስቀል ወይም በቀይ ጨረቃ ማኅበር ወይም እነዚህን በመሳሰሉ ሌሎች ሰብዓዊ ድርጅቶች ሠራተኞች፣ ወኪሎች ወይም ባልደረቦች ወይም በነዚሁ ድርጅቶች ጥበቃ ሥር በሚገኙ ሰዎች ላይ የፀብ ሥራ ወይም የኃይል ድርጊት የፈፀመ፣ የዛተ ወይም ያዋረደ እንደሆነ፣ ወይም
  • የነዚህን ድርጅቶች ዕቃዎች፣ ግዙፍ ሥራዎች ወይም ማከማቸዎች ያፈረሰ ወይም ጉዳት ያደረሰባቸው እንደሆነ፣

በቀላል እስራት፤ የተፈጸመው ወንጀል ከባድ በሆነ ጊዜ ከ 5 ዓመት ባልበለጠ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ ወንጀሉ የተፈፀመው በጦርነት ጊዜ እንደሆነ ቅጣቱ ከአንድ ዓመት እስከ 5 ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እስራት ይሆናል፡፡

በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድርጅቶች አርማዎችና መለያ ምልክቶች ያለአግባብ የተገለገ እንደሆነ በአንቀጽ 282 መሠረት በቀላል እስራት ወይም ከባድ በሆነ ጊዜ ከ 5 ዓመት ባልበለጠ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ዓለም አቀፍ ሕጎችን በመጣስ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን መፈፀም በብሔራዊ ሕጎች ብቻ ሳይሆን በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሕጎችም ሊያስጠይቅ ስለሚችል ማንኛውም ሰው ይህን አውቆ የወንጀል ደርጊቱን ከመፈፀም ሊቆጠብ ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ