ጉዳይን ያለአግባብ ማጓተት የሚያስከትለው የህግ ተጠያቂነት

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

ጉዳይን ያለ አግባብ ማጓተት በተገልጋዩ ህብረተሰብ እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል ባለ ግንኙነት የሚፈጸም ተገቢነት የሌለው ተግባር ነው፡፡ ተገልጋዩ የህብረተሰብ አባል በሕግ ክርክሮች እና በአስተዳደር አከላት የሚሰጡ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን ለማግኘት ወደተለያዩ መንግስታዊ አና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ፊት ይቀርባል፡፡ በዚሁ ሁኔታ አገልግሎት ፈልጎ የቀረበው ተገልጋይ እንደ ጉዳዩ ባህሪ በሕግ እና አሠራር በተቀመጠ ምክንያታዊ ጊዜ ውስጥ ለጉዳዩ እልባት አግኝቶ መሸኘት አለበት፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ተገልጋዮችን ተገቢ ላልሆነ እንግልት በመዳረግ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን እና ጉልበታቸውን እንዲያባክኑ በማድረግ ለከፋ ምሬት እና ተስፋ መቁረጥ በመዳረግ በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሻክር ይሆናል፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍም ጉዳይን አለአግባብ ማጓተት ምንነት እና የሚያስከትለውን የሕግ ተጠያቂነት በአጭሩ የምንዳስስ ይሆናል፡፡

ጉዳይን ያለአግባብ ማጓተት ምንነት

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ.ህገመንግሥት አንቀጽ 12 ላይ የመንግሥት ስራ በግልጽነት እና ተጠያቂነት በሰፈነበት ሁኔታ መከናወን እንዳለበት ያመለክታል፡፡ ይህ መርህ በሕግ እና አስተዳደራዊ ውሳኔዎች አሰጣጥ ላይ ተፈጻሚነት አለው። የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተቋቋሙበትን ዓላማ ለማሳካት የሚያስችሏቸው የገልግት መስጫ ስታንዳርድን የሚያመለክቱ የተለያዩ መመሪያዎች እና የአሠራር ሥርዓት አላቸው፡። ከነዚህ መካከልም ጉዳዮችን ተቀብለው ውሳኔ የሚሰጡበትን የጊዜ ገደብ የሚያመላክቱ ድንጋጌዎች በአዋጅ በደንብ እና መመሪያዎች የተደነገጉ ናቸው፡፡

ከዚህ ባለፈም በዜጎች ቻርተር፣ በመሠረታዊ የአሠራር ለውጥ(ቢፒአር) እና ሌሎች የለውጥ መሳሪያዎች እንደየ ጉዳዮቹ ባህሪ እና የውስብስብነት ደረጃ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች አንድን ጉዳይ ተቀብለው መርምረው እልባት የሚሰጡበትን የጊዜ ገደብ ያመላክታሉ፡፡ እነዚህን በሕግ የተዘረጉትን የአሠራር ደረጃ ባለመጠበቅ ጉዳይን ያለ በቂ ምክንያት ሳይወስኑ ወይም ሳይፈጽሙ ማቆየት ጉዳይን ያለአግባብ የማጓተት ትግባር ነው፡፡

በፍትሕ አስተዳደር ዘርፍ ያለውን በምናይበት ጊዜ በመርህ ደረጃ የዘገየ ፍትሕ እንደተነፈገ የሚቆጠር ነው፡፡ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 20 (1) መሠረት ማንኛውም የተከሰሰ ሰው ክስ ከቀረበበት በኋላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ የመሰማት መብት እንዳለው ተደንግጎ ይገኛል፡፡

በዚህም ጉዳያቸው ታይቶ የመጨረሻ ፍርድ ያልተሰጣቸውን ተከሳሾች በተገቢው ጊዜ ፍርድ መስጠት የሚገባ ሲሆን ውሳኔ አስከሚያገኙ በእስር የሚቆዩበትን ጊዜ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ፍርድ እንደተሰጠ ተደርጎ ሊታይ አይገባውም፡፡ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ንቀጽ 3 መሠረት ማንኛውም በወንጀል ፍርድ ሂደት ውስጥ ያለ ሰው ከጥፋተኝነት ፍርድ በፊት በተከሰሰበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ሊቆጠር እና ሊታይ አይገባውም፡፡ በወንጀል ጉዳይ የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት የተከሰሱ ሰዎች መብት ብቻ ሳይሆን ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎችም መብት ነው፡፡ በዚህም በህገመንግስቱ አንቀጽ 19(3) መሠረት በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች በአርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት ቀርበው ለመታሰር ያበቃቸውን በቂ ምክንያት የማወቅ መብት አላቸው፡፡ ለመታሰራቸው በቂ ምክንያት የሌለ ከሆነ ፍ/ቤቱ የኣካል ነጻነታቸውን ጠብቆ በነጻነት ሊለቃቸው እንደሚገባ ነገር ግን ልዩ በሆነ ሁኔታ ፍትሕ እንዳይጓደል ምርመራ ለማካሄድ አስፈላጊ የሆነውን ተጨማሪ የእስር ማቆያ ጊዜ በጥብቅ መስፈርት ሊፈቅድ ይችላል፡፡

ከዚህም የምንረዳው በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙም ሆነ የተከሰሱ ሰዎች በህገመንግስቱ በተጠበቀላቸው መብት መሠረት ጉዳያቸው ሳይጓተት ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ ውስጥ ውሳኔ የማግኘት መብት አላቸው፡፡ በፍትሐብሄር ፍትሕ አስተዳደርም ፍርድ ቤቶቻችን የሚቀርቡላቸውን ጉዳዮች እንደ ጉዳዩ ውስብስበነት በተወሰነ ጊዜ ውስጥ አይቶ አከራክሮ ለመወሰን የሚያስችላቸው የፍትሐብሔር ስነሥርዓት ሕግ እና የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 008/2013 ጉዳይን በተወሰነለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ያለማጓተት መወሰን እንደሚገባ አመላካች የአሠራር ስርአቶች ናቸው፡፡

ጉዳይን ያለአግባብ ማጓተት በወንጀል እና በፍትሐብሄር ጉዳይ ብቻ የሚታይ ሳይሆን በማናቸውም አስተዳደራዊ ጉዳዮችም ጭምር ተቀባይነት የሌለው የአሠራር ብልሹነት ነው፡፡ የፌደራል አስተዳደር ስነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 አንቀጽ 33 ላይ “በተገቢው ጊዜ መወሰን” በሚል ርዕስ እንደተደነገገው የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጠዉ ሰዉ የአስተዳደር ውሳኔዉን ሳይዘገይ በተገቢዉ ጊዜ መስጠት እና በጉዳዩ ዙሪያ ያሉ ጥቅሞች በውሳኔው መዘግየት ምክንያት ለጉዳት እንዳይጋለጡ ማድረግ አለበት በማለት በመደንገግ በግልጽ ጉዳይን ያለ አግባብ ማጓተት ህገወጥ እንደሆነ የደነገገ ሲሆን ከውጤት አንጻርም የአስተዳደር ውሳኔው በተገቢው ጊዜ ሳይሰጥ መቅረት የአስተዳደር ውሳኔ ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ እንደተሰጠ ውሳኔ ይቆጠራል በማለት አስቀምጦ ይገኛል፡፡ በአገራችን የሕግ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው ይሄው የአስተዳደር ስነ ሥርዓት አዋጅ የአስተዳደር አካላት የተገልጋዮችን መብት በማክበር ጉዳያቸውን ሳያጓትቱ በተገቢው ፍጥነት መወሰን እንዳለባቸው ያመለክታል፡፡ በዚሁ አግባብ አለመወሰንምጥያቄውን ውድቅ እንደማድረግ ይወሰዳል፡፡ ይህ ማለትም ተገልጋዩ ወደሚከተለው አቤቱታ ሰሚ የበላይ የመንግሥት አካል ቅሬታውን ማቅረብ እና ምላሽ ማግኘት ይችላል ማለት ነው፡፡

ጉዳይን ያለአግባብ ማጓተት የሚያስከትለው የሕግ ተጠያቂነት

ለጉዳይን ያለአግባብ ማጓተት ወንጀል ተጋላጭ የሆኑት የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ ህዝባዊ የሆኑ የግሉ ዘርፍ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትንም የሚያካትት ነው፡፡ ከዚሁ አኳያ በተገልጋዮች ላይ የሚፈጸም ምክንያታዊ ያልሆነ የጉዳይ ማጓታት ተግባር ከአስተዳደራዊ እና የፍሐብሄር ተጠያቂነት ብቻ ሳይሆን በወንጀልም የሚያስጠይቅ ተግባር ነው፡፡ በሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 18 መሠረት ማንኛውም የመንግሥት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ በሃላፊነቱ በስራው ምክንያት በቀረበለት ጉዳይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ጥቅም ለማግኘት ሲል በጉዳዩ ላይ ጥቅም ያለውን ማንኛውንም ሰው ለመጥቀም ወይም ለመጉዳት በማሰብ ከሕግ፣ ከመመሪያ ወይም ከተለመደው አሠራር ውጪ ያለበቂ ምክንያት ጉዳዩን ያልወሰነ፣ ያዘገየ ወይም ባለጉዳይን ያጉላላ ሰው እንደ ጉዳዩ ሁኔታ በመቀጮ ወይም በቀላል እስራት ወይም ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ ሰእስራት እና አመስት ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ ደንግጎ ይገኛል፡፡

እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው በአዋጁ እንደተደነገገው ጉዳይን ማጓተት ወንጀል የሙስና ወንጀል የሆነበትን መሠረታዊ ምክንያት ነው፡፡ በዚሁም መሠረት የሙስና ወንጀሎች በመሠረታዊነት የሚፈጸሙት የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለአንዱ ወገን በተለያዩ ምክንያቶች በማዳላት ሌላውን ወገን ለመጥቀም በማሰብ ነው። የዚህ ወንጀል ፈጻሚዎች ጉዳይን አለአግባብ የማጓተት ተግባር የሚፈጽሙት ባለጉዳዩ በመመላለስ ምክንያት ከሚደርስበት እንግልት ለማምለጥ ሲል ገንዘብ እንዲከፍላቸው ተጽእኖ ለማሳደር አለያም ባለጉዳዩ ተማሮ ጉዳዩን መከታተሉን እንዲተወው በማድረግ የባለጉዳዩን መብት ለመረጡት ሌላኛው ሰው በማስተላለፍ በዚህም የሚከፈላቸውን ተገቢ ያልሆነ የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሌላው ልብ ልንለው የሚገባው አጥፊው ጉዳይን ያለአግባብ ማጓተት ፈጽሟል ለማለት የተላለፈው ግልጽ የሆነ በሕግ፣ በመመሪያ እና በአሠራር ደንብ የተቀመጠ ምክንያታዊ የውሳኔ መስጫ ጊዜን በመተላለፍ ውሳኔውን በሰአቱ ሳይሰጥ የቀረ መሆኑን በማስረዳት ነው፡፡ በዚህም እንደየሙያና አገልግሎት መስኩ ውሳኔ ሊሰጥበት የሚገባው ጉዳይ የሚፈልገውን ምክንያታዊ ጊዜ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡

ማጠቃለያ

የመንግሥት መስሪያ ቤቶችም ሆኑ የህዝባዊ ድርጅቶች ተገልጋዮቻቸውን ሲያስተናግዱ አገልግሎት ወይም ውሳኔ የሚሰጥበት ጉዳይ ያለውን ልዩ ባህሪ ግምት ውስጥ በማስገባት በሕግ እና በአሠራር ሥርዓት እንዲሁም የተለመዱ አካባቢያዊ ሀኔታዎችን በማገናዘብ ለተገልጋዮቻቸው በተገቢው ጊዜ ውሳኔ የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ያለ በቂ ምክንት ሕግ እና አሠራርን በመጣስ ተገልጋዮችን ለማንገላታት እና ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት እንዲሁም አግልግሎት ጠያቂው ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ጉዳይን ያለበቂ ምክንያት ማጓተት በሕግ የሚያስጠይቅ እና የሚያስቀጣ የወንጀል ተግባር መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ ተገልጋዩ ማህበሰረብ በመንገስትም ይሁን ህዝባዊ ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ሲሄድ በሕግ እና አሠራር ሥርዓት የተቀመጡ የአሠራር ደረጃዎችን ተረድቶ በዛ ውስጥ ውሳኔ እንዲያገኝ መጠየቅ እና ይህ በማይሆንበት ጊዜ ጉዳዩን ያለ በቂ ምክንያት የሚያጓትቱ የመንግሥት እና ህዝባዊ ድርጅት ሰራተኞች እና ሀላፊዎች ላይ የሕግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ከፍትሕ አካላት ጋር በመተባበር መሥራት ያስፈልጋል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ