የጦርነት ህግ

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

ዓለማችን ከዚህ ቀደም በሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ ስቃይና መከራን ያደረሱ አሰቃቂ ጦርነቶችን አይታለች፡፡ በዓለም ላይ በጦርነት ምክንያት በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለስደት፣ ለረሃብ፣ ለድህነት፣ ለከፍተኛ የአካል ጉዳት እና ሞት ተዳርገዋል እየተዳረጉም ይገኛሉ፡፡

በመሆኑም ከዚሁ በመነሳት ጦርነቶች በሰው ልጆች ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ፣ የንፁሃን ሕይወት እና ንብረት ለመጠበቅ እንዲሁም የቆሰሉ እና የተማረኩ ወታደሮችን በርህራሄ እና በሰብዓዊነት እንዲያዙ ለማድረግ ሀገራት በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ስምምነቶችን አድርገዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በ1899 እና በ1907 የተደረገው ሀገራት በሚዋጉበት ወቅት አንዳንድ አደገኛ የጦር ስልት እና የጦር መሳሪያዎችን ላለመጠቀም የተስማሙበት የሕግ ስምምነት በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡

ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ የዓለም ሀገራት ያፀደቁት እና የጦርነት ሕግ ተብሎ የሚታወቀው በ1949 የተደነገገው የጄኔቫ ኮንቬንሽን እና እሱን ተከትሎ የወጡት ፕሮቶኮሎች የተካተቱበት ነው፡፡ ይህም ስምምነት በጦርነት ወቅት ለንፁሃን ሰዎች ሊደረግ ሚገባውን ጥበቃ እና እንክብካቤ፣ የቆሰሉ እና የተማረኩ ወታደሮች ሊያዙበት የሚገባ ሁኔታ፣ በጦርነት ወቅት ስለሚያገለግሉ የመጀመሪያ እርዳታ ሰጪ የህክምና ባለሞያዎች እና ጋዜጠኞች ጥበቃ፣ በጦርነት ወቅት ሊጠበቁ ስለሚገባቸው ተቋማት እና መወሰድ ስላለበት ጥንቃቄ በመዘርዘር የሚያስቀምጥ ነው፡፡

ሀገራችንም በ1949 የወጣውን የጄኔቫ ስምምነት ያፀደቀች ሲሆን በ1996 በወጣው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ ላይም በጄኔቫ ስምምነት መሠረት ጥበቃ የሚደረግላቸውን መብቶች እና ጥበቃዎችን እንዲሁም ይህ ሕግ በተጣሰ ጊዜ የሚያስከትለውን ተጠያቂነት በማካተት ደንግጋ ትገኛለች፡፡ ይህም ጽሑፍ ይሄንኑ የሚዳስስ ይሆናል፡፡

ዓለም አቀፍ የጦርነት ህጎች

በ1899 የተደረገው የሕግ ስምምነት

ጦርነትን በተመለከተ በታሪክ ሀገራት የተለያዩ ስምምነቶችን አድርገዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ በ1899 የተደረገው የሕግ ስምምነት ይጠቀሳል፡፡ ይህም ስምምነት ሀገራት በሚዋጉበት ጊዜ መጠቀም ያለባቸውን እና የሌለባቸውን የጦር መሳሪያ አይነት እና የውጊያ ስልቶችን የሚያስቀምጥ ነው፡፡

በ1949 የተደረገው የጄኔቫ የጦር ስምምነት

የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ ጦርነቶች የሚያስከትሉትን ጉዳት በተቻለ መጠን ለመቀነስ እና ሰብዓዊነት የተሞላበት እንዲሆን በማሰብ የጄኔቫ የጦር ስምምነት ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ጊዜ አገራችንን ጨምሮ ሁሉም የዓለም ሀገራት በሚባል ሁኔታ አፅድቀውታል፡፡ የጄኔቫ ስምምነት ጦርነት የሚያደርሰውን ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳቶችን ለመቀነስ፣ ተጋለጭ ለሆኑ ሲቪሎች፣ ለጦር ምርከኞች እና በጦርነት ወቅት ጉዳት ለደረሰባቸው እና መዋጋት ለማይችሉ ወታደሮች ጥበቃን የሚሰጥ ነው፡፡ የጄኔቫ የጦር ስምምነት በውስጡ አራት ስምምነቶችን /ኮንቬንሽኖችን/ የሚያካትት ሲሆን ይህም ፡-

  • 1ኛ ኮንቬንሽን፡-ይህ ስምምነት በጦርነት ወቅት ለቆሰሉ እና በምንም ሁኔታ መዋጋት ለማይችሉ ወታደሮች፣ በጦርነት ቀጠና ውስጥ የመጀመሪያ እርዳታን ፣ የህክምና አገልግሎት ለሚሰጡ እና በጦርነት ውስጥ ተሳትፎ የሌላቸውን ሰዎች ጥበቃ የሚሰጣቸው ነው፡፡ ይህ ስምምነት በዘር፣ በእድሜ፣ በጾታ፣ በቀለም፣ በሀይማኖት፣ በብሔር፣ በአመለካከት እና በመሳሰሉት ሁኔታ በጦርነት ወቅት ለቆሰሉ እና በምንም ሁኔታ መዋጋት ለማይችሉ ወታደሮች መድሎ ሳይደረግ ሰብዓዊ አያያዝ እና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው የሚደነግግ ነው ፡፡ በተጨማሪም በጦርነት ወቅት ለቆሰሉ እና በምንም ሁኔታ መዋጋት የማይችሉ ወታደሮች ላይ የሚፈፀም ድብደባ፣ ክብረ ነክ ጥቃት፣ ካለ ፍርድ የሚፈፀም ግድያን የሚከለከል እና የህክምና እርዳታን የማግኘት መብት እንዳላቸው የሚደነግግ ነው፡፡
  • 2ኛ ኮንቬንሽን፡- ይህ ስምምነት በ1ኛ ኮንቬንሽን ላይ የሚደረገውን ጥበቃ እና መብቶች በጦርነት ወቅት ጉዳት ደርሶባቸው ከጥቅም ውጪ ወይም ከውጊያ ውጪ ለሆኑ፣ በሰጠሙ የጦር መርከቦች ላይ ላሉ ወታደሮች እና ለባህር ሀይሎች ጥበቃ የሚያደርግ ሲሆን በመርከብ ላይ ላሉ ሆስፒታሎችም የተለየ ጥበቃ ይሰጣል፡፡
  • 3ኛ ኮንቬንሽን፡-ይህ ስምምነት በ1ኛ ኮንቬንሽን ላይ የሚደረገውን ጥበቃ በጦርነት ወቅት ለተማረኩ ምርከኞች የሚሰጥ ሲሆን ምርከኞች በተገቢው እና ሰብዓዊነት በተሞላበት ሁኔታ መያዝ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ በዚህ ስምምነት መሠረት የጦር ምርኮኞች ስማቸውን፣ ማዕረጋቸውን እና የመለያ ቁጥራቸውን እንዲሰጡ ከመገደድ በስተቀር ሌላ መረጃ ለመስጠት እንደማይገደዱ እንዲሁም መረጃዎችን እንዲሰጡ በምርከኞች ላይ ድብደባን፣ ማንገላታትን እና ስቃይን መፈፀም የሚከለክል ስምምነት ነው፡፡
  • 4ኛ ኮንቬንሽን፡-ይህ ስምምነት በ1ኛ ኮንቬንሽን ላይ የሚደረገውን ጥበቃ ለሲቪሎች እና በጦርነት ወቅት ለተማረኩ ወታደሮች ሊደረግላቸው እንደሚገባ ያስቀምጣል፡፡ በጦርነት ቀጠና ውስጥ ያሉ ሲቪሎች እንዴት መያዝ እንዳለባቸው እንዲሁም በጦርነት አሸንፎ አንድን ስፍራ የያዘ ኃይል በስፍራው ያሉትን ነዋሪዎች እንዴት መያዝ እንዳለበትም በስምምነቱ ውስጥ አካቶ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ይህ ስምምነት ለሲቪል ተቋማት ጥበቃ የሚያደርግ ሲሆን ሲቪል ተቋማትን ማለትም እንደ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤት፣ የእምነት ተቋማትን እና የመሳሰሉትን ተቋማት ጥበቃ ያደርጋል፡፡

በ1977 የወጡት ተጨማሪ ሁለት ፕሮቶኮሎች በጄኔቫ ስምምነት ላይ የተጠቀሱትን መብቶች እና ግልጽ ያልሆኑ ነገሮችን የሚያብራራ እና ሌሎች ተጨማሪ ጥበቃዎችን እና መብቶችን ያካተተ ስምምነት ነው፡፡ በ2005 የተደረገው ሶስተኛው ተጨማሪ ፕሮቶኮልም በጦርነት ወቅት የሚያገለግሉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና አርማቸው ሊደረግላቸው ስለሚገባ ጥበቃ ይደነግጋል፡፡ በጄኔቫ የጦር ስምምነት ውስጥ ወሳኝ የሆነው እና ለሁሉም ስምምነቶች እና ፕሮቶኮሎች የጋራ የሆነው አንቀጽ ሶስት ሲሆን ይህም አንቀጽ የጄኔቫ ስምምነቶች እና ፕሮቶኮሎች ለዓለም አቀፍ ጦርነቶች፣ ለአገር ውስጥ ጦርነቶች እና የእርስ በእርስ ግጭቶች ላይ ተፈፃሚነት እንዳላቸው የሚያትት ነው፡፡

እነዚህን ስምምነቶች መጣስ የጦር ወንጀል ሲሆን የጦር ወንጀልን ምንነት እና አይነቶችን በመዘርዘር በግልጽ የሚያብራራው 1998 የወጣዉ የዓለም ዓቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ ሕግ (Rome Statute of the International Criminal Court) በአንቀጽ 8 ስር የጦር ወንጀል ማለት በዓለምአቀፍ የጦርነት ሕግ ስምምነት እንዲሁም በዓለምአቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባለው ልማዳዊ ሕግ መሠረት በጦርነት ወቅት የሚደረጉ ጥበቃዎችን፣ መብቶችን እና ክልከላዎችን በመጣስ የሚፈፀሙ ናቸው በማለት ያስቀምጣል፡፡ ልዩ ጥበቃ በሚያስፈልጋቸው ሰዎች ላይ የሚፈፀም የጦር ወንጀል፣ የሰብዓዊ ድጋፍ በሚያደርጉ ሰዎች እና ሰላም በሚያስከብሩ አካላት ላይ የሚፈፀም የጦር ወንጀል፣ በንብረት እና ሌሎች መብቶች ላይ የሚፈፀም የጦር ወንጀል፣ የተከለከሉ የጦርነት ስልቶችን እና የጦር መሳሪያዎችን መጠቀም ከጦር ወንጀሎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የሀገራችን የጦርነት ሕግ

ሀገራችን ኢትዮጵያም የጄኔቫ ኮንቬንሽንን ጨምሮ እሱን ተከትለው የወጡትን ተጨማሪ ፕሮቶኮሎችን ያፀደቀች ሲሆን ይህንኑ መሠረት በማድረግ በ1996 የወጣው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ ላይ የጦርነት ወንጀሎችን እና የሚያስከትሉትን ቅጣቶች በመዘርዘር አስቀምጣ ትገኛለች፡፡

የወንጀል ህጉ ከአንቀጽ 270 እስከ 280 ባለው አንቀፆች ስር በዓለማቀፍ ስምምነቶች እና በጦርነት ህጎች መሠረት ጥበቃ የሚደረግለቸውን መብቶች፣ የተደረጉ ክልከላዎችን እና ክልከላዎችን መጣስ የሚያስከትሉትን ተጠያቂነት እና ቅጣት በመዘርዘር አስቀምጦ ይገኛል፡፡ ከዚህም መካከል፡-

የወንጀል ሕግ አንቀጽ 270 በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የሚፈፀም የጦርነት ወንጀሎችን በመዘርዘር የሚያስቀምጥ ሲሆን ይህም ማንም ሰው በጦርነት፣ በጦርነት ግጭት ወይም በጠላት ወረራ ጊዜ የአለማቀፍ ሕግ ድንጋጌዎችንና የአለማቀፍ የሰብዓዊነት ሕግጋትን በመጣስ በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ጉዳት ለማድረስ በመደራጀት፣ በማዘዝ ወይም ድርጊቱን በመፈፀም ወይም በማንኛቸውም ሌላ መንግድ

  • ሰውን የገደለ፣ ያሰቃየ፣ ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ ያጉላላ፣ ሥነ ህይወታዊ ሙከራ ያደረገ፣ በሰው በአካል፣ በአእምሮ ወይም ጤንነት ላይ ከባድ ስቃይ ወይም ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ሌሎች ድርጊቶችን የፈፀመ ወይም
  • ሕዝብን በሃይል ከስፍራው እንዲፈናቀል ወይም እንዲበተን ያደረገ፣ በተደራጀ እቅድ ከአገር ያስወጣ ወይም ወደ አንድ የግዞት ስፍራ ወይም የግዴታ ሥራ ማከናወኛ ስፍራ በመላክ እንዲታሰር ያደረገ ወይም
  • በጠላት የስለላ አገልግሎት፣ የጦር ኃይል ወይም የአስተዳደር ሥራ ውስጥ መልምሎ እንዲያገለግል ያስገደደ፣ በግዴታ ዜግነቱን እንዲያጣ ወይም ሀይማኖቱን እንዲለወጥ ያደረገ፣ የዝሙት አዳሪነት፣ የብልግና ድርጊት ወይም የግብረ ስጋ ድፍረት ተግባር እንዲፈፅም ያስገደደ፣ የማስፈራራት ወይም የማሸበር ድርጊት ያደረገ፣ በመያዣነት ያገተ ወይም የጅምላ ቅጣት የጣለ ወይም የበቀል ድርጊት ያደረገ፣ በሕግ በተቋቋሙና ለፍርድ ሂደት ዋስትናን ከሚሰጡ መደበኛ ፍርድ ቤቶች ውጪ ቅጣትን የወሰነ እና ያሰፈፀመ እንደሆነ
  • አንደኛው ወገን በተቆጣጠረው ስፍራ ላይ ለሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎች አልባሳትን፣ መኝታን፣ መጠለያን፣ የህክምን መድሃኒቶችን እና መገልገያን ወይም ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ያላቀረበ፣ እንዲቀርብላቸው ያላደረገ እንደሆነ
  • እድሜቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን በጦርነት ወስጥ እንዲሳተፉ ለማድረግ ለወታደራዊ አገልግሎት አባልነት የመለመለ
  • ገንዘብ ዋጋ እንዳያገኝ ዋጋውን ዝቅ አድርጎ በማክሰር፣ ሀሰተኛ ገንዘብ በማተም ወይም በተደራጀ እቅድ ገንዘብን በማውረድ ወይም በማንኛቸውም ሁኔታ አስቦ ሕዝብን ለረሀብ የዳረገ፣ በችግር ላይ የጣለ ወይም በአጠቃላይ የሕዝብን ኑሮ ያናጋ እንደሆነ
  • ንብረትን የወረሰ፣ ያወደመ ወይም ለራሱ ያደረገ፣ህገወጥ ወይም ተገቢ ያልሆነ ግብር ወይም ቀረጥ የጣለ እንደሆነ ወይም ለወታደራዊ አገልግሎት ፍፁም አስፈላጊ ከሆነው በላይ ቀረጥ እና ግብር እንዲከፈል የደረገ እንደሆነ
  • ምግብን፣ ለምግብ ማምረቻ የሚውሉ የእርሻ ቦታዎችን፣ ሰብልን፣ የቤት እንስሳትን፣ የመጠጥ ውሃ አገልግሎቶችን፣ የመስኖ ስራዎችን፣ የጤና ተቋማትን ወይም ትምህርት ቤቶችን የወረሰ፣ ያፈረሰ፣ ያጠፋ፣ ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ ያደረገ ወይም ለራሱ እንዲሆኑ ያደረገ እንደሆነ
  • ታሪካዊ ሀውልቶችን የሥነ ጥበብ ሥራዎችን ወይም የማምለኪያ ቦታዎችን ያወደመ፣ የወሰደ፣ ከጥቅም ውጪ ያደረገ፣ ለእራሱ ያደረገ ወይም በእነዚህ ላይ የኃይል ተግባር ያደረገ ወይም እነዚህን ነገሮች ለወታደራዊ ዓላማ ያዋለ
  • በተፈጥሮ አከባቢ ላይ የተስፋፋ እና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ከባድ ጉዳት ሊያደርስ በሚችል መሳሪያ ወይም ውጊያ ስልት የተጠቀመ፣ በዚሁም ምክንያት የአከባቢውን ነዋሪ ጤና እንዲታወክ ያደረገ እንደሆነ ወይም አደገኛ የሆነ ኃይል እንዲለቀቅ በሚያደርግ እና በዚሁ የተነሳ በሰላማዊ ነዋሪ ላይ ከፍተኛ ጉዳትን ሊያደርስ በሚችል ሁኔታ ግድቦች እና የኒውኩለር ኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ያጠፋ እንደሆነ

ከ 5 ዓመት እስከ 25 ዓመት ሊደርስ በሚችል ፅኑ እስራት ወይም ነገሩ በጣም ከባድ በሆነ ጊዜ በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል በማለት ደንግጎ ይገኛል፡፡

በወንጀል ህጉ አንቅጽ 271 ስር በቁስለኞች፣ በበሽተኞች፣ በባህር ወይም በአየር አደጋ ላይ ባሉ ሰዎች ወይም በጤና አገልግሎት ላይ የሚፈፀሙ የጦርነት ወንጀሎችን በመዘርዘር ያስቀምጣል፡፡ በዚህ ሕግ ላይ ቁስለኛ እና ህመምተኛ ማለት በደረሰበት የመቁሰል አደጋ፣ በበሽታ ወይም በሌላ ጉዳት ወይም አዕምሮው ላይ በደረሰ መረበሽና አለመረጋጋት ምክንያት ህክምና የሚያስፈልገው ከማንኛውም የጠላትነት እናቅስቃሴ ታቅቦ የሚገኝ የመከላከያ ሰራዊት አባል እና ሌሎች ሰላማዊ ሰዎችን እንደሚያጠቃልል በአንቀጽ 271(2)ሀ ላይ ተደንግጎ ገኛል፡፡ ይህም ሕግ ማንም ሰው ፡-

  • በቁስለኞች፣ በህመምተኞች፣ በባህር ወይም በአየር አደጋ ላይ ባሉ በህክምና ወይም በመጀመሪያ እርዳታ ሰራተኞች ላይ የግድያ፣ የማሰቃየት ሁኔታዎችን፣ አስፈላጊ የሆነውን የህክምና እርዳታ መከልከል፣ ርህራሄ በሌለው ሁኔታ ሰውን የመበደል ድርጊት የፈፀመ ወይም ማንኛውም ሌላ የአካል ወይም የሕሊና ስቃይ እንዲ ደርስበት ያደረገ፣ ለጤና ጥበቃ፣ ለእርዳታ መስጫ ክፍል ወይም ለማጓጓዣ የሚያገለግሉ እቃዎችን፣ የመስሪያ ቤት ወይም የግምጃ ቤት ሕግን ተቃራኒ በሆነ መንገድ ወይም ያለአግባብ ወይም ለወታደራዊ አገልግሎት ፍፁም አስፈላጊ ሆኖ ከሚገኘው ውጪ ያፈረሰ፣ ከአገልግሎት ውጪ ያደረገ ወይም የወሰደ እንደሆነ
  • የጤና አገልግሎት ሰራተኞች፣ የሀይማኖት አገልግሎት ሰጪዎችና ጋዜጠኞች የሙያ ሥነምግባር እና መመሪያ ከሚያዘው ውጪ እንዲሰሩ ወይም የሙያ ሥነ ምግባር እና መመሪያ በሚያዘው መሠረት እንዳይሰሩ ወይም ቁስለኞችን፣ በሽተኞችን ወይም ሰላማዊ ሰዎችን ለመጠበቅ የወጡ ሌሎች መመሪያዎችን ወይም ደንቦችን ተላልፈው እንዲሰሩ ያስገደደ እንደሆነ

ከ 5 ዓመት እስከ 25 ዓመት ለሚደርስ በሚችል ፅኑ እስራት ወይም ነገሩ በጣም ከባድ በሆነ ጊዜ በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል በማለት ደንግጎ ይገኛል፡፡

በህጉ አንቀጽ 272 ስር በታሰሩ የጦር ምርከኞች በተጋዙ ሰዎች ላይ ስለሚፈፀም የጦርነት ወንጀል የሚያትት ሲሆን ይህም ማንም ሰው፡-

  • በታሰሩ የጦር ምርከኞች ወይም በተጋዙ ሰዎች ላይ የመግደል የማሰቃየት ተግባር ወይም ከሰብዓዊ ርህርሄ ውጪ የሆነ የማጉላላት በደል እንዲፈፀምባቸው ያደራጀ፣ ያዘዘ ወይም ድርጊቱን የፈፀመ ወይም በዚህ ሁኔታ የሚገኙ ሰዎችን በጠላት ስለላ፣ የወታደራዊ ወይም አስተዳደር ሥራ እንዲያገለግሉ ያደረገ እንደሆነ ከ 5 ዓመት እስከ 25 ዓመት ሊደርስ በሚችል ፅኑ እስራት ወይም ነገሩ በጣም ከባድ በሆነ ጊዜ በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም በሞት እንደሚቀጡ ደንግጎ ይገኛል፡፡

በአጠቃላይ በሰለጠነው ዓለም ጦርነት የራሱ የሆነ ሕግና ሥነ ምግባር አለው፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያን ጨምሮ ሀገራት የተስማሙባቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ያሉ ሲሆን የጦር ሕግጋት በዓለም ዓቀፍም ሆነ በሀገራችን የወንጀል ሕግ ጥበቃ የሚደረግላቸው እና ጥሰቶችም ሲከሰቱ የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትሉ ናቸው፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ