የንብረት ማስመለስ አዋጁ አስፈላጊነት እና ይዞ የመጣዉ አዲስ ነገር

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

ክፍል አንድ

የንብረት ማስመለስ ምንነት

የንብረት ማስመለስ ማለት በህገወጥ ድርጊት ምክንያት የተገኘን/ተመዘበረ ሃብትን/ንብረትን መመርመር፣ መለየት፣ ማገድ፣ መያዝ፣ እንዲሁም መውረስና ማስተዳደርን የሚያካትት የሕግ ሂደት (bundle of legal acts) ነው፡፡

የንብረት ማስመለስ አዋጁ አስፈላጊነት እና ይዞ የመጣዉ አዲስ ነገር

የንብረት ማስመለስ አዋጁ (አዋጅ ቁጥር 1364/2017) አስፈላጊነት እና ይዞ የመጣዉ አዲስ ነገር በተመለከተ ኢትዮጵያ የተመድ እና የማፑቶ ጸረ-ሙስና ስምምነቶችን ፈርማ ያጸደቀች በመሆኗ የተለያዩ የዓለም ዓቀፍ ግዴታዎች ያለባት በመሆኑ እና የንብረት ማስመለስ ሕግጋት፣ ስምምነቶችና ልምዶች ጋር በተጣጣመ መልኩ መዘጋጀት የሚያሰፈልግ በመሆኑ፣ በሀገራችን ኢትዮጵያ ማንኛውም ዓይነት የገንዘብ ወይም የንብረት ጥቅም የሚያስገኝ ወይም ጉዳት እንዲደርስ የሚያደርግ ወንጀል በመፈጸም የተገኘውን ጥቅም ወይም የደረሰውን ጉዳት የሚያካክስ የሀብት ማስመለስ ሥርዓት የሚደነግጉ እዚህም እዛም የተበታተኑ የነበሩ በመሆናቸው፣ የንብረት ማስመለስ ሕግ ላይ ተጠቃልለው የማይገኙ በመሆናቸው በአፈጻጸም እና በሀብት ማስተዳደር ሂደት ላይ የራሳቸው የሆነ ክፍተት ማስከተላቸው እነዚህ የንብረት ማስመለስ ድንጋጌዎች ወደ አንድ የሕግ ማዕቀፍ በማምጣት እና ለሁሉም የወንጀል ዓይነቶች እንዲያገለግሉ በማድረግ ለመሠረታዊ የሕግና የአፈጻጸም ጥያቄዎች ወጥነት ያለውና በቂ መልስ የሚሰጥ ሕግ እንዲኖር ማድረግ ዓላማ በማድረግ የወጣ ነው፡፡

የንብረት ማስመለስ ሕግ ዓላማ

የንብረት ማስመለስ ሕግ በዋናነት አለማዉ የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶችንና ገንዘቦችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመያዝ፣ ለማገድ፣ ለመውረስ ወይም ለማስተዳደር የሚያስችል ግልጽና ዝርዝር የሕግ ማዕቀፍ በማበጀት ማንም ሰው ከሕገ-ወጥ ድርጊት ማናቸውንም አይነት የኢኮኖሚ ጥቅም እንዳያገኝ ለማድረግ እና የንብረት ማስመለስ ሕግ ወንጀልን በመከላከል ሂደት ያለውን ከፍተኛ ሚና ለማሳካት የሚያስችል የንብረት ማስመለስና ማስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡

የንብረት ማስመለስ የሕግ መዓቀፍ (አዋጅ) ዲያስፖራዎችን ኢላማ ያደረገ አለመሆኑ እና መደበኛ ባለሆነ መልኩ ገንዘብ በመላክ ንብረት ያፈሩትን ስጋት ላይ የማይጥል እንዲሁም ኢንቨስትመንትን የማይጎዳ ስለመሆኑ፡-

  • በመሰረቱ የትኛውም ሕግ አንድን የማኅበረሰብ ክፍል ኢላማ/ታርጌት/ አደርጎ (class/group discriminatory) በሆነ መልኩ ሊወጣ አይችልም፡፡ የሕግ መርህም አይደለም፡፡ በመሆኑም ህጉ ታርጌት አድርጎ የተነሳው የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል የለም፡፡ ሕግ ሁሌም ትኩረት የሚያደገው ህገወጥ ተግባሩ ላይ እንጂ ግለሰብ፣ድርጅት ወይም የተወሰነን ማህረሰብ አይደለም፡፡
  • ይህ ሕግ የሚመለከተው በህገወጥ መንገድ ከግለሰቦች፣ ከሕዝብ እና መንግሥት ላይ በወንጀል ድርጊት ምክንያት ንብረትና ሀብት ያፈሩ ሰዎችን ነው፡፡ እነዚህን ሰዎች በህገወጥ መንገድ ያገኙትን ንብረት ልትጠቀሙበት አይገባም ማለት ደግሞ በየትኛውም መመዘኛ ትክክለኛ እና ህጋዊ አካሄድ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ቁጥጥር የማይደረግበት የገንዘብ ፍሰት መኖር፣ ዜጎች ከላባቸው ይልቅ በወንጀል ድርጊት የሚከብሩበትን የሚያበረታታ ሀገር በተቃራኒው የዜጎችን ፍትሀዊ የሀብት ተጠቃሚነት ከማጥፋቱም በላይ በዚህ መልክ የሚገኙ ንብረቶች ምንም አይነት ክትትልና ቁጥጥር ስለማይደረግባቸው ተመልሶ ለተለያየ አይነት የወንጀል መፈጸሚያነት ሊውሉ እንደሚችሉ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚሸሹ ሀብቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስራን በግልጽ ስርዓት መምራት ደህንነቱ የተጠበቀ የፋይናንስ ፍሰተን የሚያረጋገጥ በመሆኑ ለኢንቨስትመንት ሳቢ እና አሰተማማኝ አካባቢ የሚፈጥር ነው፤ በዚህም ህጋዊ ሆነው የሚንቀሳቀሱ ባለሃብቶችንና ዜጎችን ከህገወጥ የሀብት ሰብሳቢዎች የሚጠብቅ ሕግ ነው፤
  • አንድን ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ይዟል የሚባልን ሰው በሚመረመርበት ወቅት ከውጭ ሀገር ተልኮለት የሰራውን ቤት ወይም ለኑሮ የሚያስፈልገውን ጥቂት ነገር ላይ ትኩረት ያደረገ ሳይሆን አጠቃላይ ግለሰቡ የመኖሪያ ቦታ፣ በተደጋጋሚ ግለሰቡ የሚገኝበት ቦታ፣ ግለሰቡ የሚይዛቸው ቅንጡ መኪናዎች፣ ጌጣጌጦች፣ የኑሮ ሁኔታ (life style and consumption/gifts), travel, expensive schools, መደበኛ ያልሆነ የባንክ ተቀማጭ፣ መደበኛ ያልሆኑ ግብይቶች (መሬት፣ ቤት ወይም የትኛውም ንብረት)፣ ከተለያዩ ተቋማት (ውጭ ሀገርም፣ ሀገር ውስጥም) እንዲሁም ግለሰቦች የሚመጣ ሪፖርት ወይም ጥቆማ በአንድነት የሚታዩ ጉዳዮች ናቸው እንጂ በጥቂት ጉዳዮች (ማንኛውም ሰው ለኑሮ የሚያስፈልገውን መጠቀሚያ) ላይ ያነጣጠረ አይደለም፡፡
  • ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ምርመራ በሚደረግበት ግዜ የአንድን ግለሰብ/ድርጅት ምንጩ የማይታወቀውን ንብረቱን ብቻ ሳይሆን ህጋዊ የገቢ ምንጩ ምን እንደሆነ በጥንቃቄ የሚታይ ስለሆነ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት አፍርቷል ብሎ ለመጠርጠር የአንድን ግለሰብ ሙሉ ፋይናንሻል ፕሮፋይል መሥራት በተለይም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት መለየት አስፈላጊ በመሆኑ በሂደቱ ከፍተኛ የሆነውን የገንዘብ እንቅስቃሴውን በማየት የሚወሰን እንጂ አንድ/ጥቂት የሆነን የገንዘብ እንቅስቃሴን ብቻ በማየት የሚወሰን አይደለም፡፡

ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ኃላፊነት የመብት መጠበቂያ መንገድ (safeguarding mechanism) የተቀመጡለት ስለመሆኑ፤

ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ኃላፊነትን በተመለከተ የመብት መጠበቂያ መንገድ safeguarding mechanism የተቀመጡለት ስለመሆኑ በአወጁ በግልፅ የተደነገጉ ናቸዉ፡፡ ከእነዚህም መካከል:-

የመብት መጠበቂያ (Legal safe guards)

  • ጉዳዩ ፍርድ ቤት ከመሄዱ በፊት ተጠርጣሪው ስለንብረቱ ህጋዊ ምንጭ ለዐቃቤ ሕግ/ለሀብት መርማሪ የማስረዳት መብት የሚሰጥ መሆኑ፤
  • ነፃ እና ገለልተኛ የፍርድ ቤት ውሳኔ ሰጪነት የሚካተት መሆኑ (Judicial Oversight)፡
  • ከዚህ በተጨማሪ የንብረቱን ምንጭ እንዲያስረዳ የተጠየቀው ሰው የንብረት ምንጩን ለማስረዳት በራሱ ላይ የወንጀል ኃላፊነት የሚያመጣበት ማስረጃ ቢሰጥም በወንጀል ችሎት ላይ ማስረጃ ሆኖ እንዳይቀርብ በማድረግ የመብት ጥበቃን ያደርጋል፡፡
  • የታወቀ መረጃን አጠቃቀም እና ለሶስተኛ ወገን ይህን መረጃ ስለማሳወቅ የሚመለከት ገደብ (Limitation on the use of disclosed information and disclosed to third parties)
  • የቅን ልቦና ገዢዎችን መብት ያከበረ መሆኑ
  • ዝቅተኛው የንብረት ዋጋ ግምት መነሻ (10,000,000) የልዩነት ዋጋ (ጠቅላላ ሀብት ሳይሆን) ተደርጎ መቀመጡ (minimum threshold for the value)

ተቋማዊ ጥበቃ (institutional safeguards)

  • ገለልተኛ የሆነ ቁጥጥር (independent oversight of the UWO system)
  • በዳኝኘት አካል ወይም በዳኛ የሚወሰን ጉዳይ (Review by a judicial officer)

ተግባራዊ ጥበቃዎች(practical safe guards)፤ ፍትሃዊ ሂደት እና ሥነ-ሥርአት (fair process and procedures) በተለይም ምርመራ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅና ያለው በግዜ የተገደበ፣ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ መሆን የሚገባው መሆኑ::

ክፍል ሁለት

የንብረት ማስመለስ አዋጅ የተካተተው ውርስ ከወንጀል ህጉ የንብረት መውረስ ቅጣት የሚለይበት አግባብ

ንብረት መውረስ በጠቅላላው በወንጀል ሕጉ ወይም በሌሎች የወንጀል ድንጋጌዎች የንብረት መውረስ እንደቅጣት ያልተቀመጠ ቢሆንም እንኳን በድርጊቱ ጥቅም መገኘቱ ከተረጋገጠ ንብረቱ እንደሚወረስ የሚደነግግ ነው፡፡ ይህም ማለት ማንኛውም ሰው ከወንጀል ድርጊቱ ሊጠቀም የማይገባ በመሆኑ እና በወንጀል ሕጉ መሠረት ንብረት የማይወረስባቸው ነገር ግን በእጅጉ የኢኮኖሚ ጥቅም የሚያስገኙ ወንጀሎችንም የሚያካትት ነው፡፡

በጥፋተኝነት ላይ የተመሰረተ እና ያልተመሰረተ ውርስ ልዩነት

በጥፋተኝነት ላይ የተመሠረተ የንብረት መውረስ የውርስ መርህ ሲሆን ሁሉንም የይግባኝ ሂደቶችን አልፎ የመጨረሻ የጥፋተኝነት ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ በሚቆጠር ለወንጀል ቅጣት አፈጻጸም በወንጀል ሕግ በተቀመጠው የይርጋ የጊዜ ገደብ ውስጥ ዐቃቤ ሕግ በሚያቀርበው ማመለክቻ መሠረት በፍርድ ቤት የሚሰጥ የውርስ ትእዛዝ ነው፡፡ በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሠረተ የንብረት መውረስ በተለየ ሁኔታ በግልጽ ተዘረዝረው የተቀመጡ ጉዳዮችን መሠረት በማድረግ ይህም የወንጀል ጉዳዩን የሚመራው ሥነ-ሥርዓት ሂደት እና በሌሎች ምክንያቶች የወንጀሉን ተጠያቂነት ማስቀጠል የማይቻል ከሆነ ወይም የሚቋረጥበት ሁኔታ ሲፈጠር ወይም በማንኛውም ምክንያት የወንጀል ጥፋተኛነት ውሳኔ ማሰጠት የማይቻልበት ሁኔታ ከተፈጠረ እና ከወንጀል የተገኘ ጥቅም መኖሩ በማስረጃ ሲረጋገጥ የሚሰጥ የውርስ ውሳኔ ነው፡፡

ጥፋተኝነት በፍርድ ቤት ሳይሰጥ ንብረት እንዲወረስ ማደረግ የዜጎችን ህገ-መንገስታዊ ንብረት የማፍራት መብት የማይጥስ ስለመሆኑ

ሲጀምር ይሄ ስርዐት በዚሀ ሕግ አዲስ የመጣ እና የተዋወቀ አይደለም፡፡ በአዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 35 ስር ጥፋተኝነት ሳይሰጥ ንብረት ስለሚወረስበት አግባብ ከሚታወቅበት ሶስት መነሻዎች (ተከሳሽ ሲሞት፣ ሲጠፋ ወይም ሳይታወቅ ሲቀር) ከሚለው ሰፋ ባለ መልኩ ተግባራዊ ሊሆን ወደሚችልበት ማዕቀፍ መጥቷል እንጂ አዲስ ሀሳብ አይደለም፡፡ ስለሆነም ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ሰፊ የሆነ የዕውቀትና የአረዳድ ችግር እንዳለ በማወቅ ወደተግባር መግባት ያስፈልጋል።

በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሠረት ውርስ ሲባል ዐቃቤ ሕግ እየተነሳ ንብረትን ይወርሳል ሳይሆን ጉዳዩ ላይ አሁንም ቢሆን የውርስ ትእዛዝ መስጠት የሚችለው ፍርድ ቤት መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ መንገዱ ነው የተቀየረው እንጂ ለዐቃቤ ሕግ የማይረጋገጥ/Check የማይደረግ የዘፈቀደ ንብረትን የመውረስ ሥልጣን ሰጥቶታል ማለት አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ በአዋጁ በተቀመጡት ሁኔታዎች የወንጀል ክስ ማቅረብ ሳይቻል ሲቀር (ለምሳሌ ሰውየው ቢሞት፣ ቢጠፋ፣ በይቅርታ ቢወጣ፣ በወንጀል የማስረጃ ምዘና በወንጀል ጥፋተኝነት ለማረጋገጥ የሚያስችል በቂ ወይ ተቀባይነት ያለው መረጃ ሳይገኝ ሲቀር) ለፍርድ ቤት የሚቀርብ ፍትሀብሔራዊ ባህሪ ያለው የውርስ አቤቱታን ተከትሎ በፍርድ ቤት የሚሰጥ ውሳኔ ነው፡፡ መረሳት የሌለበት ይሄ የውርስ አይነት መርህ ሳይሆን ልዩ ሁኔታ መሆኑ ነው፡፡

አስር ዓመት ወደ ኋላሄዶ ተፈፃሚ የሚሆንበት መሰረቱ(የሕግ አግባብ) እንዲሁም ምክንያት

የሀብት ማሰመለስ አዋጁ በአጠቃላይ ሲታይ ተፈጻሚነቱ ወደፊት ነው ነገር ግን ክፍል 2 ስር የተደነገገው ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ብቻ ተፈጻሚነቱ ወደኋላ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 8 ላይ ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ክስ የሚቀርብበት ጊዜ እና የገንዘብ መጠን ተደንግጓል፡፡ በዚህ አንቀጽ ስር የተካተተው አዋጁ ወደኋላ 10 ዓመት ተመልሶ የሚሠራ መሆኑንና ይህንንም ለመክሰስ የአስር ሚሊዮን የገንዘብ ገደብ ተቀምጧል፡፡ ይህም የገንዘብ ገደብ የተቀመጠበት ዋነኛ ምክንያት በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ያለውን የሰው ሃይል (የስራውን ስፋት መሸከምና ለመሥራት የሚያስችል ልምድና ብቃት ያለው)፣ የመክሰስ አቅም እና የፋይናንስ አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት አነስተኛ የሃብት መጠን ያላቸውን ግለሰቦች በመተው ከፍተኛ ንብረት ያላቸውን ተጠያቂ ለማድረግ በማሰብ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሕጉ ወደኋላ ተመልሶ እንደመስራቱ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ማሕበራዊ እና የፋይናንስ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያደርሳሉ ተብሎ የሚገመቱትን ግለሰቦችና ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ድርጅቶችን ተጠያቂ ማድረግ የተሻለ አማራጭ ሆኖ ስለተገኘ ነው፡፡

ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን በተመለከተ ወደ ኋላ ሄዶ የማይሰራ ከሆነ፤ ከዚህ በፊት በህገ ወጥ መንገድ ንብረት ያፈሩ ሰዎችን ህጉ ከወጣ በኋላ ብቻ ተጠያቂ የምናደርግ ከሆነ፤ በሕገ ወጥ መንገድ ያገኙትን ንብረት ህጋዊ የማድረግ (blessing) እንድምታ ያለዉ በመሆኑ፤ እንዲሁም አዋጁ እንደሌሎች ህጎች ከወጣ በኋላ ተፈፃሚ የሚሆን ከሆነ በዚህ አዋጅ ልንጠይቅ የምንችለዉ ቀጣዩን ትውልድ ብቻ በመሆን ከአዋጁ ዓላማ እንፃር ወደ ኋላ ሄዶ እንዲሰራ ማድረጉ አስፈላጊ ሆኗል፤ ከዚህ በተጨማሪም የሌሎች ሀገራት ልምድም ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን በተመለከተ ህጋቸው ወደኋላ ሄዶ ተፈፃሚ እንደሚሆን ያመለክታል።

በሌላ በኩል አዋጁ ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ተጠያቂነት ያለምንም የገንዘብ መጠን ተፈጻሚ ይደረጋል፡፡ ይህ ድንጋጌ እስካሁን ድረስ ከፍተኛ ውዝግብ እያስነሳ የሚገኝ ሲሆን በተለየ ሁኔታ ትኩረት የሚሻ ነው፤ በተለይም በአፈጻጸም ረገድ ከመነሻው ጀምሮ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ያልተፈለጉ ጉዳዮችን በመለየት በዝርዝር አሠራር ሂደት ሊቀረፉ ይገባል። አዋጁ በረቂቅ ደረጃ ከመነሻዉም ጀምሮ ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን ለማስረዳት የሚቀርቡ ማስረጃዎችን በተመለከተ የተዛቡ ነገሮች በሚድያም ሲቀርብ ስለነበር፤ አዋጁ ከመዉጣቱ ጋር ተያይዞ የካፒታል መሸሽ እንዳያገጥም ከጥቂት ዓመታት በፊት አብዛኛዉ ማኅበረሰብ ግብይቱ ካሽ ቤዝድ በመሆኑ እና በመደበኛ የባንክ ሥርዓት ክፍያን ስለማይፈፅም ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ስራ መሥራት አስፈላጊ ነው።

ከ10 ዓመት ወደኋላ በመሄድ የሀብትን ምንጭ በመረጃ ማስረዳት ለኛ ሀገር የመረጃ አያያዝ ደካማ በሆነበት ዜጎች ላይ ጫና የማይፈጥር ስለመሆኑ፤

አዋጁ የሀብት ምንጭ አስራዳ ሲባል ሀብቱን ያገኘበትን (source of fund) እንዲያስረዳ እንጂ ለእያንዳነድ ላፈረኋው ንብረት ደረሰኝ አቅረብ እያለ አይደለም፡፡ አንደ ሰው ያለ አግባብ ያፈራው ንብረት ቤት ቢሆን ቤቱን የገዛበት የሸያጭ ውል አይደለም የሀብት ምንጭ ማስረጃ ተደርጎ የሚቆጠረው፡፡ ቤቱን የገዛበትን ሀብት ያገኘበት ምንጭ ህጋዊ መሆኑን ማስረዳት መቻል አለበት፡፡ ቤቱን ለመግዛት ያወጣው ብር የተገኘው በህጋዊ መንገድ መሆኑን ነው የምርመራው/የክሱ ዋና ጭብጥ ይህ ደግሞ የግድ በሰነድ ብቻ የሚረጋገጥ አይደለም፡፡ ህጉ የሀብት ምንጭን ለማስረዳት የሰነድ ማስረጃ ብቻ ነው ብሎ ገደብ አላደረገም፡፡

አዋጁ ለጠቋሚዎች ማበረታቻ መስጠቱ መጠቃቂያ እንዳይሆን የተደረግ የሕግ መአቀፍ ስለመሆኑ፤

በወንጀል የተገኘን ሀብት በተመለከተ በራሱ የወንጀል ጥቆማ ብቻ ማቅረብ በቂ በመሆኑ ምክንያት የወንጀል ጠቋሚዎችና ምስክሮች አዋጅ እንዲሁም በወንጀል ሥነ-ሥርዓት የሚገዛው ሂደት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በንብረት ማስመለስ አዋጅ ስር ንብረት ጠቋሚ የሚለው ሃሳብ መሠረታዊ መነሻ በወንጀል እና በሌሎች ህገወጥ ተግባራት ሀብት የሚያካብቱ ሰዎች በአመዛኙ የሰሩትን ወንጀል በማስረጃ ለማረጋገጥ እና በወንጀል ለመክሰስ ባይቻል እንኳን ምንም አይነት ህጋዊ ስራ ወይም የገቢ ምንጭ ሳይኖራቸው ሰፊ ሀብት አካብተው የሚገኙ ሰዎች በማህበረሰቡ ውስጥ በደንብ የሚታወቁ ቢሆንም ይህንን ማጋለጥ በራሱ በጠቋሚዎች ላይ የሚፈጥረው የንብረት እና የህልውና አደጋ ቀላል የማይባል በመሆኑ ምክንያት ለጠቋሚዎች ተገቢ የሚባል ማበረታቻ መስጠት በራሱ ጥቆማ ለመስጠት እንዲነሳሱ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አግኝተው እራሳቸውን የሚጠብቁበትን ሁኔታ ማመቻቸት በራሱ ውጤታማ አሠራር እንደሆነ ከተለያዩ ሀገራት ልምድ ማየት ይቻላል፡፡

ነገር ግን የቀረበ ጥቆማ ሁሉክስ ይቀርብበታል ማለት አይደለም፡፡ ጥቆማው እንደማንኛወም ጥቆማ በምርመራ ውስጥ የሚያልፍ ሆኖ ዐቃቤ ሕግ በጉዳዩ ላይ ክሰ ለማቅረብ የሚያስችል በቂ ማስረጃ ሲኖረው ብቻ ነው ክስ የሚያቀረበው፡፡ ከዚህም አልፎ ደግሞ ጥቆማን መነሻ በማድረግ ክስ ቢቀረብም ዞረዘሮ ውሳኔ የሚሰጠው ሁለቱም ተከራረካሪ ወገኖች በግልጽ እና ገለልተኛ ችሎት ፊት ክርክር አድረገው መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ስለዚህ ትክክለኛ እና መሠረታዊ ማሰረጃ ያላቸው ጥቆማዎች ብቻ ተመርምረው ክስ የሚቀርብባቸው በመሆኑ፣ የትኛውንም ያህል ጥቆማ ቢቀረብ መሰረተ ቢስ ከሆነ ምንም አይነት ውጤት ስለማያስከትል የዜጎች የንብረት መብት እንዲሁ በአሉባልታ ጣልቃ የሚገባበት አለመሆኑን operationally እያረጋገጥነው የምንሄደው ጉዳይ ነው::