የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት የወንጀል ተጠያቂነት በኢትዮጵያ

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

በሕግ ሁለት ዓይነት ሰዎች አሉ፡፡ እነሱም የተፈጥሮ ሰው እና በሕግ ሕጋዊ ሰውነት የተሰጠው ሰው ናቸው፡፡ በሕግ ህጋዊ ሰውነት የተሰጠው ሰው ማለት የንግድ ድርጅቶች፣ ማህበራት እና መሰል ሌሎች ድርጅቶችን የሚመለከት ነው፡፡ የተፈጥሮ ሰው ወንጀል ሲሰራ በሕግ እንደሚጠየቅ ሁሉ የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት በወንጀል የሚጠየቅበት ሁኔታ በህጉ ተመልክቷል፡፡ በዚህ ጽሑፍ በሀገራችን ድርጅት በወንጀል የሚጠየቅበትን ሁኔታ እና ተያያዥ ጉዳዮችን እንዳስሳለን፡፡

የድርጅት ምንነት

በሀገራችን የድርጅት የወንጀል ተጠያቂነትን በተመለከተ መነሻ የሆነው የወንጀል ህጉ አንቀጽ 34 ሲሆን ለድንጋጌው ዓላማ ለድርጅትን ምንነት ትርጓሜ ሰጥቶ እናገኛለን፡፡ በዚህ ድንጋጌ ንዑስ አንቀጽ 4 መሠረት “ድርጅት” ማለት መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆነ ወይም ሕዝባዊም ሆነ ግላዊ መዋቅር ያለው አካል ሲሆን ለንግድ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለፖለቲካ፣ ለሃይማኖት ወይም ለሌላ ሕጋዊ ዓላማ የተቋቋመንና በመንግሥት ዕውቅና ያገኘን ማናቸውንም ማኅበር እንደሚያጠቃልል ደንግጓል፡፡ ሆኖም የመንግሥት አስተዳደር አካላት ወይም ተቋማት በሕግ ሰውነት የተሰጣቸው ቢሆንም በዚህ ድንጋጌ ውስጥ በድርጅትነት የሚሸፈኑ አይደሉም፡፡

ድርጅት በወንጀል የሚጠየቅበት ሁኔታ

የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት በወንጀል ተጠያቂ ሊሆን የሚችለው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 34 በተመለከቱት ሁኔታዎች ነው፡፡

ይኸውም

  • አንድ የወንጀል ድርጊት በድርጅት ከተፈፀመ አስቀጪ እንደሆነ በህጉ በግልፅ ሲደነገግ እና
  • ከሀላፊዎቹ ወይም ከሰራተኞቹ አንዱ ከድርጅቱ ሥራ ጋር በተያያዘ የድርጅቱን ጥቅም በህገወጥ መንገድ ለማራመድ በማሰብ ወይም የድርጅቱን ህጋዊ ግዴታ በመጣስ ወይም ድርጅቱን በመሳሪያነት ያለአግባብ በመጠቀም በዋና ወንጀል አድራጊነት፣ በአነሳሽነት ወይም በአባሪነት ወንጀል ካደረገ ነው፡፡

የድርጅትን የወንጀል ተጠያቂነት ያካተቱ ህጎች

ድርጅት በወንጀል ሊጠየቅ የሚችለው አንድ ወንጀል በድርጅት በተፈፀመ ጊዜ ድርጅቱ በወንጀል ሊጠየቅ እንደሚችል በህጉ በግልፅ ሲደነገግ ነው፡፡ ይህን መነሻ በማድረግም በሀገራችን በሥራ ላይ ያሉ በርካታ የወንጀል ድንጋጌዎችን ያካተቱ ልዩ ህጎች ድርጅት በወንጀል ተጠያቂ የሚሆንባቸውን ሁኔታዎች ደንግገዋል፡፡ ለአብነት የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣ አዋጅ ቁጥር 881/2007 በአዋጁ አንቀጽ 5፣ በፌደራል የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 132፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 33፣ በሰው የመነገድ እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀጽ 18፣ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 17 እና የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥር አዋጅ 1177/2012 አንቀጽ 22(11) ይጠቀሳሉ፡፡

ህጋዊ ሰውነት በተሰጠው ድርጅት ላይ የሚጣል የወንጀል ቅጣት

ድርጅት በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ቢገኝም ድርጅትን እንደተፈጥሮ ሰው ማሰር ስለማይቻል በድርጅት ላይ በዋናነት የሚጣለው ቅጣት በወንጀል ህጉ አንቀጽ 90(3) የተመለከተው የገንዘብ መቀጮ ነው። ይህ ማለት አንድ ወንጀል በተፈጥሮ ሰው ሲፈፀም በእስራት የሚያስቀጣ ከሆነ እና ወንጀል ፈፃሚው ህጋዊ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት ሆኖ ከተገኘ ለእስራቱ ተመጣጣኝ ነው ተብሎ በህጉ በተደነገገው የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል ማለት ነው፡፡ ከመቀጮ በተጨማሪ በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ድርጅት እንዲታገድ፣ እንዲፈርስ፣ እንዲዘጋ ሊወሰን እንደሚችል ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 34(2) መረዳት ይቻላል፡፡

በወንጀል ህጉ አንቀጽ 90(3) መሠረት የመንግሥት የአስተዳደር አካላትን ሳይጨምር የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት በወንጀል ተካፋይ ሆኖ ሲገኝ የድርጅቱ ሀላፊዎች ወይም ሰራተኞች በየግላቸው መጠየቃቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ድርጅቱ ወንጀል ተጠያቂ ተደርጎ

  1. እስከ 5 ዓመት ቀላል እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ አስር ሺህ ብር
  2. እስከ 5 ዓመት ፅኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ ሀያ ሺህ ብር
  3. እስከ 10 ዓመት ፅኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ ሀምሳ ሺህ ብር
  4. ከ10 ዓመት በላይ ፅኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር፣ መቀጮ እንዲከፍል ይወሰንበታል፡፡

የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት ጥፋተኛ የተባለበት ድንጋጌ በመቀጮ ብቻ ሚያስቀጣ በሆነ ጊዜ ደግሞ በድርጅቱ ላይ ሚጣለው ቅጣት የመቀጮውን አምስት እጥፍ እንደሚሆን በወንጀል ህጉ አንቀጽ 90(4) ተደንግጓል፡፡

ሆኖም ይህ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 90 የተደነገገው ቢኖርም በልዩ ህጎች የተለየ ቅጣት ሊቀመጥ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በሰው የመነገድ እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀጽ 18 መሠረት

  1. በቀላል እስራት ወይም እስከ 5 ዓመት ፅኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር
  2. ከ5 ዓመት እስከ 15 ዓመት ፅኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል ከአምስት መቶ ሺህ እሰከ አንድ ሚሊዮን ብር
  3. ከ15 እስከ 20 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል ከአንድ ሚሊዮን እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር
  4. ከ20 ዓመት በላይ በሆነ እስራት ወይም ሞት ለሚያስቀጣ ወንጀል ከሁለት ሚሊዮን እስከ ሶስት ሚሊዮን ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡

በተመሳሳይ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1176/2012፣ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥር አዋጅ 1177/2012 እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣ አዋጅ ቁጥር 881/2007 ለድርጅት ተፈፃሚ የሚሆን የየራሳቸውን የመቀጮ መጠን ደንግገዋል፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ በዘመናዊ የሕግ ሥርአት የተፈጥሮ ሰው ብቻ ሳይሆን በሕግ በግልፅ በተደነገገ ጊዜ ህጋዊ ሰውነት የተሰጠው ድርጅትም የወንጀል ተጠያቂነት ያለበት መሆኑን ማወቅና ድርጅቶችን የወንጀል ተጠያቂ ከሚያደርጉ የወንጀል ተግባራት መታቀብ ያስፈልጋል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ