መግቢያ
በሀገራችንም ሆነ በተለያዩ የዓለማችን አካባቢዎች በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የተለያዩ ወንጀሎች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ የጠለፋ ወንጀል ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ወንጀል በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ በአምስተኛው መጽሀፍ በምዕራፍ 4 ርዕስ 2 ስር በሰው ነጻነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ተብለው ከተደነገጉት ውስጥ የሚመደብ የወንጀል ዓይነት ነው፡፡ ጠለፋ በሁለቱም ጾታዎች ላይ ሊፈፀም የሚችል ሲሆን በዋነኛነት በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚፈጸም ነው፡፡ በ1996 ዓ.ም የወጣው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ የጥቃትን መጠን እና ዓላማ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለጠለፋ ጥብቅ ተጠያቂነት ያስቀምጣል። የጠለፋ ድርጊቶችን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት የተለያዩ እርምጃዎች የተወሰዱ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ለድርጊቶች ተጎጂዎች ጥበቃን የሚሰጡ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ማፅደቅ፣ አገራዊ ህጎችን ማውጣት እንዲሁም ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች መስጠት ይገኙበታል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ ስለ ጠለፋ ምንነት፣ ጠለፋ ድርጊትን ሽፋን የሰጡ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን፣ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት እና በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ ክልከላ የተደረገባቸውና የወንጀል ቅጣትን የሚያስከትሉ ድርጊቶችን እንመለከታለን፡፡
የጠለፋ ምንነት
ታዋቂው የሕግ መዝገበ ቃላት ብላክስ ሎው በ8ኛ እትሙ ጠለፋን ሲተረጉመው “The act of leading someone away by force or fraudulent persuasion” በሚል ሲሆን አንድን ሰው በማስገደድ ወይም በማጭበርበር ያለ ፈቃድ በማሳመን፣ በማጭበርበር ወይም በኃይል መውሰድ እንደሆነ አስቀምጦታል፡፡ ጠለፋ በወንጀል ህጋችን በግልጽ ትርጉም ባይሰጠውም በአውደ ጥበባዊ የሕግ መዝገበ ቃላት ጠለፋ ማለት አንድን ሰው በጉልበት አፍኖ በመውሰድ እና በመደበቅ ገንዘብ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት ነው። ሰውን የመጥለፍ ወንጀል ጽንሰ ሀሳብ ሰውን በጉልበት መውሰድ እና መደበቅ ነው፡፡ ጠለፋ በኃይል በተንኮል፣ በማታለል፣ በመጥለፍ የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ሲባል ሰውን/ሴትን መውሰድ ነው በሚል ተርጉሞታል፡፡
እንዴት ይፈጸማል
ጠለፋ አንዲትን ሴት በግዳጅ ጋብቻ ለማስፈጸም በማሰብ የሚደረግ ያለፈቃዷ ወደ ሌላ ቦታ የመውሰድና አስገድዶ የማቆየት ድርጊት ነው፡፡ይህ ድርጊት ከሴቷ እና ከቤተሰብ ፈቃድ ውጭ በማስገደድ የሚፈፀም ጋብቻ ነው፡፡ እንደሌሎች ጥቃት ሁሉ ድርጊቱ በሀገራችን በተለይም በገጠር አካባቢ ተስፋፍቶ የሚታይ ነው፡፡ የምትጠለፈው ሴት ድብደባ እና እንግልት ስለሚደርስባት ለአካል ጉዳት ወይም ሞት፣ ደስተኛ ያልሆነና ያልተረጋጋ ሕይወት (ጋብቻ) መኖር፣ ጭንቀት፣ ትምህርት (ሥራ ማቋረጥ) ወዘተ… የመሳሰሉትን ጉዳቶች ሊያስከትል ይችላል ፡፡ የጠለፋ ወንጀል በኢ.ፌዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ ከ587-588 ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ወንጀሉ የሚከብደው ደግሞ በአንቀጽ 590 መሠረት ነው፡፡
ጠለፋ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች /ሕግ እንዴት ይታያል
በተለያዩ የዓለም አቀፉ ስምምነቶች በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ጠለፋ አጥብቆ ያወግዛል። በነዚህ ዓለማቀፍ ስምምነቶች መሠረት ሀገራት በግዳጅ ጋብቻ፣ በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እና ሴቶችን ለወሲብ ንግድ በማሰማራት ምክንያት ጠለፋ ወንጀልን የመከላከል እና በሕግ የመጠየቅ ግዴታ አለባቸው። ከስምምነቶቹም መካከል፡-
- ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) አንቀጽ 3 እያንዳንዱ ሰው የሕይወት፣ የነጻነትና የደኅንነት መብት አለው፡፡ እንዲሁም በአንቀጽ 2 ላይ “ማንኛውም ሰው በዘር፣ ቀለም፣ ጾታ፣ እና ሌሎች ምክንያቶች ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግበት በመግለጫው ውስጥ የተቀመጡትን መብቶችና ነፃነቶች የማግኘት መብት አለው” በማለት ያስቀምጣል፡፡ በመግለጫው አንቀጽ 4 የግዳጅ ጋብቻን እና ጠለፋን ጨምሮ ባርነት መከልከሉን ያሳያል በተመሳሳይ አንቀጽ 16 ጋብቻ በነጻ እና ሙሉ ስምምነት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ይገልጻል። በመሆኑም ሴቶች እና ሕፃናት በስምምነቱ የተካተቱ መብቶች ተጠቃሚ ለመሆን በጾታና በእድሜያቸው ምክንያት ከሚደርሱባቸው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የመጠበቅ መብት አላቸው፡፡
- የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተርም አንቀጽ 6 ማንኛውም ሰው ነፃነቱና አካላዊ ደህንነቱ ተጠብቆለት የመኖር መብት አለው፡፡ ቀድሞ በሕግ በተደነገጉት ሁኔታዎችና ምክንያቶች ካልሆነ በስተቀር ማንም ሰው ነፃነቱን እንዲያጣ ሊደረግ አይችልም በማለት ደንግጓል፡፡
- በሴቶች ላይ የሚደረጉ ማናቸውም ዓይነት ልዩነት ወይም አድሎ ለማስወገድ የወጣ ስምምነት (The Convention on the Elimination of All Forms of Discrimination against Women (CEDAW), 1979) አንቀጽ 2 (ረ) እንደሚደነግገው በሴቶች ላይ አድልዎ የሚፈጥሩ ልማዶች ለማስወገድ ነባር ሕጎችን፣ ደንቦችን ለማሻሻል ወይም ለመሻር ጨምሮ ሁሉንም ተገቢ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው፡፡በኮንቬንሽኑ አንቀጽ 6 መሠረት ክልሎች የሴቶችን ህገወጥ ዝውውር እና ብዝበዛ ለመከላከል እርምጃዎችን እንዲወስዱ ይደነግጋል።በተመሳሳይ መልኩ ኮንቬንሽኑ ሴቶች በነጻነት የትዳር ጓደኛ የመምረጥ እና ሙሉ ፍቃድ ወደ ጋብቻ የመግባት መብት ዋስትና ይሰጣል። የCEDAW አጠቃላይ ምክረ ሃሳብ ቁጥር 19 (1992) እና 35(2017) ለግዳጅ ጋብቻ ጠለፋ እንደ ጾታ-ተኮር ጥቃት ሆኖ ተቀምጧል።
- በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለማስወገድ የተሰጠ መግለጫ (Declaration on the Elimination of Violence Against Women (DEVAW),1993) በአንቀጽ 4 ስር እንደሚያስቀምጠው የስምምነቱ አባል መንግስታት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ማውገዝ እንዳለባቸው ግዴታ የሚጥል ሲሆን በተጨማሪም ይህን ግዴታቸውን ላለመወጣትና ጥቃቶቹን ላለማስወገድ ማንኛውንም ባህል፣ ወግ ወይም ሃይማኖት እንደ ምክንያት ማንሳት አይችሉም፡፡
- የአፍሪካ የሰብዓዊ እና ህዝቦች መብቶች ቻርተር እና የማፑቶ ፕሮቶኮል (2003) ሴቶች የትዳር ጓደኛቸውን በነጻነት የመምረጥ መብታቸውን አረጋግጠዋል። ጠለፋ እና አስገዳጅ ጋብቻን ጨምሮ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ሁሉ ይከለክላል:አባል ሀገሮችም ለጋብቻ ጠለፋን ጨምሮ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ወንጀል እንዲያደርጉና እርምጃ እንዲወስዱ ይደነግጋል፡፡
ጠለፋ በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 35 (4) ሴቶችን የሚጨቁኑ ወይም በአካላቸው ወይም በአዕምሮአቸው ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ሕጎች፣ ወጎችና ልማዶች የተከለከሉ መሆናቸውን እና ሴቶች ከጎጂ ባህል ተፅዕኖ የመላቀቅ መብታቸውን መንግሥት ማክበር እንዳለበት ይደነግጋል፡፡
ሕገ- መንግሥት ጥቅል እና ዝርዝር ጉዳዮችን የማያካትት ሕግ በመሆኑ በሰው ነጻነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዝርዝር ሁኔታዎች በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ ተካተው ይገኛሉ፡፡ በዚሁ መሠረት የወንጀል ሕጉ የተከለከሉ ድርጊቶችን በመዘርዘር የሚያስከትሉትንም ቅጣት ያስቀምጣል፡፡
የጠለፋ ዓይነቶች እና የወንጀል ተጠያቂነታቸው
በወንጀል ሕጉ ከተቀመጡት ክልከላዎች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡-
1. ሰውን መጥለፍ (አንቀጽ 586) ፡- ይህ የጠለፋ አይነት በሁለቱም ጾታ ወይም በማንኛውም ሰው ላይ የሚፈጸም ሲሆን ማንም ሰው በኃይል ሌላውን ሰው አፍኖ የወሰደ እንደሆነ፣ ወይም ይህንኑ ድርጊት የፈፀመው በዛቻ፣ በማስገደድ፣ በተንኮል፣ በማታለል ወይም በማናቸውም ሌላ አኳኋን የሌላውን ሰው ፈቃድ ካገኘ በኋላ እንደሆነ ከ7 (ሰባት) ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡
2. ሴትን መጥለፍ (አንቀጽ 587) ፡- ማንም ሰው አንዲት ሴትን አገባታለሁ በሚል አሳብ በኃይል የጠለፈ እንደሆነ፣ ወይም ይህንኑ ድርጊት የፈፀመው በማስፈራራት፣ በዛቻ፣ በተንኮል ወይም በማታለል ፈቃደኛ እንድትሆን ካደረገ በኋላ እንደሆነ ከ 3 እስከ 10 ዓመት ሊደርስ በሚችል ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ በተለይም የጠለፋ ድርጊቱን ተከትሎ አድራጊው ሴትዮዋን አስገድዶ የደፈረ እንደሆነ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ ስለ አስገድዶ መድፈር በተመለከተው ድንጋጌ ( አንቀጽ 620) መሠረት በተጨማሪ ከ5 እስከ 20 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣልይቀጣል፡፡ የግብረ ስጋ ድፍረቱ ከ18 ዓመት በታች በሆኑ ህጻናት ላይ ተፈጽሞ ከሆነ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 627 መሠረት ከ 15 እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ያስቀጣል፡፡ የጠለፋ ድርጊት ተከትሎ በጠላፊውና በተጠላፊዋ መሀከል ጋብቻ መፈፀሙ የወንጀል ተጠያቂነትን አያስቀርም፡፡ ጠላፊውን ከወንጀል ተጠያቂነቱ ሌላ ተጠላፊዋ (ተበዳይዋ) በጠለፋው ድርጊት ለደረሰባት የኅሊናና የማቴሪያል ጉዳት አግባብ ባላቸው የፍትሐብሔር ሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ካሣ የመጠየቅ መብት አላት፡፡
3. ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን መጥለፍ (አንቀጽ 589) ፡- ማንም ሰው ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን በኃይል አፍኖ የወሰደ አንደሆነ፣ ወይም ይህንኑ ድርጊት የፈፀመው በዛቻ፣ በማስገደድ፣ በተንኮል፣ በማታለል ወይም በማናቸውም ሌላ አኳኋን የልጁን ፈቃድ ካገኘ በኋላ እንደሆነ ከ 5 ዓመት እስከ 15 ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ እንዲሁም ማንም ሰው ወላጅን ወይም የአሳዳሪውን የማሳደግ ወይም የመጠበቅ ሕጋዊ መብት ለማሳጣት በማቀድ ለአካለመጠን ያልደረሰ ልጅ የወሰደ፣ የጠለፈ ወይም ያለአግባብ ይዞ ያስቀመጠ እንደሆነ ከ 5 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡
4. የአዕምሮ ሕመምተኛ የሆነችን ወይም የመከላከል አቅም የሌላትን ሴት መጥለፍ (አንቀጽ 588) ፡- ማንም ሰው ያበደችን፣ የአዕምሮ ጉድለት ወይም ዝግመት ያለባትን፣ ሕሊናዋ የሳተችውን ወይም ራሷን ለመከላከል ወይም ጥቃትን ለመመለስ የማትችለውን ወይም ራሷን ለመከላከል እንዳትችል የተደረገችውን ሴት ሁኔታ እያወቀ አስቦ የጠለፈ እንደሆነ ከ5 ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡
ወንጀሉን የሚያከብዱ ሁኔታዎች (አንቀጽ 590) ፡-
የጠለፋው ድርጊት በተፈፀመበት ጊዜ ዛቻው፣ ማስገደዱ፣ የመወሰን ችሎታን ማሳጣቱ፣ ከሕግ ውጭ ይዞ ማስቀመጡ ወይም መጥለፉ የተፈፀመው ፡-
- የማይገባ ጥቅም ከተጎጀው ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ወይም ለግልሙትና ወይም ለአመንዝራነት ተግባር ወይም ለንጽህና ክብር ተቃራኒ ለሆነ ተግባር ለመጠቀም ወይም ለዚሁ ተግባር አሳልፎ ለመስጠት በማሰብ፣ ወይም
- ተጎጅውን ለመበዝበዝ ወይም ጥቅም፣ ገንዘብ ለመቀበል፣ ወይም
- የተለየ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ እንደሆነ፣ ወንጀሉ የከበደ ሆኖ በሚከተሉት ድንጋጌዎች እንደሚከተለው ይሆናል፡-
ወንጀሉ፡-
- ዛቻ ወይም ማስገደድ (አንቀጽ 580- 582) ሲሆን ከ 3 ወር እስከ 5 ዓመት መድረስ የሚችል ቀላል እስራት፣
- የመወሰን ችሎታን ማሳጣት ወይም ከሕግ ውጭ ይዞ ማስቀመጥ (አንቀጽ 583 እና 585) ሲሆን ከ7 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት፣
- መጥለፍ (አንቀጽ 586 እና 587) ሲሆን ከ 5 ዓመት እስከ 15 ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስራት፣
- የአዕምሮ ሕመምተኛ የሆነችን ወይም ለመከላከል አቅም የሌላትን ሴት መጥለፍ (አንቀጽ 588) ሲሆን ከ7 ዓመት እስከ 20 ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስራት ወይም
- ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን መጥለፍ (መስረቅ) አንቀጽ 589 ሲሆን ከ10 ዓመት እስከ 25 ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ አስራት ያስቀጣል፡፡
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ ጠለፋ በአብዛኛው በገጠር አልፎ አልፎ በከተማ አካባቢ ሊፈፀም የሚችል የወንጀል ኃላፊነትን የሚያስከትል ድርጊት በመሆኑ መንግሥት ከሚያደርገው የሕግ ጥበቃ ጎን ለጎን ዜጎች ድርጊቱ በሰው ነጻነት አለፍ ሲልም ህይወት እና አካል ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት በመገንዘብ ድርጊቱ እንዳይፈጸም የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይኖርበቸዋል፡፡
በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ