ገንዘብ በአንድ ሀገር ውስጥ ህጋዊ መገበያያ ሰነድ ነው፡፡ ሀገራት የገንዘብ ኖታቸውን የመወሰን ሉአላዊ ሥልጣን ያላቸው በመሆኑ አገራችንን ጨምሮ ሀገራት የመገበያያ ገንዘባቸውን ይወስናሉ፡፡ በሀገራችን ብር ህጋዊ ገንዘብ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ ስለሀገራችን ህጋዊ ገንዘብ እና በገንዘብ ላይ ስለሚፈፀሙ ወንጀሎች እንመለከታለን፡፡
ህጋዊ የገንዘብ ኖት
ህጋዊ የገንዘብ ኖትን በተመለከተ በብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ አዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀጽ 17(1) መሠረት የኢትዮጵያ ህጋዊ የገንዘብ መደብ ብር እንደሆነ እና ይኸውም የሀገሪቱ ህጋዊ ገንዘብ እንደሆነ ድንግጎ ይገኛል፡፡ የዚህ ህጋዊ መገበያያ ኖት ስም በአገር አቀፍ ደረጃ “ብር” ተብሎ የተሰየመ ሲሆን በአለምአቀፍ ደረጃ ዒቲቢ(ETB) ተብሎ በዚሁ አዋጅ ተሰይሟል፡፡ ህጉ ከብር ውጪ ሳንቲሞችንም እንዲሁ እውቅና ሰጥቷል፡፡
ብሔራዊ ባንክ በተለየ ሁኔታ በፈቀደው አግባብ ካልሆነ በስተቀር በአገራችን ውስጥ የሚደረግ ማናቸውም የገንዘብ ስምምነቶች እና ውሎች በብር እንደተፈጸሙ ይቀቆጠራል፡፡ ይህ ማለት ገንዘብን በተመለከተ የሚደረግ ስምምነት በአገር ውስጥ ሲደረግ የግዴታ በብር መደረግ አለበት ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውጨ በሌላ አገር ምንዛሬ ለማከናወን የግድ ብሔራዊ ባንክ ሊፈቅድ ይገባል ማለት ነው፡፡ ይህ ፍቃድም በልዩ ሁኔታ በጥብቅ መስፈርት የሚሰጥ መሆኑን ከህጉ ንባብ እና አንድምታ መረዳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን አገራችን ተቀብላ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና በሌላ የአገራችን ሕግ ከዚህ በተለየ ሁኔታ ግንኙቶች በሌላ የገንዘብ ኖት እንዲደረጉ በግልጽ በተደነገገ ጊዜ ገንዘብ ነክ ውሎች ወይም ግንኘነቶች በዓለም ዓቀፍ ህጉ ወይም በግልፅ በደነገገው ሕግ ወይም ብሔራዊ ባንክ ባዘዘው መሠረት በሚፈቀድ የገንዘብ ኖት ሊመዘገብ ይችላል፡፡
ህጋዊ ገንዘብን የመወሰን እና የማሳተም ሥልጣን
በኢ.ፌ.ድ.ሪ ህገመንግሥት አንቀጽ 51 ንዑስ አንቀጽ 7 መሠረት ብሔራዊ ባንክን የማስተዳደር፣ ገንዘብ ማተም፣ መበደር እና የውጭ ምንዛሬን መቆጣጠር የፌደራል መንግሥት ሥልጣን እና ኃላፊነት እንደሆነ ተደንጓል፡፡ በፌደራል መንግሥት ደረጃ ሥልጣን እና አወቃቀር መሠረት እነዚህን ብሮች እና ሳንቲሞች የመቅረጽ፣ የማተም፣ የማስቀረጽ፣ የማሳተም፣ የማሰራጨት፣ የማስወገድ እና እንዲወገዱ የማድረግ ብቸኛ ሥልጣን ያለው ብሔራዊ ባንክ እንደሆን በብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ አዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 መረዳት ይቻላል፡፡ በእነዚህ ህጋዊ ገንዘቦች ላይ የሚጻፈውን ጽሑፍ፣ የኖቶቹ ስፋት፣ ቅርጽ እና መደባቸው እንዲሁም ሌሎች ልዩ ልዩ ጉዳየች በብሔራዊ ባንክ እንደሚወሰን የአዋጁ አንቀጽ 18 ያመለክታል፡፡
የወንጀል ተጠያቂነት የሚስከትሉ የወንጀሎች ድርጊቶች
ህጋዊ የገንዘብ ኖቶችን በተመለከተ የኢ.ፌ.ድ.ሪ የወንጀል ሕግ ከአንቀጽ 356 ጀምሮ እስከ አንቀጽ 362 አስቀጪ የሆኑ የወንጀል ድርጊቶች እና የሚያስቀጠቱን የቅጣት መጠን ደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚሁም መሠረት በህጉ አንቀጽ 356 መሠረት ህጋዊ መገበያያ የሆኑትን ገንዘቦች ያለ ፍቃድ መሥራት ወይም አስመስሎ መሥራት ከ5 ዓመት በማያንስ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ የወንጀል ድርጊት ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በአንቀጽ 357 መሠረት ህጋዊ ገንዘቦችን ከትክክለኛ ዋጋቸው በላይ እንዲዘዋወሩ ለማድረግ በማሰሰብ መልካቸውን መለወጥ፣ እውነተኛ መልካቸው ላይ ሌላ ነገርን መጨመር፣ ቀለማቸውን መለወጥ ወይም በሌላ ማናቸውም አይነት ዘዴን በመጠቀም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ወደሀሰተኛነት መለወጥ ከ15 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ያስቀጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአንቀጽ 358 መሠረት በኬሚካል፣ በፊዚካል፣ መካኒካል ወይም ማናቸውንም ዘዴ ተጠቅሞ ህጋዊ የሆኑትን ገንዘቦች ዋጋቸውን ዝቅ እንዲል ማድረግ ከ10 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ያስቀጣል፡፡ ይህ ወንጀል በአገራች ውስጥም ሆነ በውጪ አገር ቢፈፀም የሚያስቀጣ ነው፡፡
ወደ አገር ከማስገባት ጋር ተያይዞ ሀሰተኛ የሆኑ ወይም ዋጋቸው ዝቅ እንዲል የተደረጉ ገንዘቦችን እውነተኛ እንደሆኑ ወይም ሙሉ ዋጋቸውን እንደያዙ አስመስሎ ራሱ እንዲገበያይባቸው ወይም እንዲዘዋወሩ ለማድረግ በማሰብ ወደ አገር ውስጥ ማስገባትም ሆነ ከአገር ማስወጣት እንዲሁም ይዞ መገኘት፣ ማስቀመጥና ማቅረብም ጭምር ከ15 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ያስቀጣል፡፡ እነዚህ በገንዘብ ኖቶች ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች ከተፈጸሙ ህጉ ድርጊቱ የተፈጸመው ገንዘቦቹን ለማዘዋወር እንደሆነ ግምት ይወስዳል፡፡
ማዘዋወርንም በተመለከተ በአንቀጽ 361 ላይ እንደተደነገገው ሀሰተኛ የሆኑትን ወይም ወደ ሐሰት የተለወጡትን ገንዘቦች እውነተኛ አስመስሎ ወይም ከተወሰነው በላይ ዋጋ እንዳላቸው አስመስሎ በኢትዮጵያ ውስጥ ወይም ከአገር ውጭ ማዘዋወር ከ10 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ያስቀጣል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 እንደተገለጸው ዋጋቸው የተቀነሰውን ገንዘቦች ሙሉ ዋጋ እንደያዙ አስመስሎ ማዘዋወር ከ5 ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም በገንዘብ መቀጮ የሚያስቀጣ ወንጀል ነው፡፡ ወንጀል አድራጊው ገንዘቡን እውነተኛ ነው በሚል እምነት ወይም በትክክለኛ ዋጋው ከተቀበለ በኋላ ሀሰተኛ መሆኑን ወይም ዋጋው መቀነሱን እያወቀ ከኪሳራ ለመዳን ሀሰተኛውን ወይም ወደ ሐሰት የተለወጠውን ገንዘብ ያዘዋወረ እንደሆነ በቀላል አስራት ይቀጣል፡፡ በተጨማሪም ዋጋው የተቀነሰውን ገንዘብ ሙሉ ዋጋው እንዳለ በማስመሰል ያዘዋወረ እንደሆነ በመቀጮ የሚቀጣ ይሆናል።
በወንጀል ህጉ አንቀጽ 362 መሠረት ከላይ የተገለጹት ወንጀሎች የተፈጸሙበት የገንዘብ መጠን ማነሱ ከወንጀል ተጠያቂነት ያስመልጥም፡፡ ይልቁንም ህጉ ባስቀመጠው መሠረት የገንዘቡ መጠን ትንሽ ከሆነ ቅጣቱ ቀላል እስራት ይሆናል፡፡
ገንዘቦችን አስመስሎ መሥራትን ስናይ ወንጀል ፈፃሚው የማታለል ሀሳብ ባይኖረውም ገንዘቦችን በማስመሰል መሥራት፣ በሚያሳሳት መልኩ አምሳያ ሆነው እንዲዘዋወሩ በማስታወቂያነት አስመስሎ ማወጣት ድርጊቱ የማሳሳት አደጋ የሚፈጥር ወይም ለመፍጠር የሚችል ከሆነ እንዲሁም እነዚህኑ መስለው የተሰሩትን ገንዘቦች ወደ አገር ማስገባት፣ ከአገር ማስወጣት፣ በአደራ በቀበል፣ ለሽያጭ ወይም በስጦታ ማቅረብ ወይም እንዲዘዋወሩ ማድረግ በህጉ አንቀጽ 369 መሠረት በመቀጮ ወይም ከሶስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት ያስቀጣል፡፡ እነዚህን የሐሰት ገንዘቦች ከመሥራት ጋር በተገናኘ ሌላው መታወቅ ያለበት ነገር ማንም ሰው አግባብ ያለው ባለሥልጣን በግልፅ ሳያዘው ለገንዘብ ማተሚያ ወይም መስሪያነት የሚያገለግሉትን መሳሪያዎች ፎርሞች፣ ከውሮች ወረቀቶች፣ ሞዴሎች እና መሰል እቃዎች የሰራ፣ በእጁ ያስገባ፣ ወደ አገር ያስገባ ወይም ያስወጣ፣ ለሌላ ሰው ያቀረበ ወይም አሳልፎ የሰጠ እንደሆነ እንዲሁም እነዚህ ገንዘቦች እንዲሰሩ የሚሰጡ ትእዛዞችን የተቀበል፣ የፈጸመ፣ ያስፈጸመ፣ ለሌላ ሰው ያስረከበ እንደሆነ በህጉ አንቀጽ 370 መሠረት በቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል፡፡
ከላይ በአዋጅ ቁጥር 591/2000 መሠረት እንዳየነው የሀገሪቱ መገበያ ብር ነው፡፡ ይሄንን ህጋዊ ገንዘብ በቂ ምክንያት ሳይኖረው አልቀበልም ማለት ወንጀል እንደሆነ ስለ ደንብ መተላለፍ በደነገገው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 778 ደንግጎ ይገኛል፡፡ ቅጣቱም በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እስራት ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በአንቀጽ 779 መሠረት በሐሰት የተዘጋጀ ወይም ወደ ሐሰት የተለወጠ ገንዘብ በእጁ የገባ ሰው ገንዘቡ የመጣበትን ሁኔታ ካወቀ ይሄንኑ ወይም የሐሰት ገንዘቡ በእጁ የሚገኝ መሆኑን ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ሳይዘገይ ካላስታስታወቀ እና ገንዘቡን ካላስረከበ በመቀጮ ወይም ማረፊያ ቤት እስራት የሚቀጣ ይሆናል፡፡
በጥቅሉ ህጋዊ ገንዘቦችን የማዘጋጀት፣ ማሳተም እና ወደ ገበያው ማስገባት እንዲሁም አስፈላጊ ሲሆን ከገበያው ማስወጣት እና ማስወገድ የብሔራዊ ባንክ ሥልጣን እና ኃላፊነት ሲሆን በእነዚሁ ህጋዊ ገንዘቦች ገጽታ፣ በገንዘቦች ላይ የሚጻፈውን ነገር፣ የኖቶቹ ስፋት፣ ቅርጽ እና መደባቸው እንዲሁም ሌሎች ልዩ ልዩ ጉዳዮች መወሰን የብሔራዊ ባንክ ኃላፊነት ብቻ ነው፡፡ ይህ ታውቆ ተጠቃሚዎች እና ሰፊው ማኅበረሰብ ብሔራዊ ባንኩ ባወጣው እና በየጊዜው በሚሰጣቸው መመሪያዎች መሠረት የብር ኖቶቹን በአግባቡ መያዝና መጠቀም እንዲሁም ከገንዘብ ኖቶች ጋር በተያያዘ ከሚፈፀሙ ወንጀሎች መቆጠብ ይጠበቅበታል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ