የሕብረት ሥራ ማኅበራት በኢትዮጵያ

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

አብዛኛው የሀገራችን ሕዝብ ኑሮውን መሠረት ያደረገው በግብርና ነው፡፡ ይህ የኑሮ ዘዴ አጋዥ የሆነ አሠራር እና ሥርዓት እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልገዋል፡፡ ህዝቡ የራሱን የልማት ተግባር ለማከናወን ግንባር ቀደም ተዋናይ የሚሆንበት አደረጃጀት መኖር ያስፈልገዋል፡፡ የሕብረት ሥራ ማኅበራት በዚህ በኩል ዋና አማራጭ በመሆን የህብረተሰቡን ተሳትፎ የሚያጎለብቱ መድረኮች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የሕብረት ሥራ ማኅበራትን በዘመናዊ መልኩ ማደራጀት ከተጀመረ 57 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በመሆኑም የሕብረት ስራ ማኅበራት በአገራችን ፈጣን፣ ቀጣይና ፍትሐዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማትና ዕድገት ከማረጋገጥና የአባላትን ብሎም የሕዝብን ተጠቃሚነት ከማሳደግ አንፃር ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ያከናውናሉ፡፡ በዚህም በከተማ እና በገጠር ለሚኖረው የህብረተሰብ ክፍል በርካታ ጠቀሜታዎች ይሰጣሉ።

የሕብረት ሥራ ማኅበራት የአምራቹንና የሸማቹን ህብረተሰብ በምርትና አገልግሎት በማስተሳሰር ለተጠቃሚው ጥራት ያለውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ በተፈለገ ጊዜና ቦታ ለማቅረብ የሚረዳ፣ የሸማቹን መብትና ፍላጎት የሚያስጠብቁ፣ አምራቹም የሚያመርተው ምርት ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ የሚያስችሉ ድርጅቶች ናቸው፡፡ የፌዴራል ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ የሕብረት ሥራ ማኅበራትን እንቅስቃሴ የማጎልበት፣ የሰው ኃይል የማሰልጠን፣ ጥናትና ምርምር የማካሄድ ተግባር በሕብረት ሥራ ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 985/2008 የተሰጠው የመንግሥት መስሪያ ቤት ነው፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ የሕብረት ሥራ ጽንሰ ሀሳብ፣ የሕብረት ሥራ ማኅበር ምንነት፣ የሕብረት ሥራ ማኅበራት አስፈላጊነት እና መርሆች እንዲሁም የሕብረት ሥራ ማኅበራት ዓይነቶች የሚሉትን እንመለከታለን።

የሕብረት ሥራ ጽንሰ ሀሳብ

የሕብረት ሥራ የሚለውን ፅንሰ ሀሳብ ለማየት ሕብረት የሚለውን ትርጓሜ በቅድሚያ እንመልከት፡፡ ሕብረት ማለት የተዋሐደ (አንድነት)፣ ለአንድ ዓላማ ወይም ለአንድ ውጤት የተሰለፈ እና ወደ አንድ አቅጣጫ የሚያመራ የጋራ ጥረት ነው፡፡ በሕብረት ውስጥ የጋራ ምኞት ወይም የጋራ ፍላጎት አለ፡፡ የሕብረትን ጽንሰ ሀሳብ በቀላሉ ለመረዳት ሕብረት የፍላጎት አንድነትና ፍላጎትን ለማሟላት የተግባር ውህደትን (አንድነትን) የሚያመለክት ቃል ነው፡፡ ሕብረት የቃሉ ትርጉም በውስጡ መተባበርን፣ መረዳዳትን፣ መደጋገፍን እና አንድነትን ወዘተ… ይገልፃል። ሰዎች በጋራ የሚከወኑ ጉዳዮችን በጋራ የኃላፊነት መንፈስ በመተጋገዝና በመረዳዳት በቀላሉ ሲያሳኩና ሲፈጽሙ ኖረዋል፡፡ ይህ በአንድነትና በጋራ የመሥራት ሁኔታ በሀገራችን፣ በአፍሪካና በዓለም ላይ የሰዎች አኗኗር ገጽታ ወይም ዘዴ ነው፡፡ በሕብረት ውስጥ እያንዳንዱ ከሌላው በአጠቃላይም ከሕብረቱ የሚያገኘው ጥቅም አለ። ይህም እየሰፋና እየተለቀ ሲሄድ የጋራ የሆኑ ፍላጎቶችና ምኞቶች እየጎሉ ይወጣሉ፡፡

እነዚህን የጋራ ፍላጎቶችና ምኞቶችን ለማሳካት እያንዳንዱ በፍላጎትና በተነሳሽነት የሚጠበቅበትን ይወጣል። ስለዚህ በተናጠል ሊወጣቸው የማይችላቸውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ከሌሎች ተመሳሳይ ችግር ካላቸው ሰዎች ጋር በመሆን ለመፍታት ሕብረት አስፈላጊ ነው። በርግጥ የሕብረት ሥራ በብዛት በምናውቃቸው በእርሻ፣ በሀዘን፣ ወይም በሠርግ ተግባራት ብቻ የተወሰነ አይደለም። ይልቁንም በቅርብ ዘመናት በዘመናዊ የህብረተሰብ አኗኗር ውስጥ ሰዎች ልዩ ልዩ ኢኮኖሚያዊ (ምጣኔ ሀብታዊ) ችግሮቻቸውን ለመፍታት በሕግና ሥርዓት የሚመሩና የሚሰሩባቸው የንግድ ድርጅቶች፣ የማኅበር ቤቶችን እና የመሳሳሉትን መስርተዋል።

እንዲህ ዓይነት በማኅበር የመሥራት ዘዴ በፋብሪካና በማዕድን ሥራ ውስጥ በሚሰሩ ሰዎች ዘንድም የተለመደ ነው። ሠራተኞች ገንዘባቸውን (ደመወዝ) ወደ አንድ ቦታ በማሰባሰብ የገንዘብ ቁጠባና ብድር አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት በማቋቋም የሚሰሩበት መስሪያ ቤት ከደመወዛቸው በቋሚነት በየወሩ እየቀነሰ በአቋቋሙት የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ሕብረት ሥራ ማኅበር እንዲቆጠብላቸው ያደርጋሉ።

የገንዘቡ ክምችት ሲያድግ እርስ በእርስ በመበዳደር በግላቸው በደመወዛቸው ብቻ ሊያሳኩት የማይችሉትን ጉዳያቸውን በቀላሉ ያሟላሉ። እንዲህ ዓይነት የመደራጀት እንቅስቃሴ የገበያ እጥረት ባለባቸው ሁኔታዎች የከተማ ነዋሪዎች ዘንድም የተለመደ ነው።

እጅ ለእጅ በመያያዝ የንግድ እንቅስቃሴውን ሁኔታ የሚወስኑበት የሚፈልጉትን ሸቀጣሸቀጥ (አገልግሎት) በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛት የሚችሉበት የሸማቾች የሕብረት ሥራ ማኅበራትን በማቋቋም እየሰሩ ይገኛሉ።

የሕብረት ሥራ ማኅበር ምንነት

የሕብረት ሥራ ማኅበራት ራሳቸውን ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ለማጣጣም ከሚያደርጉት ተለዋዋጭነት ባህሪያቸው አንፃር ለሁሉም የሕብረት ስራ ማኅበራት በእኩል የሚያገለግል ወጥና አጠቃላይ የሆነ ትርጉም መስጠት በጣም አስቸጋሪና የማይቻል ነው። ይሁን እንጂ ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት እና ዓለምአቀፍ የሕብረት ሥራ ማኅበራት ቃል ኪዳን በብዛት የተለመደውን ድርጅታዊ አወቃቀርና መሠረታዊ ባህሪያት እንዲያንፀባርቅ አድርገው ለኅብረት ሥራ የሰጡት ትርጉም ተቀባይነት አለው።

ዓለምአቀፍ የሥራ ድርጅት (እ.ኤ.አ 1919)

“የሕብረት ሥራ ማኅበር ማለት በአባላት ከፍተኛ ተሳትፎ ተመጣጣኝ ካፒታል አውጥተው በዲሞክራሲያዊ ሁኔታ የሚቆጣጠሩበት እና ትርፍና ኪሳራን በፍትሐዊ መንገድ የሚከፋፈሉበት በድርጅታቸው አማካይነት የጋራ ግባቸውን ለማሳካት በፈቃደኝነት የተገናኙ የሰዎቸ ስብስብ ነው፡፡”

ዓለምአቀፍ የሕብረት ሥራ ቃል ኪዳን (እ.ኤ.አ 1895)

“የሕብረት ሥራ ማኅበር ማለት በጋራ በባለቤትነት በዲሞክራሲያዊ መንገድ በሚቆጣጠሩት ድርጅታቸው አማካይነት የጋራ ማኅበራዊ ምጣኔ ሀብታዊ ፍላጎታቸውን ለማርካት በፍቃደኝነት የተገናኙበት ራስገዝ የሆነ የሰዎች ስብስብ ነው።”

በእነዚህ ዓለምአቀፍ የስራ ድርጅት እና ዓለምአቀፍ የሕብረት ሥራ ቃልኪዳን ድርጅት ባስቀመጧቸው ትርጉሞች ውስጥ ዋና ዋና ሀሳቦች የሚከተሉት ናቸው።

  • ፍቃደኝነት፡- ማንኛውም የሕብረት ሥራ ማኅበር በአባላቱ ሙሉ ፈቃደኝነት ብቻ መቋቋም እንዳለበትና ከዚህ ውጪ ሰዎች ማኅበር እንዲያቋቁሙ ጫና የሚደረግባቸው ከሆነ መርህን የሳተ እንደሚሆን ያስገነዝበናል።
  • የጋራ (ተመሳሳይ) ፍላጎት፡- አባላት በአንድ ማኅበር መታቀፍ መሠረቱ የጋራና በአንድ ላይ የሚያስተሳስር ፍላጎት ወይም ችግር መኖር እንደሆነ እና የተለያዩ ፍላጎቶችና ችግሮች ያላቸውን ሰዎች በአንድ ማኅበር ማቀፍ ዘላቂነት እንደሚኖረው ያስረዳል።
  • ዲሞክራሲያዊ ቁጥጥር፡- ሕብረት ስራ ማኅበራት በአባላት ባለቤትነትና ፍላጎት የተመሰረቱ እንደመሆናቸው እያንዳንዱ አባል አንድ ድምፅ ብቻ ይዞ በሚገኝበት ጠቅላላ ጉባዔ በበላይነት ይመራል፣ ይቆጣጠራል፣ የዕለት ተዕለት ተግባሮችንም በተመረጡ ኮሚቴዎች እንዲፈፀሙ ያደርጋል። በሕብረት ሥራ ማኅበራት ውስጥ አንድ ሰው አንድ ድምፅ ብቻ ያለው ሲሆን የካፒታል መጠንን መሠረት አድርጎ ድምፅ አይሰጥም።
  • ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ (ምጣኔ ሀብታዊ) ድርጅት፡- የሕብረት ስራ ማኅበራት ዋነኛ ዓላማ የአባላትን ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች በማስወገድ የኑሮ ደረጃቸውን ማሻሻል ነው። ለዚህም ተግባራቸው አባላት ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ሀብታቸውን በማቀናጀት ለበለጠ ዕድገት ይጥራሉ። በዚህ ጥረት በሰዎች ላይ በተናጠል ይደርስ የነበረውን ኪሳራ ዝቅ ለማድርግ ትርፍ ከፍተኛ እንዲሆን በማድርግ የአባላት የግልና የጋራ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ችግሮች እንዲፈቱ ብልጽግና እንዲኖር የማድርግ ሚና ስለሚጫወቱ ማኅበራቱ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ድርጅቶች ይባላሉ።

በሀገራችን ሕግ መሠረት የሕብረት ሥራ ማኅበራት የሚመለከተው የሕብረት ሥራ ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 985/2009 አንቀጽ 2(1) ሲሆን በዚህም መሠረት “የሕብረት ሥራ ማኅበር” ማለት ሰዎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ሌሎች የጋራ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት እና በተናጠል ሊፈቱ ያልቻሏቸውን ችግሮች በጋራ ለማቃለል ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው ሰዎች በፈቃደኝነት የሚያቋቁሙት፣ በጋራ ባለቤትነት የሚያስተዳድሩት፣ በሕብረት ሥራ ማኅበራት መርህ መሠረት የሚመሩትና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚቆጣጠሩት ራሱን የቻለ ህጋዊ ሰውነት ያለው የሕብረት ሥራ ማኅበር ነው፡፡” የሕብረት ሥራ ማኅበራት የአባላትን የማምረት አቅም በማሳደግ ወይም ለአባላት የሥራ ዕድል በመፍጠር የአባላትን ምርትና ገቢ ለመጨመር በአባላት ሙሉ ፍላጎት የሚቋቋሙና ሰፊውን የህብረተሰብ ክፍል የሚያሣትፉ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ተቋማት ናቸው፡፡

ጃፓን፣ ኦስትሪያ፣ ታይላንድ፣ ማሌዢያና አውሮፓ… ለሕብረት ስራ ማኅበራት የድጋፍ ማእቀፎች አሏቸው፡፡ የፋይናንስ ችግርን ለመፍታት የተለየ ባንክ፣ የተለየ የፖሊሲ ማዕቀፍ አላቸው፡፡ ለምሳሌ ደቡብ ኮሪያ ሦስት አይነት ባንክ አላት፡- ንግድ ባንክ፣ ሕብረት ስራ ባንክና ፖሊሲ ባንክ ናቸው፡፡ የትኛውም ማኅበር የገንዘብ እጥረት ሲገጥመው ቢዝነስ ፕላን አቅርቦ ብድር ያገኛል፡፡ የሚሰራበት ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ከግብር ነፃ ነው፡፡ ሌላም ሌላም፡፡ አውሮፓና አሜሪካ እንደ ሀገር የፋይናንስ ችግር ሲገጥማቸው የሕብረት ስራ ማኅበራቶቻቸው ግን ሳይነኩ ወጥተዋል፡፡ ጃፓን ግብርናዋ የሚመራው በኅብረት ስራ ነው፡፡

በሀገራችን የሕብረት ስራ ማኅበራትን ለማደራጀት አምስት የተለያዩ አዋጆች፣ አንድ የማሻሻያ አዋጅና አንድ ደንብ ከመውጣቱም በተጨማሪ ሀገራችን ከምትከተለው ፌዴራላዊ አወቃቀር አንፃር የሕብረት ስራ እንቅስቃሴን በአንድ ጥላ ስር ለመምራት በፌዴራል ደረጃ የማደራጀት፣ የመመዝገብ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ሥልጠና፣ ምርምር እና ሌሎች የሙያና የቴክኒክ ድጋፎችን እንዲያገኙ የሚያስችል የፌዴራል ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ እንዲሁም በሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች እስከ ወረዳ ቢሮዎችና ጽ/ቤቶች ደረጃ የሕብረት ስራ ማኅበራት ማስፋፊያና ማደራጃ ተቋማት እንዲቋቋሙ ተደርጓል፡፡

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወጣው አዋጅ ቁጥር 274/1994 (እንደተሻሻለው) የሕብረት ስራ ኮሚሽን ግንቦት 6 ቀን 1994 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በ1998 ዓ.ም የአስፈፃሚ አካላትን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ መጠሪያ ስሙ ኮሚሽን መሆኑ ቀርቶ የፌዴራል ሕብረት ስራ ኤጀንሲ ተብሎ ይጠራ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ኮሚሽን ሆኖ ተደራጅቷል፡፡ የፌዴራል ሕብረት ሥራ ኮሚሽን በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ለሕብረት ሥራ ማኅበራት ዕድገት የሚበጁ ፕሮጀክቶችንና ፕሮግራሞችን በማጥናትና በማዘጋጀት እንደ አስፈላጊነቱ ከክልሎች ጋር በመተጋገዝ ማኅበራት ድጋፍ የሚያገኙበትን መንገድ ያመቻቻል፡፡ በዚህም መሠረት የአነስተኛ የገጠር ፋይናንስ ተቋማት ማስፋፊያ ፕሮግራም (Rural Financial Intermediation Program) ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ ለሰባት ዓመታት ፕሮግራም ተይዞለት እየተሰራ የነበረ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ሁለት ፕሮጀክቶች ማለትም የአርብቶ አደር ማኅበረሰብ ልማት ፕሮጀክት እና የቤተሰብ ጥሪት ግንባታ ፕሮግራም ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ዓመታት በመንቀሳቀስ ላይ የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ጊዜም የሕብረት ሥራ ማኅበራት ኃላፊነታቸው የተወሰነ በመሆኑ እና ከመንግሥት ድጋፍ ስለሚደረግላቸው ተመራጭ ሆነው የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

በሕብረት ሥራ ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 985/2009 መሠረት ማኅበራትን ለመደገፍና ለመከታተል እንደገና ተደራጅቷል፡፡ በአንቀጽ 9 መሠረት ማንኛውም የሕብረት ሥራ ማኅበር መጠሪያ ስም እንዲኖረው የሚጠበቅ ሲሆን፣ የስም አወጣጡም ምክንያታዊ፣ ሕግንና የሕዝብን ሞራል የማይቃረን መሆን አለበት፡፡ ከማንኛውም የሕብረት ሥራ ማኅበር ስም መጨረሻ “ኃላፊነቱ የተወሰነ የሕብረት ሥራ ማኅበር” የሚል ሐረግ መፃፍ ይኖርበታል፡፡

የሕብረት ሥራ ማኅበራት አስፈላጊነት እና መርሆች

አስፈላጊነት

ለሕብረት ሥራ ማኅበራት አስፈላጊነት ዋናዋና ምክንያቶች፡-

  • የሕብረት ሥራ ማኅበራት የህብረተሰቡ ድርጅት ሆነው ስለሚንቀሳቀሱ፣
  • ሕብረት ሥራ ማኅበራት ዲሞክራሲዊ አሠራርን በትክክል ተግባራዊ ስለሚያደርጉ፣ ወይም እንዲያደርጉ ስለሚጠበቅባቸው፣
  • የሕበረት ሥራ ማኅበራት የነፃ ገበያ ሥርዓት ስለሚያሳድጉ፣
  • ሕብረት ሥራ ማኅበራት የሰውን ልጅ ህይወት ስለሚለውጡ (ክብር ስለሚሰጡ)፣
  • ሕብረት ሥራ ማኅበራት የልማት አንቀሳቃሽ ሞተሮች ሰለሆኑ ናቸው፡፡

መርሆች

የሕብረት ሥራ ማኅበራት መርሆች በውስጣቸው የያዟቸውን የሕብረት ሥራ ዕሴቶች የሚተረጉሙባቸው የባህሪ ወይም የሥነምግባር መመሪያዎች ናቸው፡፡ የሕብረት ሥራ መርሆች መነሻ እ.ኤ.አ በ1844 በእንግለዝ ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ በሮችዴል ከተቋቋመው የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማኅበር ይጀምራል። ይህም በየደረጃው በተለያየ ጊዜ ሲሻሻል ቆይቶ እ.ኤ.አ በ1995 የማንችስተር ስቲ በእንግሊዝ ሀገር የዓለምአቀፍ የሕብረት ሥራ ማኅበራት ቃል ኪዳን 7 (ሰባት) የተሻሻሉ መርሆችን አጽድቋል፡፡ እነሱም ዝርዝራቸው የሚከተሉት ናቸው፡-

  • አባልነት ክፍትና በፈቃደኝነት መሆን፣
  • የአባላት ዴሞክራሲያዊ ቁጥጥር፣
  • የአባላት ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ፣
  • ነፃና ራስ በራስ ማስተዳደር፣
  • ትምህርት፣ ሥልጠና እና መረጃ መስጠት፣
  • ከሌሎች አቻ ሕብረት ሥራ ማኅበራት ጋር ሕብረት መፍጠር፣
  • ማኅበራዊ ኃላፊነት ወይም ለአካባቢ ዘላቂ ልማት ጥረት ማድረግ የሚሉት ናቸው።

የሕብረት ሥራ ማኅበራት ዓይነቶች

የሕብረት ሥራ ማኅበር ምርት የማምረት ወይም አገልግሎት የመስጠት ወይም ምርት የማምረት እና አገልግሎት የመስጠት ሁለገብ ተግባር አጣምሮ የሚያከናውን ሆኖ ሊመሠረት ይችላል፡፡ የሕብረት ስራ ማኅበራት በተለያየ የአደረጃጀት እርከን ተደራጅተዋል (አዋጅ ቁጥር 985/2009)፡፡ የመጀመሪያው እርከን መሠረታዊ የሕብረት ስራ ማኅበር የሚባል ሲሆን፤ ሁለተኛው የሕብረት ስራ ማኅበራት አደረጃጀት እርከን የሕብረት ስራ ሕብረት /ዩኒዪን/ ነው፡፡ ይህም ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ተመሳሳይ ዓላማ እና ተግባር ያላቸው መሠረታዊ የሕብረት ስራ ማኅበራት የሚያቋቁሙት የሕብረት ስራ ማኅበር ነው፡፡ ሶስተኛው እርከን ፌዴሬሽን በመባል የሚታወቅ ሲሆን ሁለት ወይም ከሁለት በላይ በሆኑ ተመሳሳይ ዓላማና ተግባር ባላቸው ዩኒየኖች ይመሰረታል፡፡ አራተኛው እርከን ሊግ ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚመሠረት ነው፡፡

በአጠቃላይ የሰው ልጅ ተፈጥሮን ለኑሮው አመች ለማድርግ፣ የኑሮ ደረጃውን ለማሳደግና ፍላጎቱን ለማርካት በተናጠል ሳይሆን በሕብረት ሥራ መንቀሳቀስ ይጠቅመዋል፡፡ የሕብረት ሥራ ማኅበራት ለአባሎቻቸው ከሚያስገኙት ጥቅም ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ግንባታ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ በሀገራቱ ጠንካራ የሕብረት ሥራ ማኅበራትን በመፍጠር ህብረተሰቡን ዘላቂና አስተማማኝ የልማት ተሳታፊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ