በጋብቻ ላይ ጋብቻ መፈፀም እና የአመንዝራነት ወንጀል

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

ቤተሰብ የማሕበረሰብም ሆነ የሀገር መሠረት ስለመሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ጋብቻ የቤተሰብ መመስረቻ ዋነኛ መንገድ በመሆኑ በኃይማኖት እምነቶች፣ በማሕበረሰቡም ሆነ በሕግ እውቅናና ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ ሆኖም በጋብቻ ላይ ጋብቻ መፈፀም በሕብረተሰቡ ውስጥ የሚስተዋል ተግባር በመሆኑ በአድራጊዎቹ ግለሰቦች፣ በትዳር አጋሮችም ሆነ በማህበረሰቡ ዘንድ የራሱ ተፅእኖ እና ውጤት ይኖራል፡፡ በዚህ አጭር የንቃተ ሕግ ፅሑፍ ስለ ጋብቻ ምንነት፣ በጋብቻ ላይ ጋብቻ መመስረት ምንነት እና የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት እንዲሁም ስለአመንዝራነት በመጠኑ የምንዳስስ ይሆናል፡፡

የጋብቻ እና በጋብቻ ላይ ጋብቻ ምንነት

ጋብቻም ሆነ በጋብቻ ላይ ጋብቻ መፈፀም በሕግ በተለይም በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ በቀጥታ ትርጉም ተሰጥቶት አይገኝም፡፡ ሆኖም ከአጠቃላይ የሕጉ ድንጋጌዎች ተነስተን መግለፁ የሚከብድ አይሆንም፡፡ በመሆኑም ጋብቻ ማለት አንዲት ሴት እና አንድ ወንድ በመፈቃቀድ ህጉ የሚጠይቃቸውን መስፈርቶች በማሟላት በመረጡት የጋብቻ ስርዓት ጋብቻ ፈፅመው አብረው ለመኖር የሚያደርጉት ስምምነት መሆኑን መረዳት እንችላለን፡፡ በተጨማሪም በህጉ ውስጥ “አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ” የሚለው ሀረግ እንደሌሎች ሀገሮች በተመሳሳይ ጾታ መካከል የሚደረግ ጋብቻ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን እንረዳለን፡፡ ይልቁንም በወንጀል ህጋችን እንደተደነገገው በተመሳሳይ ጾታ መካከል የሚደረግ ጾታዊ ግንኙነት የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በመረጡት ሥርዓት ሲባል ጋብቻ የሚፈፀምባቸው በሕጉ እውቅና የተሰጣቸው ማለትም በክብር መዝገብ ሹም ፊት የሚፈፀም ጋብቻ፣ በኃይማኖት እና በባህል የሚፈፀም ጋብቻ ተብለው የሚታወቁ ሦስት ዓይነት የጋብቻ አፈፃፀም ሥርዓቶች ስላላሉ ይህን ለማመልከት ነው፡፡

በጋብቻ ላይ ጋብቻ መፈፀም ማለት ደግሞ አስቀድሞ የተፈፀመ ጋብቻ ፀንቶ ባለበት ሁኔታ (ሳይፈርስ) ሌላ ጋብቻ መፈፀም እንደሆነ ከቤተሰብ ህጉ ከአንቀጽ 11 ላይ መረዳት እንችላለን፡፡

በጋብቻ ላይ ጋብቻ መፈፀም ስለመከልከሉ

በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 11 መሠረት በጋብቻ ላይ ጋብቻ መፈፀም የተከለከለ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም አስቀድሞ የተፈፀመው ሕጋዊ ጋብቻ ፀንቶ ባለበት ጊዜ ከሌላ ከማንም ሰው ጋር በጋብቻ መተሳሰር አይችልም፡፡ ሰዎች በሕጋዊ ጋብቻ ከተሳሰሩ በኋላ ጋብቻቸው በተለያየ ምክንያት ላይፀና ወይም ቀጣይነቱ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡ ይህ በሚያጋጥምበት ጊዜ ከተቻለ ተጋቢዎቹ የችግሩን መንስኤ በመለየት ተነጋግረው በመፍታት የትዳራቸውን ቀጣይነት ማረጋገጥ የተሻለ ይሆናል፡፡ ይህ ካልተቻለ ግን ሕጋዊ ሂደቱን በመከተል ጋብቻው በፍቺ መፍረስ ይኖርበታል፡፡ ሕጋዊ ሂደቱን ሳይከተሉ ከእንግዲህ በሽምግልና ወይም በመካከላቸው በሚያደርጉት ስምምነት በቃ ተፋትተናል በማለት መለያየት በሕግ እንደተፋቱ ስለማይቆጠር ወደፊት በንብረት ጉዳይም ሆነ ቀጣይ በሚኖራቸው የጋብቻ ህይወት ላይ አሉታዊ ጫና ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ ቀድሞ የነበረው ጋብቻ በፍርድ ቤት እንዲፈርስ ሳይደረግ የሚመሰርቱት ሌላ ጋብቻ በጋብቻ ላይ ጋብቻ መፈፀም ስለሆነ የመፍረስ አደጋ የተጋረጠበት ከመሆኑም በላይ የወንጀል ተጠያቂነትም ያስከትላል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የተፈራ ንብረትም በጋብቻ ውስጥ የተፈራ ንብረት ተደርጎ ስለሚወሰድ የቀድሞ ተጋቢ የጋራ ንብረት ስለሚሆን ወደአልተፈለገ ክርክርና እንግልት የሚያስገባ ተግባር ነው፡፡

በልዩ ሁኔታ ግን ባህልንና ኃይማኖትን መሠረት አድርጎ በሕግ በግልፅ እውቅና ተሰጥቶ ሲገኝ በጋብቻ ላይ ጋብቻ መፈፀም የሚቻልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡

በጋብቻ ላይ ጋብቻ መፈፀም የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት

ከላይ እንደተገለፀው በጋብቻ ላይ ጋብቻ መፈፀም ከመከልከሉም በላይ የወንጀል ቅጣትንም የሚያስከትል ተግባር ነው፡፡ በወንጀል ሕጋችን በአንቀጽ 650 መሠረት ማንም ሰው አስቀድሞ በሕግ በፀና ጋብቻ ታስሮ ሳለ ይኸው ጋብቻ ከመፍረሱ ወይም ከመሻሩ በፊት ሌላ ጋብቻ የፈፀመ እንደሆነ በቀላል እስራት ይቀጣል ይላል፡፡ ነግር ግን ነገሩ በከባድ ሁኔታ ተፈፅሞ ከተገኘ በተለይም ጥፋተኛው የራሱን እውነተኛ ሁኔታ በመሰወር ከርሱ ጋራ ሁለተኛውን ጋብቻ የፈፀመውን ሰው አውቆ ያሳሳተ እንደሆነ ከ5 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣው ይሆናል፡፡ ይህ ቅጣት የሚመለከተው በዋናነት ቀድሞ ጋብቻ ውስጥ ላለ እና ሌላ ጋብቻ በመሰረተው ሰው ላይ ቢሆንም ከዚሁ ግለሰብ ጋር ሁለተኛውን ጋብቻ የፈፀመው ሰውም ጋብቻ እንዲመሠረት ያደረገው የቀድሞውን ጋብቻ መኖሩን እያወቀ ከሆነ በቀላል እስራት የሚቀጣ ይሆናል (ወንጀል ሕግ አንቀጽ 650(2))፡፡

በአንድ አንድ ማሕበረሰብ በባህል ደረጃ እንዲሁም በአንዳንድ ኃይማኖቶች መሠረት አንድ ሰው ከአንድ ጋብቻ በላይ ወይም በጋብቻ ላይ ጋብቻ እንዲፈፅም የሚፈቀድበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜ እና አግባብ ባለው ሕግ እውቅና የተሰጠ ከሆነ የወንጀል ሕጉ ቅጣት ተፈፃሚ እንደማይሆን ተደንግጓል (ወንጀል ሕግ አንቀጽ 651)፡፡ ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ሁሉንም አካታች እንዲሆን ታስቦ ነው፡፡

አመንዝራነት

አመንዝራነት ማለት ከትዳር አጋር ውጪ ከሌላ ሰው ጋር የሚደረግ የግብረ ስጋ ግንኙነት ተግባር ነው፡፡ አመንዝራነት በሕግ የተከለከለ እና የወንጀል ቅጣትንም ሊያስከትል የሚችል ተግባር ነው፡፡ በዚህም መሠረት አንድ ባለትዳር በሕግ መሠረት በፀና ጋብቻ ታስሮ ሳለ ከሌላ ሰው ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት የፈፀመ ወይም በቤቱ ውስጥ ውሽማ ያስቀመጠ እንደሆነ በተበደለው ባለትዳር የግል አቤቱታ አቅራቢነት በቀላል እስራት ወይም በመቀጮ እንደሚቀጣ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 652(1 እና 3) ስር ተደንግጓል፡፡

ይህ የአመንዝራነት ተግባር የተፈፀመው በአቤት ባዩ ገፋፊነት ወይም ስምምነት ከሆነ ወይም ከተፈፀመ በኋላም ይቅርታ አድርጎ ከነበረ ጥፋተኛው ከወንጀል ተጠያቂነት ነፃ ይሆናል፡፡

ማጠቃለያ

በኃማኖቶችም ሆነ በማሕበረሰቡ ዘንድ ክቡር የሆነውን እንዲሁም ለቤተሰብ መሠረት የሆነውን ጋብቻ ምንነትና ፋይዳ ተገንዝበን ስንገባበትም ሆነ ስንወጣ በጥንቃቄ ልንፈፅመው የሚገባን ማሕበራዊ መስተጋብር ነው፡፡ በኃይማኖት ወይም በአካባቢያዊ ባህል ከሚፈቀድባቸው ሁኔታዎች ውጪ በጋብቻ ላይ ጋብቻ መፈፀም የተከለከለና የወንጀል ቅጣትንም የሚያስከትል ተግባር ነው፡፡

አመንዝራነትም በወንጀል ሕጉ እንደወንጀል ከተፈረጁት ድርጊቶች መካከል ስለሆነም ማንኛውም ባለትዳር ሰው ከትዳር አጋሩ ውጪ ከሌሎች ጋር ግብረስጋ ግንኙነት መፈፀም በወንጀል እንደሚያስጠይቅ ተገንዝቦ እራሱን ከወንጀል ተጠያቂነት ትዳሩንም ከመፍረስ አደጋ ሊጠብቅ ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ