ሕፃናት እንደ ማንኛውም ተፈጥሮአዊ ሰው መብት ያላቸው ሲሆን በሥነ-አዕምሮአዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲሁም አካላዊ ሁኔታ ምክንያት ተጨማሪ ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸው በዓለም አቀፍና ብሔራዊ ሕግ ማዕቀፎች ተደንግጓል፡፡ በዚህ የንቃተ ሕግ ጽሑፍ በአጠቃላይ መሠረትዊ የሕፃናት መብቶች እና ሕፃናትን በተመለከተ የተደነገጉ መርሆችን ለመዳሰስ ተሞክሯ፡፡
የህፃን ትርጉም
ለሕፃንነት የሕግ ትርጓሜ መስጠትን አስፈላጊ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ዋነኛው የመብትና ግዴታ ወሰን (scope of rights and duties) ለማወቅ ስለሚያስችል ነው፡፡ እንዲሁም ሕፃናት ለአደጋ ተጋላጭ ከመሆናቸው አኳያ ልዩ ጥበቃ (special protection due to vulnerability) ስለሚያስፈልጋቸው ሕፃናትን በመለየት ይህን ጥበቃ ለማድረግ ነው፡፡
ህፃን ማን ነው ለሚለው ጥያቄ የተለያዩ አገራት ሕጎች የተለያየ ትርጓሜ ሰጥተዋል፡፡ ምንም እንኳ አንድ ወጥ የሆነ የሕፃን ትርጓሜ ባይኖርም ሕፃን የሚለው ቃል ብዙ አገራት ዕድሜን ግምት ውስጥ ያስገባ ትርጉም ይጠቀማሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር በአንዳንድ አገሮች ሕፃን ለሚለው ትርጓሜ ለመስጠት ማኅበራዊ አረዳድን (social construction of age) ግምት ውስጥ የሚያስገቡ ሲሆን ለምሳሌ በጉርምስና ወቅት የሚታዩ አካላዊ ለውጦች እና የድምፅ መጎርነን ከግምት ውስጥ ያስገባሉ፡፡
በዓለም አቀፍ የሕፃናት መብቶች ኮንቬንሽን አንቀጽ 1 የተመለከተው ዕድሜን መሠረት ያደረገ ትርጉም ሲሆን “ሕፃን ማለት ማንኛውም ዕድሜው ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች የሆነ የተፈጥሮ ሰው” እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ሆኖም በምን ጉዳይና ምን ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ዝቅ ማድረግ ወይም 18 ዓመት ሳይሞላ ለአካለ መጠን መድረስ እንደሚቻል ባያስቀምጥም አገራት በሚያወጡት ሕግ መሠረት ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች መውረድ የሚቻልበት አጋጣሚም እንዳለ በኮንቬንሽኑ ተገልጧል፡፡ በዚሁ መሠረት ለምሳሌ በኢትዮጵያ ለጋብቻ ሊባል ማለትም ከባድ ምክንያት ሲያጋጥም ተጋቢዎቹ ወይም ከተጋቢዎቹ የአንዳቸው ወላጆች ወይም አሳዳሪ በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት ፍትሕ ሚኒስትሩ ከመደበኛ የጋብቻ እድሜ (18 ዓመት) ከሁለት ዓመት ያልበለጠ ጊዜ በመቀነስ እንዲጋቡ ሊፈቅድ ይችላል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ሕፃኑ ከሞግዚት አስተዳደር ነፃ እንደወጣ (emancipated) ይቆጠራል፡፡ ይህ የዕድሜ ጣራ መድረሻ (አሥራ ስምንት ዓመት) ከየት እንደሚጀምር በግለፅ የተደነገገ ነገር ባይኖርም በኮንቬንሽኑ መግቢያ ላይ እንደተገለፀው ከመወለድ በፊትም ማለትም በጽንስ ወቅትም ጥበቃ እንዳለ ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የአፍሪካ የሕፃናት መብቶች እና ደኅንነት ቻርተር አንቀጽ 2 ሕፃን ለሚለው ትርጓሜ ሲሰጥ “ሕፃን ማለት ማንኛውም ዕድሜው ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች የሆነ የተፈጥሮ ሰው ነው” በማለት ደንግጓል፡፡
በኢትዮጵያ ለሕፃን ያለውን ትርጉም ስንመለከት ሀገሪቱ ፌደራላዊ ስርዓት የምትከተል በመሆኑ እና የ1987 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራስያዊ ሪፐብሉክ ሕገ መንግሥት የፌደራል እና የክልል መንግሥታት የየራሳቸውን የቤተሰብ ሕግ እንዲያወጡ ስለሚፈቅድ የተለያየ የሕፃን ትርጓሜ ሊኖር የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ በፌደራል የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 215 መሠረት አካለ መጠን ያልደረሰ ሰው ማለት ጾታ ሳይለይ ዕድሜው አሥራ ስምንት ዓመት ያልሞላው ልጅ ነው፡፡
የሕፃናት መብት መርሆዎች
ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ ሕጎች የሕፃናት መብቶችን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል በማሰብ የተለያዩ መርሆዎችን አውጥተዋል፡፡ እነዚህ መርሆዎች የሕፃናት መብቶች ለማስከበር እና ማስተግበር ከፍተኛ አስተዋፅዖ አላቸው፡፡ ከእነዚህ መርሆዎች ዋነኛው የሆነው ለሕፃናት ጥቅምና ደኅንነት ቅድሚያ መስጠት (Best interest of the child) የሚለው መርህ ነው፡፡ በዚህ ረገድ እ.ኤ.አ በ1959 የወጣው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሕፃናት መብቶች መግለጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕፃናት ጥቅም እና ደኅንነት ቅድሚያ መስጠት የሚለውን መርህ አካቶ የወጣ ዓለም አቀፍ ሰነድ ነው፡፡ በመሆኑም ሕፃናት ነክ ውሳኔዎች ሲወሰኑ (ለምሳሌ ወላጆቻቸው የሚለያዩ ከሆነ ከማን ጋር መኖር እንዳለባቸው ሲወሰን) ውሳኔ ሰጭ አካላት ለሕፃናት ጥቅምና ደኅንነት ቅድሚያ በመስጠት የሕግ ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተያያዘ ሁኔታ የኮንቬንሽኑ አራት ዋና ዋና መርሆዎች በሕፃናት መብቶች ኮንቬንሽን ውስጥ የተዘረዘሩትን ሌሎች መብቶች ለማስፈፀም እና ለመተርጎም የሚያገለግሉ ናቸው ፡፡
እነርሱም፣
- የእኩልነት መብት (The Non-discrimination clause) የኮንቬንሽኑ አንቀጽ 2
- ለሕፃናት ጥቅምና ደኅንነት ቅድሚያ መስጠት (The Best Interest of the Child) የኮንቬንሽኑ አንቀጽ 3)
- የመሳተፍ መብት (The Right to participation) ኮንቬንሽኑ አንቀጽ 12፣
- በሕይወት የመኖር እና የመልካም አስተዳደግ መብት (The Right to life, survival and development) የኮንቬንሽኑ አንቀጽ 6፣ ናቸው፡፡
መሠረታዊ የሕፃናት መብቶች በኢትዮጵያ
የሀገራችን ህገ መንግሥት ለህፃንነት ትርጉም ያልሰጠ ወይም የእድሜ ገደብ ያላስቀመጠ ቢሆንም የሕፃናትን መብት ዝርዝር በአንቀጽ 36 ስር ደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚህ መሠረት ማንኛውም ህፃን የሚከተሉት መብቶች አሉት፡-
- በህይወት የመኖር መብት፣
- ስምና ዜግነት የማግኘት መብት፣
- ወላጆቹን ወይም በሕግ የማሳደግ መብት ያላቸውን ሰዎች የማወቅና የእነሱንም እንክብካቤ የማግኘት መብት፣
- ጉልበት ከሚበዘብዙ ልማዶች የመጠበቅ፣ በትምህርት፣ በጤናውና በደህንነቱ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ስራዎች እንዲሰራ ያለመገደድ ወይም ከመሥራት የመጠበቅ፣
- በትምህርት ቤቶች ወይም በሕፃናት ማሳደጊያ ተቋሞች ውስጥ በአካሉ ከሚፈፀም ወይም ከጭካኔና ኢ-ሰብዓዊ ከሆነ ቅጣት ነፃ የመሆን መብት ናቸው፡፡
በተጨማሪም በህገ መንግስቱ እንደተደነገገው ሕፃናትን የሚመለከቱ እርምጃዎች በሚወሰዱበት ጊዜ በመንግስታዊ ወይም በግል በጎ አድራጎት ተቋሞች፣ በፍርድ ቤቶች፣ በአስተዳደር ባለስልጣኖች ወይም በሕግ አውጪ አካላት የሕፃናት ደኅንነት በቀደምትነት መታሰብ አለበት፡፡ ወጣት አጥፊዎች በማረሚያ ወይም በመቋቋሚያ ተቋሞች የሚገኙ በመንግሥት እርዳታ የሚያድጉ ወጣቶች በመንግሥት ወይም በግል እጓለ ማውታን ተቋሞች (የሕፃናት ማሳደጊያዎች) ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ከአዋቂዎች ተለይተው መያዝ አለባቸው፡፡ እንዲሁም ከጋብቻ ውጪ የተወለዱ ሕፃናት በጋብቻ ከተወላዱ ሕፃናት ጋር እኩል መብት አላቸው፡፡ እንዲሀም መንግሥት ለእጓለ ማውታን ልዩ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው እና በጉዲፈቻ የሚያድጉበት ሥርዓት የሚያመቻቹና የሚያስፋፉ፣ ደህንነታቸውንና ትምህርታቸውን የሚያራምዱ ተቋሞች እንዲመሰረቱ እንደሚያበረታታ ይደነግጋል፡፡
በአጠቃላይ ሕፃናት የሚከተሉት ዓለም ዓቀፍ መሠረታዊ መብች ሊጠበቁላቸው ይገባል፡፡
- የእኩልነት መብት:- በጾታ፣ በዘር፣ በጎሳ፣ በቋንቋ፣ በኢኮኖሚ አቋም፣ በብሔር ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት ወይም አድሎአዊ በሆነ በማንኛውም ሁኔታ ላይ በመመርኮዝ ልዩነቶች ሊደረጉ አይገባም፡፡
- መብላት እና መጠለያ የማግኘት መብት:- ሁሉም ልጆች ለትክክለኛው እድገታቸው አስፈላጊ የሆነውን ምግብ የማግኘት እንዲሁም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሚኖሩበት ቤት የማግኘትና የመደሰት መብት አላቸው ፡፡
- የትምህርት መብቶች:- ሁሉም ልጆች ችሎታቸውን ለማዳበር እና የራሳቸውን የወደፊት ዕድል ለመፍጠር ትምህርት የማግኘት መብት አላቸው፡፡ ምክንያቱም ለትክክለኛው ሥነ-ልቦናዊ፣ ስሜታዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገታቸው አስፈላጊ ነው፡፡
- የጤንነት መብት:- ልጆች ጤንነታቸውን ለመንከባከብ እና ለማቆየት እንዲሁም በሽታን ለመከላከል አስፈላጊ የሕክምና ክትትል እና እንክብካቤ ማግኘት አለባቸው፡፡ ወደ ጤናማ አዋቂዎች እንዲያድጉ ጥሩ ፈውስ የማግኘት መብት አላቸው፡፡
- በሕይወት የመኖር መብት፡- ሕፃናት ህይወታቸውን አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ነገሮች የመጠበቅ እና የመትረፍ (right of protection and survival) መብት አላቸው፡፡ እንዲሁም በቂ የኑሮ ደረጃ (adequate standard of living) የማግኘት መብት አላቸው፡፡
በአጠቃላይ ሕፃናት በተለይ በእድሜያቸው ምክንያት ለተለያዩ አደጋዎች የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ስለሆነ መንግሥት በሂደት (progressively) የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በፈቀደ መጠን የሕፃናትን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሕፃናትን መብት ለማክበር፣ ለመጠበቅ እና ለማሟላት ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት