የኤሌክትሮኒክ ገበያ ሕግ በኢትዮጵያ

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

አሁን ባለንበት ዘመን የኤልክትሮኒክ ግብይት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተደራሽነት እያሰፋ መደበኛውን ግብይት እየተካ ይመስላል። የኤሌክትሮኒክ ግብይት የኤሌክትሮኒክ ዘዴዎችን በመጠቀም ምርት መሸጥና መግዛት፣ አገልግሎትን በማቅረብ እና በማግኘት የሚፈፀም እንደመሆኑ ዕድገቱ ከቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር በትይዩ ሊሄድ የሚችል ነው፡፡ ቴክኖሎጂውም በብርሃን ፍጥነት በሚባል መልኩ አዳዲስ ፈጠራዎችን እያስተዋወቀ በሰዎች መካከል ያለውን ግንኙነት በቦታ፣ በጊዜ እና በሁኔታዎች ላይ እያደረገው ይገኛል፡፡ በተለይም በንግዱ ዓለም ሰዎች መንቀሳቀስ ሳይጠበቅባቸው ካሉበት ቦታ ሆነው የሚፈልጉትን ምርት እና አገልግሎት የሚያገኙበት፣ ክፍያ የሚፈጽሙበት እንዲሁም የመንግሥት አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ይህም ሁኔታ በሰዎች መካከል የነበረውን መደበኛ የአካል ግንኙነት ወይም ከእጅ በእጅ ግንኙነት አውጥቶ ወደ ኤሌክትሮኒክ እየቀየረው ይገኛል፡፡

በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ በሚደረግ ግንኙነት ግንኙነቱ ከሚደረግበት ሥርዓት፣ የግንኙነቱ መረብ ከሚዘረጋበት ቦታ፣ በግንኙነት የሚሳተፉ ሰዎች በአካል ሳይተያዩ የሚፈጽሙት መሆኑ፣ ሥርዓቱ በሀገራት መካከል በተወሰነው ጂኦግራፊያዊ ክልል ሳይወሰን ድንበር ተሻጋሪ መሆኑ፣ አማራጭ የኤሌክትሮኒክስ የግንኙነት ዘዴዎች ፈጣን በሚባል ደረጃ መፈጠራቸው፣ ግንኙነቱ የግላዊነት እና መረጃ መብት ጥሰትን ጨምሮ ለተለያዩ አደጋዎች ተጋላጭ መሆኑ የኤሌክትሮኒክ ግንኙነት በሕግ የሚኖረው ውጤት እና አስተዳደር ምን መሆን አለበት የሚለውን ጥያቄ በማስነሳቱ የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን አዋጅ ቁጥር 1205/2012 ዓ.ም ተደንግጎ ወጥቷል፡፡

የኤልክትሮኒክ ግብይት ከኦንላይን ችርቻሮ እስከ ኤልክትሮኒክ አገልግሎቶች ድረስ ያለውን ሁሉ የሚያጠቃልል ከፍተኛ የሚባል የዓለም ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀስበት የግብይት ዘዴ ነው፡፡ በሀገራችን የኤልክትሮኒክ ንግድ እና የኤልክትሮኒክ የመንግሥት አገልግሎት በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ብዙ ግብይቶች የሚስተናገዱበት መድረክ እየሆነ መጥቷል። በዚህ ፈጣን ዕድገት ባለው ግብይት በተሳታፊዎች መካከል ፍትሐዊነትን፣ ደኅንነትን እና መተማመንን ለማረጋገጥ ግልጽ የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልጉታል።

የኤሌክትሮኒክ ግብይቶች በህላዊ የነበረውን ንግድ በበይነ መረብ መንገድ በማድረጉ ምክንያት ግብይቱ እንዴት ይመራ? በግብይቱ የሚሳተፉ ሸማቾች ከመደበኛው ግብይት ሸማቾች ጋር እኩል እንዴት ጥበቃ ይደረግላቸው? በኤሌክትሮኒክ የሚነሱ ሌሎች የሕግ ጉዳዮች በምን መለኩ ምላሽ ያግኙ? የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉት የኤሌክትሮኒክ ግብይትን መሠረታዊ ባህሪ ከሕግ ማዕቀፉ ጋር በመረዳት ነው።

ኤሌክትሮኒክ ገበያ በኢትዮጵያ በሕግ ሪፎርም ፕሮግራም ከተደረጉ ማሻሻያዎች አንዱ ነው፡፡ ስለሆነም በካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013 መሠረት በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ ትብብር በአክሲዮን ኩባንያነት እንደሚቋቋም ተደንግጓል፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ የኤሌክትሮኒክ ንግድ ምንነት፣ የኤሌክትሮኒክ ንግድ ዓይነቶች እና የኤሌክትሮኒክ ንግድ ጥቅም የሚሉትን የምናይ ይሆናል፡፡

የኤሌክትሮኒክ ንግድ ምንነት

የኤሌክትሮኒክ ንግድ የሚለውን ከማየታችን በፊት ኤሌክትሮኒክ ምን እንደሆነ ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ በኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን አዋጅ ቁጥር 1205/2012 አንቀጽ 2 (11) መሠረት “ኤሌክትሮኒክ” ማለት ከቴክኖሎጂ አንፃር የኤሌክትሪክ፣ የማግኔታዊ፣ የኦፕቲካል ወይም ሌላ ተመሳሳይ አቅም ያለው የመጠቀሚያ መንገድ ነው፡፡

ለኤሌክትሮኒክ ንግድ ወጥ የሆነ ትርጉም የተሰጠው ባይሆንም በተለያዩ ጽሁፎች የተለያዩ ትርጉሞች ተሰጥቶት ይገኛል። የኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ድርጅት /The Organization for Economic Co-operation and Development-OECD/ የኤሌክትሮኒክ ንግድ በይነ መረብን በመጠቀም በንግድ ድርጅቶች፣ በሸማቾች፣ በመንግሥት እና በግል ተቋማት መካከል የሚደረግ ሸቀጦችን የመግዛት ወይም የመሸጥ እንዲሁም አገልግሎቶችን ማግኘት እንደሆነ ገልጾት እናገኛለን፡፡ እንደ ድርጅቱ ገለፃ አንድን ግብይት ኤሌክትሮኒክ ንግድ የሚያስብለው ዕቃዎቹ ወይም አገልግሎቱ በአውታረ መረብ የታዘዙ መሆናቸው ሲሆን የዕቃዎቹ አቅርቦት እና ክፍያው በዲጂታል መሆን እንደማይጠበቅበት ይገልፃል።

በሌላ በኩል የኤልክትሮኒክ ንግድ ሸቀጦችን እና አገልግሎቶችን ከመግዛት እና ከመሸጥ በሰፋ መልኩ መታየት እና መገለጽ እንዳለበት የሚገልጹም አሉ። እንደነዚህ ጸሀፊዎች ገለጻ የኤልክትሮኒክ ንግድ ሸቀጥ እና አገልግሎትን ከመግዛትና ከመሸጥ ባለፈ በንግድ ድርጅቶች መካከል የሚደረግን የንግድ ትብብር፣ ግብይትን ለመደገፍ የሚተገበሩ የውስጥ ኤሌክትሮኒክ ግንኙነቶች፣ የደንበኞች አገልግሎት፣ የኤሌክትሮኒክ ትምህርት የመሳሰሉ በበይነ መረብ የሚደረግ ማንኛውንም ግብይት ያጠቃልላል በማለት ይገልፃሉ፡፡ በኢትዮጵያ አሁን በስራ ላይ ያለውና የኤሌክትሮኒክ ትራናዛክሽንን የሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 1205/2012 በአንቀጽ 2 (12) ላይ የኤሌክትሮኒክስ ንግድ፤ ማለት ኢንተርኔትን ወይም ሌሎች የመረጃ መረብን በመጠቀም የሚደረግ የሸቀጦችና የአገልግሎቶች ግብይት ወይም ልውውጥ ነው፤ በማለት ትርጉም ሰጥቶታል።

በአሌክትሮኒክ ንግድ ከሚፈጸሙ ግብይቶች ውስጥ ግዙፍነት የሌላቸው እንደ የሶፍትዌር ወይም የኤሌክትሮነክ መጽሐፍ ሽያጮች በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክ ግብይት የሚገኝበት ሁኔታ፣ ከአጠቃላዩ የሀገሪቱ ዲጂታል ኢኮኖሚ ንግድ ሁኔታ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው፡፡ መንግሥት የዲጂታል 2025 ስትራቴጂን በማውጣት ከዚህ ጋር የተያያዙ አዋጆችና መመርያዎች በማውጣት በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡

የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የኤሌክትሮኒክስ ንግድ ወይም ኢ-ኮሜርስ አንዱና ዋነኛው የፋይናንስ አቅም ማጠናከሪያ መንገድ አድርጎ አስቀምጦታል። ኤሌክትሮኒክስ ንግድ ወይም ኢ-ኮሜርስ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በኢንተርኔት መግዛት እና መሸጥን ያመለክታል። ለምሳሌ፡- የነዳጅ ግብይት ተጠቃሽ ነው፡፡

የኤሌክትሮኒክ ንግድ ዓይነቶች ፡-

የኤሌክትሮኒክ ንግድ በግብይቱ እንደሚሳተፉ ተሳታፊዎች ዓይነት እና የንግድ ግንኙነት አንፃር በሚከተሉት መደቦች ይከፈላል (ዲጅታል ገበያ ሕግ በኢትዮጵያ፣ ፍቃዱ አንዳርጌ መኮንን፣ 2017 ዓ.ም፣ ገጽ 15-18) ።

ከንግድ ድርጅት ወደ ንግድ ደርጅት (Business to Business)

ይህ ግንኙነት በሁለት ንግድ ድርጅቶች መካከል የሚደረጉ ትልልቅ ግብይቶችን የሚመለከት ሲሆን ኦን ላይን መደብሮች ወይም የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓቶችን በመጠቀም በንግድ ድርጅቶች መካከል የሚደረግ የንግድ ግንኙነት ነው። ለምሳሌ አንድ አምራች በይነ መረብን በመጠቀም ኦንላይን የሽያጭ ማዕከሎች አማካኝነት ምርቶቹን ለጅምላ ሽያጭ ሊሸጥ ይችላል። በዚህ ግብይት የንግድ ደርጅቶች የኤሌክትሮኒክ ንግድ የሚካሄድባቸውን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደር፣ የኤለክትሮኒክ ክፍያዎች እና ደረሰኞች የሚተገበሩበት ሥርዓት በመዘርጋት የንግድ ሥራቸውን ያቀላጥፋሉ።

ከንግድ ድርጅት ወደ ሸማቾች (Business to Consumer) ፡-

ይህ ዓይነቱ ግብይት በንግድ ድርጅቶች እና በሸማቾች መካከል የሚደረግ ግብይት ነው። የንግድ ድርጅቶች ምርት እና አገልግሎቶችን ለደንበኞች የግል ፍጆታ በበይነ መረብ በቀጥታ የሚሰጡበት ሂደት እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችል ነው። ግብይቱ የሚደረገው በቀጥታ በነጋዴው እና በደንበኛው መካከል ሲሆን በግብይቱ ውስጥ በአገኛኝነት ወይም አመቻችነት የሚሳተፉ ሦስተኛ ወገኖች የሌሉበት ነው። ከቢዝነስ ወደ ሸማች በሚደረገው ግብይት ሌላ መግለጫ ሆኖ የሚቀርበው አንድ ለብዙ ( a one to many) ቅርጽ ያለ መሆኑ ነው። አንድ ለብዙ የተባለበት ምክንያት አንድ የኦን ላይን መደብር ምርቱን ወይም አገልግሎቱን ለብዙ ደንበኞች በተመሳሳይ ጊዜ ስለሚሸጥ ነው። የህም በግብይቱ መድረክ ደንበኞች የሚፈልጉትን ምርት እና አገልግሎት በመምረጥ ግብይቱን የሚያከናውኑበት ነው። Amazon.Com ከንግድ ድርጅት ወደ ሸማች ለሚደረግ ግብይት በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል ነው።

ከንግድ ድርጅት ወደ መንግሥት (Business to Government) ፡-

የዚህ ዓይነት ግብይት በድርጅቶች እና በመንግሥት አካላት መካከል የሚደረግ ግብይትን የሚመለከት ነው። ንግድ ድርጅቶች የኤሌክተሮኒክ መድረኮችን በመጠቀም ምርቶችን ወይም አገልግሎቶችን ለመንግሥት አካላት ወይም ኤጀንሲዎች ይሸጣሉ ወይም ያቀርባሉ። ይህ ግብይት የግል ኩባንያዎች በመንግሥት ግዥ ሂደቶች ውስጥ እንዲሳተፉ፣ በመንግሥት አጀንሲዎች ለሚወጡ ውሎች፣ ጨረታ እና ከመንግሥት ሥራ ጋር ለተያያዙ አገልግሎቶች በኦንላይን እንዲሳተፉ እና ክፍያም እንዲከፍሉ ያስችላቸዋል። በዚህ የግብይት መድረክ የኤሌክትሮኒክ ግዥ፣ ኤሌክትሮኒክ ጨረታ፣ ኤለክትሮኒክ ደረሰኝ እና ኤሌክትሮኒክ ክፍያን ጨምሮ የተለያዩ ፕሮግራሞች ጥቅም ላይ ይውላሉ።

የኤሌክትሮኒክ ግዥ ( e-procurement) የመንግሥት ተቋማት የወረቀት አሠራርን በማስቀረት ግዥ በኤሌክተሮኒክ መንገድ እንዲፈፀም የሚያስችል ሲሆን የግዥ ሂደቱን ምቹ፣ ጊዜ እና ገንዘብ ቆጣቢ እንዲሁም ቀላል የኮንትራት አስተዳደር እንዲኖር ያስችላል። የኢሌክትሮኒክ ጨረታ (e- tendering) መንግሥት የሚያወጣቸውን ጨረታዎች በኦን ይን ወይም በኤሌክተሮኒክ መንገድ የማቅረብ ሂደት ነው። የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ (e-recipt) የንግድ ደርጅቶች የኤሌክትሮኒክ ደረሰኞችን ለመንግሥት ኤጀንሲዎች እንዲያቀርቡ ያስችላቸዋል። ኤሌክትሮኒክ ክፍያ (e-payment) ንግድ ድርጅቶች ከመንግሥት ጋር ለሚያደርጉት ግብይት ኦንላይን እንዲከፍሉ ያስችላቸዋል።

ከሸማች ወደ ሸማች (Consumer to Consumer)

ይህ ዓይነቱ ግብይት በግለሰብ ሸማቾች መካከል የሚደረጉ ግብይቶችን የሚመለከት ነው። ግለሰብ ሸማቾች በኦን ላይን መድረኮችን ወይም ገበያ ቦታዎችን በመጠቀም በቀጥታ በመካከላቸው ምርቶችን ወይም አገልግሎቶቹን የሚገዙበትና የሚሸጡበት የንግድ ግንኙነት ነው። በዚህ ግብይት የኤሌክትሮኒክ ንግድ መድርኮች ገዥዎችን እና ሻጮችን ለማገናኘት የኮሚሽን ክፍያ የሚወስዱበት ሲሆን ግብይቶችን በማመቻቸት እንደ መሀል አገናኝ በመሆን ይሰራሉ።

ከሸማቾች ወደ ንግድ ደርጅት (Consumer to Business) ፡-

ይህ ዓይነቱ ግብይት እያንዳንዱ ሸማች ምርቶቻቸውን ወይም አገልግሎታቸውን ለንግድ ድርጅቶች የሚሸጡበትን ግብይቶችን የሚያካትት ነው። በተለመደው የግብይት ሥርዓት ንግድ ድርጅቶች ምርት እና አገልግሎታቸውን ይሸጣሉ። ለምሳሌ አገልግሎታቸውን ለንግድ ደርጅቶች የሚያቀርቡ ነፃ የገበያ ቦታዎች (Freelance market places) በተጠቃሚዎች የመነጨ ይዘት (User-generated content) ያላቸውን ስራዎች የሚያስተላልፉበት መድረክ እንደ ምሳሌነት መጠቀስ ይችላል። ነፃ የገበያ ቦታዎች ንግድ ድርጅቶችን እና ግለሰቦች ለተለያዩ የሥራ ዓይነቶች ከግል ተቀጣሪዎች ጋር የሚገናኙባቸው የመስመር ላይ መድረኮች ናቸው። እነዚህ የግል ተቀጣሪዎች በፕሮጀክት ወይም በኮንትራት መሠረት አገልግሎታቸውን ለደንበኞች የሚያቀርቡ ሲሆን በተለምዶ እንደ ድረ-ገጽ ማበልፀግ፣ ግራፊክ ዲዛይን፣ መጻፍ፣ ማማከር እና በሌሎች መስኮች ይሰራሉ። ሌላው ሸማቾችን ከንግድ ድርጅቶች ጋር የሚያገናኘው መድረክ ከተጠቃሚዎች የመነጨን ሥራ የሚያቀርቡ መድረኮች ሲሆኑ እንደ YouTube, Instagram, Tik Tok በምሳሌነት ይጠቀሳሉ። እነዚህ ከተጠቃሚዎች የሚመነጩ ይዘት ያላቸው ሥራዎች በኩባንያቸው ወይም በንግድ ደርጅቱ ሳይሆን በሸማቾች ወይም በአንድ ምርት ወይም አገልግሎት ተጠቃሚዎች የሚፈጠሩ ናቸው። በኦንላይን መድረክ ወይም በማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ተጠቃሚዎች የተፈጠሩና የሚጋሩ የጽሁፍ ልጥፎች፣ ፎቶዎች፣ ቪዲዮዎች እና ሌሎች ይዘት ያላቸው ሥራዎች ጋር ተያያዥነት ያላቸው ናቸው።

የኤሌክትሮኒክ ንግድ ጥቅም ፡-

የኤሌክትሮኒክ ንግድ ከተለመደውና በአካል በመገናኘት ፊት ለፊት ከሚደረገው ግብይት የተሻለ የሚያደርጉት የተለያዩ ጥቅሞች እንዳሉት ብዙዎች የሚስማሙበት ነው። ከሚጠቀሱት ጥቅሞች መካከል፡-

  • አመችነት (Convenience)
  • ተደራሽነት (Accessible)
  • ወጪ ቆጣቢነት (Cost Effective)
  • የሸማቾች ልምድ መሻሻል (improved Customer Experience) የሚሉት ይገኙበታል /Technology and Law in Ethiopia, Mezmur Yared Debella April.2024/።

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ የኤሌክትሮኒክ ገበያ ነባሩን የግብይት ዘዴ እየተካው የሚሄድ መሆኑ ይጠበቃል፡፡ ስለሆነም ህብረተሰቡ ራሱን ከቴክኖሎጂ ጋር በማላመድ እና ብቁ በመሆን ከዘመኑ ጋር አብሮ መዘመን እንዳለበት መረዳት ተገቢ ነው፡፡ በተጨማሪም ግብይቶችን በኤሌክትሮኒክ ዘዴ በማድረግ ለኢኮኖሚው ዕድገት የበኩላችን ድርሻ መወጣት ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ