በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ለክልሎች በዉክልና የሰጣቸዉ ተግባራቱንና የአገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽነትን በማስፋት በኩል ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ይህንኑ አገልግሎቱን ለማሳደግም በድሬዳዋ እና ሐዋሳ ከተማ ከሚገኙ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በተጨማሪ ከታክስና ጉሙሩክ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ የምርመራ እና የክርክር ስራዎች የሚከናወኑበት 6 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን በማደራጀት ወደ ስራ ማስገባት ተችሏል፡፡
ተግባሩ በተሳካ መልኩ እንዲከናወን ለማስቻልም ፍትሕ ሚኒስቴር እና ሁሉም የክልል ፍትሕ ቢሮዎች ጋር 2ኛዉ የጋራ ጉባኤ መድረክ ሪፖርት፣ ሱፐርቪዥን ሪፖርት፣ እና የጋራ ሪፖርት ማቅረቢያ ቼክሊስት ቀርቦና ዉይይት ተደርጎበት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
እንዲሁም በ3ኛዉ የፍትሕ አካላት የጋራ ጉባኤ ላይ የሁሉም የፍትሕ ቢሮ ተቋማት፣ የፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ም/ኮሚሽነሮች፣ ማረሚያ ቤት ከሚሽን፣ ገቢዎች ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች በተገኙበት የተጠቃለለ የ2015 ዓ.ም የፍትሕ ሚኒስቴር እና የክልል ፍትሕ ቢሮዎች የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ዉይይት ተደርጎበታል፡፡
በተያያዘ በዚሁ መድረክ ላይ የኢትዮጵያ የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን (መሠረታዊ ለውጥ) መነሻ ጽሁፍ፣ በኦሮሚያ ክልል የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ የማኅበረሰብ አቀፍ የፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ የባህላዊ ፍርድ ቤት ሚና፣ የተገኙ ውጤቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች በሚመለከት ያለውን መልካም ተሞክሮ እና በሰው መነገድና ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመመርመርና ለማስቀጣት የተዘጋጀ የአሠራር ስርዓት ማኑዋልን በሚመለከት ሰነዶች ቀርበዉ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
በተጨማሪም በውክልና ለተሰጡ ጉዳዮች ማስፈፀሚያ የሚሆን የድጎማ በጀት ከዚህ ቀደም በተዘጋጀዉ የበጀት ቀመር መመሪያ መሠረት ክፍፍል በመፈፀም የክልል ፍትሕ ቢሮዎች እንዲያዉቁት ተደርጓል፡፡
በዚህ ረገድ የክልል ፍትሕ ቢሮዎች ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በትብብር በመሥራት ለውጥ ለማምጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን አሳይተዋል። በተለይም ክልሎቹ በሚቀጥሉት 3 ዓመታት የሚተገበር የትራንስፎርሜሽን ዝርዝር ዕቅድ አዘጋጅተው መተግበር መጀመራቸው በጋራ መድረኩ የተፈጠረው ቅንጅታዊ ውጤት መሆኑም ለመመልከት ተችሏል።