የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳሬክቶሬት አዘጋጅነት ተቋሙን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለተቀላቀሉ ዐቃብያነ ሕግ በወንጀል ምርመራ፣ በክስ አደረጃጀት እና ክርክር ዙሪያ ያላቸውን ክህሎት ለማሳደግ ታስቦ የተዘጋጀ ሥልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡
የንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳሬክቶሬት ባደረገው የሥልጠና ፍላጎት ዳሰሳ መነሻነት በተቋሙ ውስጥ ላሉ ለድጋፍ ሰጪ ሰተኞች እንዲሁም ለዐቃብያነ ሕግ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየሰጠ እንዳለ ይታወቃል፤ በዚህም መሠረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቋሙን ለተቀላቀሉ ዐቃብያነ ሕግ በወንጀል ምርመራና ክስ ላይ ያላቸውን ክህሎት በሥልጠና በማሳደግ የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል ታሳቢ ተደርጎ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ተገኘተው መልዕክት ያስተላለፉት በፍትሕ ሚኒስቴር ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መከታተያ ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ጌቱ ታደሰ ሥልጠናው በስራ ላይ ያጋጠሙ የክህሎት ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አክለውም በወንጀል ምርመራ፤ በክስ አደረጃጀት እና ክርክር ዙሪያ በስራ ላይ የሚታዩ ችግሮች ከተለዩ በኀላ ሥልጠናው ስራውን በሚመሩ ሀላፊዎች ድጋፍ እንዲሰጥ በማድረግ እርስ በርስ ተቀራርበው ያጋጠሙ ችግሮችን በማንሳት መወያየት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው ባለሙያዎቹ ሥልጠናውን በትኩረት እንዲከታtሉ ሲሉ በአፅኖት ተናግረዋል፡፡
የሥልጠና መድረኩን የከፈቱት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታ እና ሪፎርም ዘርፍ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ መዝሙር ያሬድ በበኩላቸው ፍትሕ ሚኒስቴር የሙያ ስነምግባርን ጠብቆ መሥራትን የሚፈልግ ተቋም በመሆኑ ዐቃቤ ህጉ ያሉትን የሕግ መርሆች አክብሮ መሥራትና ህጉን ብቻ መሠረት አድርጎ የተጠርጣሪዎች መብት ሳይጋደል አጠፊዎች ተገቢ የሆነ ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ የሚጠበቅበት በመሆኑ ይህንን ተግባር በጥሩ ሁኔታ ለመፈፀም የሚያግዙ መሰል የስራ ላይ ሥልጠናዎችን በመውስድ እራስን ማብቃት አስፍላጊ መሆኑን አመላክተዋል።
ሀላፊው አያይዘውም ዐቃቤ ህጉ በሥልጠናው ላይ በየዕለቱ በሚኖረው ስራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በማንሳት መወያየት ችግሮችን ብቻ ሳይሆን ያጋጠሙ ተሞክሮዎችን በማንሳት ልምድ መለዋወጥ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የመጀመሪያ ዙር የሆነው ይህ ሥልጠና አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙት ከአስራ አንዱም ምድብ ጽ/ቤቶች ተወክለው ለመጡ ዐቃብያነ ሕግ ለተከታታይ 5 ቀናት የሚሰጥ መሆኑ በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡