የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከአለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም ) ጋር በመተባበር በሰው የመነገድና ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎች ዙሪያ ያሉ የሕግ ማዕቀፎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሥልጠና ለከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ለፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት እና ለክልል ፍርድ ቤት ዳኞች በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ወቅት ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት እና የፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ አቶ ተስፋዬ ንዋይ በሰው የመነገድና ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ብዙ ዘመናትን ያስቆጠረና በሰዎች አካል፣ ህይወትና ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ያለ ወንጀል መሆኑን ገልፀው የወንጀሉ ተጎጂዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ እንደሚገኝ ጥናቶች እንደሚያመላክቱ ጠቁመዋል።
እነዚህ ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎችም አለም አቀፋዊ ባህሪ ያላቸውና በተደራጀ መልኩ የሚንቀሳቀሱ ከመሆናቸው በተጨማሪ በአስገድዶ ማሰራትና በአስገድዶ የወሲብ ንግድ ላይ በማሰማራት በርካታ ገንዘብ እንደሚያካብቱ የገለፁት ምክትል ፕሬዝዳንቱ እነዚህን ተግባራት ለመከላከልና ለመቆጣጠር በርካታ ዓለም ዓቀፍ ኮንቬንሽኖች፣ ፕሮቶኮሎች ብሎም ሕግ በማውጣት ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም ከዚህ በተጨማሪ የተከለከሉ የወንጀል ተግባራትን ፈፅመው የተገኙ ሰዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ለማስቻል የፍትሕ አካላት በተገቢው መንገድ ሚናቸውን በቅጡ ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።
አይይዘውም የፍትሕ አካላትና የዳኝነት አካላት አዋጁን ለማስፈፀም በተናጠልና በጋራ በባለቤትነት መንፈስ ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባና ወደ ስራቸው ሲመለሱም ከሥልጠናው የሚያገኙትን እውቀትና ልምድ በመጠቀም የድርሻቸውን እንዲወጡ አደራ ብለዋል።
በሥልጠናው የፍልሰት ስያሜዎች (ትርጓሜዎች)፣የፍልሰት አስተዳደር በኢትዮጵያ ያሉ የሕግ ማእቀፎች፣ የህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሀብት ማስመለስ፣ አገር አቀፍና ዓለም ዓቀፍ የሕግ ማእቀፎች፣ የቅድመ ጥቆማ ምርመራ እንዴት ይከናወናል የፍርድ ቤቶች ሚናስ የሚሉና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ሰነዶች የሚቀርቡ ይሆናል።
ሥልጠናው ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በተግባር ላይ ያተኮረ የልምድ ልውውጥ እንደሚደረግበት ይጠበቃል።