የማህበረሰብ ዓቀፍ ፖሊስ አገልግሎትን በመጠቀም የወንጀል መከላከል ላይ ያተኮረ ስልጠና መሰጠት ተጀመረ

Training on Crime Prevention Using Community Policing Launched

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት ለፌዴራል እና አዲስ አበባ ፖሊስ የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አመራሮች በማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት በመጠቀም ወንጀል መከላከል በተመለከተ ከሚያዚያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየተሰጠ ነው፡፡

በሥልጠናው መክፈቻ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ወርቁ በኢፌዲሪ የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ እንዲሁም የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ ላይ በማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት በመጠቀም ወንጀል መከላከል ትልቅ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ገልፀው ፍትሕ ሚኒስቴር በዚህ ረገድ የማስተባበር ኃላፊነት እንደተሰጠው በመጠቆም ይህንንም መሠረት በማድረግ ላለፉት አመታት ለፌዴራል፣ አዲስ አበባ እና ክልል ፖሊስ መሰል ሥልጠናዎች ሲሰጡ እንደነበር በመግለፅ በቀጣይም ሥልጠናዎቹ እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

ወንጀል ከተፈፀመ በኋላ የመመርመሩ ሂደት እጅግ ዉስብስብ እና አድካሚ በመሆኑ አስቀድሞ መከላከል አዋጭ በመሆኑ የፖሊስንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ቅንጅት መፈለጉ ዋና አጀንዳ ሆኗል ያሉት ሥልጠናውን የሰጡት ምክትል ኮሚሽነር ጋሹ አለማየሁ ሲሆኑ፤ ከለዉጡ በፊት የነበረዉ የፖሊስ ሥልጠና ወቅቱን ያልዋጀ እንደነበር የሚያሳዩ ጥናቶች እንደነበሩ አንስተው በፍትሕና የጸጥታ ተቋማት ላይ ዉጤታማ የሪፎርም ማሻሻያ ስራዎች በመሰራታቸዉ በአሁኑ ወቅት ሀገራዊ የወንጀል መከላከል ፖሊሲ ጸድቆ በስራ ላይ ዉሏል ብለዋል፡፡

የማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደዋነኛ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ ተደርጎ ስራ ላይ ቢዉልም ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በሰዉ ኃይል ፍልሰት፤ በየአካባቢዉ በሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች፤ በግብአት እጥረትና ሌሎች ተደራራቢ ችግሮች ተዳክሞ ቆይቷል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር በመተባበር ወንጀልን በመከላከል ረገድ የተሻለ ስራ በመሰራቱ የአካባቢዉን ሰላምና ጸጥታ ለማረጋገጥ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

ማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ላይ የሚሰማሩ አባላትን ማብቃት አስፈላጊ በመሆኑ በማህበረሰቡ ዉስጥ አንድን አካባቢ እንዴት መጠበቅና ማብቃት እንደሚቻል፤ የመረጃ ልዉዉጥና ሪፖርት አቀራርብን፤ ከፖሊስ ጋር በአጋርነት ለመሥራት የሚረዱ የመስተጋብር ስልቶችን እና በቴክኖሎጂ የተደገፉ ሥልጠናዎችን ጨምሮ በቂ እዉቀት እንዲኖራቸዉ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑም በሥልጠናው ወቅት ተመላክቷል፡፡

በተለይም በየደረጃዉ የሚገኙ የፖሊስ አመራሮች እንደተቋም የሚነደፉ የኮሚኒቲ ፖሊሲ ስትራቴጂዎች ላይ የማያቋርጥ ቁጥጥርና ድጋፍ ከማድረግ ጎን ለጎን አፈጻጸማቸዉን መገምገምና ማስተካከያ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ሥራ ዉጤቱ በአንድ ጀንበር የማይታይ እና ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ በፖሊስና በማህበረሰቡ መካከል መተማመን እንዲፈጠር ያለዉን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገባ ግብ ቀርጾ መተግበር አስፈላጊ ሲሆን በተለይ ብዙ ፍላጎት ያላቸዉንና የወንጀል ተጋለጨነታቸዉ ከፍተኛ የሆኑትን ወጣቶች ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ በማሳደግ ያላቸዉን ከፍተኛ አቅም መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ እና ወጣቶችን ያላሳተፈ የወንጀል መከላከል ሥራ ዉጤታማ ሊሆን እንደማይችል ተገልፆል፡፡

ሰልጣኞች በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው ወደ ተግባር ቀይሮ ማየት ያስቻለ ተሞክሮ ያገኙበትና በቀጣይነት የተሻለ ስራን በቀላል መንገድ ለማከናወን የሚያስችላቸውን እውቀት ያገኙበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዚህ ሥልጠና ላይ ከ80 በላይ ከፌዴራል እና አዲስ አበባ ፖሊስ የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን ሥልጠናው በነገው እለትም የሚቀጥል ይሆናል፡፡

Tagged Under: ababa • addis • Addis Ababa Police • building • capacity • Capacity Building • community • Community Engagement • Community Policing • Crime • Crime Prevention • criminal justice policy • enforcement • federal • Federal police • information sharing • law • Law Enforcement • Police • police leadership • police reform • Police Training • policing • prevention • Security • Stakeholder Collaboration • Strategic Planning • technology-assisted training • Training • youth engagement
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች