ሀገር አቀፍ የተቀናጀ ወንጀል መከላከል ስትራቴጂ ተፈፃሚነት እና በሰብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ

Training Given on the Implementation of the National Integrated Crime Prevention Strategy and Human Rights Handling

በፍትሕ ሚኒስቴር ንቃተ ሕግ ትምህርት እና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ከድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ሀገር አቀፍ የተቀናጀ ወንጀል መከላከል ስትራተጂ ተፈፃሚነት እና ሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አባላት ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

የንቃተ ሕግ ትምህርት እና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ም/ረዳት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሆኑት አቶ ዮሐንስ ግርማ እንደገለፁት ሥልጠናው ሀገር አቀፍ በሆነ መልኩ በ2012 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ስትራተጂን መሠረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡

አቶ ዮሀንስ አያይዘውም ሕግ አስፈጻሚ ከሆኑት የፍትሕ አካላት መካከል ፖሊስ ግንባር ቀደም ሚና ያለው በመሆኑ የወንጀል መከላከል ስራው በስትራቴጂው በተቀመጡ ዓላማዎች እና ግቦች ጋር በተናበበ መልኩ እየተፈጸሙ ከመሆናቸው አንጻር ያሉ ጠንካራ ጎኖችን ማስቀጠል እና ደካማ ጎኖችን በስትራቴጂው በተጠቀሱ ዘዴዎች መሠረት ባለ ድርሻ አካላትን እና ማህበረሰቡን በማሳተፍ አስትራቴጂውን በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ ያስችል ዘንድ የፖሊስ አባላቱን ግንዛቤ ለማሳደግ ታስቦ የሚሰጥ ሥልጠና መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ተወካይ ኃላፊ ዋ/ኢ/ር ይሄነው ሺፈራው በበኩላቸው የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የአስተዳደሩን ሰላም እና ፀጥታ ከመጠበቅ ባለፈ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶችን አክብሮ በማስከበር ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ማክበር እና ማስከበር ቀዳሚው የፖሊስ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ በተቀመጠው እቅድ መሠረት የፖሊስ አባላት ሰነዱን በሚገባ ተረድተው በቀጣይ ማህበረሰቡን በማሳተፍ ሰፊ የሆነ የወንጀል መከላከል ስራዎችን በማከናወን የመፈጸም እና የማስፈፅም አቅማቸውን ማሳደግ እንደሚገባ በሥልጠናው ተመላክቷል፡፡

የፖሊስ አባላቱ የወንጀል መከላከል ስራውን ሲሰሩም ሆነ ወንጀል ተፈጽሞ ሲገኝ ተጠርጣሪዎችን እና ተከሳሾችን ለፍትሕ በማቅረብ ስራ ውስጥ ሊዘነጉ የማይገባቸው ሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ዙሪያ ሥልጠናው ያተኮረ ሲሆን የሰብዓዊ መብት ምንነት፣ ባህሪያት እና መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ጋር በተያያዘ መብቶቹን ከማክበር፣ማስከበር እና ማሟላት አንጻር የፖሊስ ኃላፊነት እና የህብረተሰቡ ሚና በሥልጠናው ላይ ተካተዋል፡፡

ሥልጠናውን የሰጡት በኢ.ፌ.ድ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ ትምህር እና ሥልጠና ዳሬክቶሬት ም/ረዳት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሆኑት አቶ ዮሐንስ ግርማ እና ረ/ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሆኑት አቶ ተክለ ልብሰወርቅ ሲሆኑ በቀጣይ ቀናትም በድሬዳዋ አስተዳደር ለሚገኙ የማኅበረሰብ ተወካይ እና የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሰጥ ተጠቁሟል ፡፡

Tagged Under: Attorney General • Capacity Building • civil liberties • Crime • Crime Prevention • Criminal Justice • dawa • dire • Dire Dawa • federal democratic republic of ethiopia (fdre) • fundamental rights • human • Human Rights • human rights training • integrated • Justice Ministry • Law Enforcement • National • national integrated crime prevention strategy • Police • police officers • Police Training • prevention • Rights • Rule of Law • Security • Stakeholder Engagement • strategic implementation • Strategy • Training
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች