ለፌዴራል ይቅርታ ቦርድ በሚቀርብ የይቅርታ አቀራረብ ረቂቅ መመሪያ ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ውይይት አካሄዱ

Stakeholders Discuss Draft Guidelines for Submission and Granting of Pardons to the Federal Pardon Board

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የይቅርታ ቦርድ ጽ/ቤት ከCenter For Justice የልማት ድርጅት ጋር በመተባበር ለፌዴራል ይቅርታ ቦርድ የሚቀርብ ይቅርታ አቀራረብና ይቅርታ አሰጣጥ ረቂቅ መመሪያ ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡

ከክልል ፍትሕ ጽ/ቤቶች፣ ከፌደራል እና ከክልል ማረሚያ ቤቶች፣ ከፌዴራል የጠበቆች ማህበር፣ ከፌዴራል ፍርድ ቤት፣ ከኤፌዴሪ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት፣ ከመከላከያ ሚኒስቴር የሕግ ዳሬክቶሬት፣ የተወከሉ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበትን መድረክ እንኳን ደህና መጣችሁ በሚል መልዕክት የስተላለፉት በፍትሕ ሚኒስቴር የይቅርታ ቦርድ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሰናይት እንየው እንዳሉት በይቅርታ አቀራረብና ይቅርታ አሰጣጥ ላይ ወጥነት ያለው የአሠራር ስርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችል መመሪያን ለማዘጋጀት የተከናወኑ ተግባራትን አስታውሰው በውይይቱ በይቅርታ አጠያየቅና በይቅርታ አሰጣጥ ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመለየት የተደረገ ጥናት እንዲሁም በጥናቱ መነሻነት የተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ግብዓትን ለማሰባሰብ ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ መድረክ በመሆኑ ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም ተሳታፊዎች ያላቸውን ልምድና ተሞክሮ በማካፈል ለረቂቅ መመሪያው አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ሀሳብና አስተያየቶችን በመስጠት ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

በመቀጠል የመክፈቻ ንግግር በማድረግ መድረኩን ያስጀመሩት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ እያሱ ቀለሜ በይቅርታ አቀራረብና ይቅርታ አሰጣጥ ረቂቅ መመሪያ የወንጀል ፍትሕ ስርዓቱን ግብ ለማሳካት እንዲረዳ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት ያለው የይቅርታ አሰጣጥ ስርዓት በሀገር ደረጃ ወጥና ተገማች እንዳይሆን የሚያደርጉ የአሠራር ልዩነቶች የሚስተዋሉበት መሆኑ በጥናት የተለየበትና ይቅርታ መስጠት የሚያስችሉ መስፈርቶች በግልፅ ያልተመላከቱበት፣ ይቅርታ የሚገባው ምን አይነት መስፈርቶችን ያሟላ ታራሚ ሊሆን አንደሚገባ በግልፅ ያልተለየበት ሁኔታ በመኖሩ እንዲሁም የይቅርታ አሰጣጥ ስነ-ስርዓቱን ማሻሻል አንደኛው የፍትሕ ዘርፉ የትራንስፎርሜሽን እቅድ በመሆኑ አጠቃላይ ማስተካከያዎችን በማድረግ ሊያሰራ የሚችል መመሪያ ማዘጋጀት ማስፈለጉን አመልክተዋል፡፡

አክለውም የይቅርታ አሰጣጥ መመሪያውን ወጥነት ባለው መልኩ አስተካክሎ ተግባራዊ ማድረግ መቻል ዜጎች በእኩልነት እንዲታዩ እና ማህበረሰቡ በፍትሕ ስርዓቱ ላይ እምነት እንዲኖረው ማድረግ እንዲሁም የፍትሕ ስርኣቱን በማሻሻል ረገድ አዎንታዊ ሚናን ስለሚይዝ የውይይት መድረኩ ተካፋዮች በቀረበው ረቂቅ መመሪያ ላይ ግብዓት ሊሆን የሚችል ሀሳብና አስተያየቶችን በመስጠት ኃላፊነቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

በዕለቱ በተያዘው መርሀ ግብር መሠረት ሲሰራበት የነበረውን የይቅርታ አጠያየቅና አሰጣጥ መመሪያ ያሉበትን ክፍተቶች በመለየት ክፍተቶችን አውቆ የማስተካከያ አማራጮችን ለማመልከት የሚረዳ ጥናት በፌዴራል፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ እና ትግራይ ክልሎች ባላቸው መመሪያ ላይ ዳሰሳ በማድረግ በጥናቱ የተገኙት ውጤቶች በባለሙያ እንዲቀረቡ ተደርጓል፡፡

በመጨረሻም ለፌዴራል ይቅርታ ቦርድ የሚቀርቡ የይቅርታ አቀራረብና ይቅርታ አሰጣጥ ረቂቅ መመሪያ ለውይይት ቀርቦ በተሳታፊዎች በኩል በርካታ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ አስተያየቶች ተሰጥተውበታል፡፡

Tagged Under: amnesty board Clemency Consultation correctional correctional facilities Criminal Justice System draft draft regulations facilities federal federal pardon board Federal Prison guidelines Justice Sector Reform legal Legal Professionals Legal Reform Pardon pardons Policy Development prison reform professionals Regional Justice Bureaus regulations stakeholder Stakeholder Consultation
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች