በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የትምህርት እና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት ከሐምሌ 18 እስከ 20/2017 ዓ.ም ለሶስት ቀናት የሚቆይ ለአመራሮች በስትራቴጂክ አመራር፣ ስትራቴጂክ እቅድ እና ለውጥ አመራር ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሁለተኛ ዙር አቅም ግንባታ ሥልጠና በአዳማ ከተማ በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡
ሥልጠናዉን በንግግር የከፈቱት በፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ፣ ትምህርት እና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸዉ ወርቁ ሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚሠራቸዉን የለዉጥ ሥራዎች ስኬታማ ለማድረግ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዉ የትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬቱ ባደረገዉ የፍላጎት ዳሰሳ ላይ ተመስርቶ አንደኛ ዙር የአመራር ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን ይህም የዛኛዉ አካል ነዉ ብለዋል::
ሥልጠናዉ በአንድ በኩል የአመራሮችን አቅም ለመገንባት ታስቦ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ለሚዘጋጀዉ የቀጣይ 5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ግብዓት ለማሰባሰብም ጠቃሚ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አያይዘውም ሥልጠናዉ ለተሳታፊዎች በስትራቴጂክ አመራር፤ ስትራቴጂክ ዕቅድ እና ለዉጥ አመራር ላይ በቂ ግንዛቤ መጨበጥ እንደሚያስችላቸዉ አክለዋል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሕ ስርዓት ማሻሻያ እና ለዉጥ አመራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኖህ ታከለ በበኩላቸዉ የአዉሮፓ ህብረት ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር ለሶስት ዓመታት የሚቆይ ስምምነት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም ህብረቱ የፍትሕ ስርዓቱን ለማሻሻል ተሸከርካሪዎችንና የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ከመስጠት ባሻገር በለዉጥ አመራር እና በስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በጥናት ለመለየት ትልቅ እገዛ አድርጎልናል ያሉ ሲሆን እየተሰጠ ያለዉ ይህ የአመራር ሥልጠናም ዋነኛ ግቡ ክፍተቶችን በመለየት አቅም መገንባት ነዉ ብለዋል፡፡