የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር በወንጀል ነገር ገብተው የተገኙ ሕፃናት ፍትሕ አስተዳደር ዙሪያ የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ዳኞችና አስተባባሪ ዳኞች፣የአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን አመራሮችና እና የዓቃቤ ሕግ የፅ/ቤት ኃላፊዎች የተሳተፉበት የፓናል ውይይት በዛሬው እለት በአዲስ አበባ አካሂዷል።
የሕፃናት ፍትሕ አስተዳደርን በተመለከተ ከሥልጠና በተለየ መልኩ ከዘርፋ ተዋንያኖች ጋር መወያየትና አመለካከት፣አደረጃጀትና አሰራሮችን ሊቀርፁ የሚችሉ ሀሳቦችን ማስቀመጥ አስፈላጊ በመሆኑ የፓናል ውይይቱ መዘጋጀቱ ተገልፆል።
በፍትሕ ዘርፍ የሶስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን እቅድ ከተካተቱ አምዶች ውስጥ የወንጀል እና የፍትሐ ብሔር ፍትሕ አስተዳደር አዲስ እይታ አንዱ መሆኑን ያስታወሱት በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) የፓናሉ ተሳታፊዎች በዚህ ቅኝት ውስጥ ሆነው እንዲወያዩ አሳስበዋል።
የወንጀል መበራከት እንደ አጠቃላይ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውጤት እንደሆነና ከዚህ አለፍ ብሎ በሕፃናት ላይ ሲበዛ ደግሞ የማህበረሰቡ ውድቀት መገለጫ አድርጎ መመልከት አስፈላጊ መሆኑን የገለፁት ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው በተለየ መልኩ ከቅጣት ባሻገር ሊማሩበት በሚችሉበትና የነገ አገር ተረካቢዎች መሆናቸውን ሊያረጋግጥ በሚችል መልኩ መታየት ይኖርበታል ሲሉ አክለዋል።
የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶቾ ዋና ዳይሬክተር አቶ አመሃ መኮንን በበኩላቸው ድርጅታቸው የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብት መከበር ያለውን አበርክቶ ለማስፋፋት ሲሰራ መቆየቱን ገልፀው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በተለይም ሕፃናት፣ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝና የዛሬው የፓናል ውይይትም የዚሁ ስራቸው አካል መሆኑን ገልፀዋል።
ቀጥሎም በወንጀል ድርጊት ገብተው የተገኙ ሕፃናት ፍትሕ አስተዳደር ከዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት አንፃር፣የምርመራ ክስና የፍርድ ሂደት በተግባር ያለው አካሄድ፣ተግዳሮትና መልካም አጋጣሚ የሚሉ እና በፍርድ ቤት በሚኖረው ሂደት በተግባር እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች የሚሉ የመወያያ ፅሁፎች በቅደም ተከተል ቀርበዋል።
የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች በቀረበው ጽሑፍ ላይ ውይይት ያደረጉ ሲሆን በወንጀል ድርጊት ገብተው የተገኙ ሕፃናት የፍትሕ አስተዳደር በተመለከተ እየተስተዋሉ ያሉ ክፍተቶችን ለማረምና የተሰጣቸውን ህገ መንግስታዊ ግዴታ ለመወጣት የፍትሕ አካላት እርሰ በርሳቸው በመናበብ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን ቀርፈው ለመፍትሄው በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አንስተዋል።
ተመሳሳይ የሆኑ የፓናል ውይይቱቶች በቀጣይም ከፍትሕ አካላት ጋር የሚደረጉ መሆኑ በመርሃ ግብሩ ላይ ተገልፆል።
ወጣት ወንጀል አድራጊዎች የሚባሉት እድሜያቸው 18 ዓመት ያልሞላ ሰዎች ሲሆኑ እነዚህ አካላት እድሜያቸው ከ9እስከ 15 የሆኑና ከ15 እስከ 18 ተብለው የሚከፈሉ ሲሆን እነዚህ ሕፃናት በወንጀል ድርጊት ገብተው ሲገኙ ምርመራቸውና የክርክር ሂደታቸው ለሕፃናት ጥቅም በሚመች መልኩ መታየት እንዳለበት በህገ መንግስቱና በወንጀል ፖሊሲው ተደንግጎ ይገኛል።