ደረጄ ካሳሁን የተባለ ተከሳሽ በሰው የመነገድ ድርጊት ለመፈፀም አስቦ ቀኑና ወሩ በውል ባልታወቀበት ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ልጁ የሆነችውን በግምት ከ7 እስከ 8 ዓመት እድሜ ያላትን የግል ተበዳይ ህፃን ገነት ደረጄን መንገድ ላይ አቅፎ በመቀመጥና የታመመች በማስመሰል ከሰዎች ብር በመለመን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቦሌ፣ ጀሞ፣ አየር ጤና እና ጦር-ኃይሎች አካባቢ በተደጋጋሚ ጊዜ በተለያየ ቀናት ከትምህርት ቤት በማስቀረት ጭምር የልመና ተግባር ላይ ያሰማራና መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም በግምት ከጠዋቱ 3፡00 ላይ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 አጉስታ ድልድይ አካባቢ የግል ተበዳይን የታመመች በማስመሰል አቅፎ ሲለምንባት ከልመና ካገኘው 3 ሺ 416 ብር ጋር እጅ ከፍንጅ የተያዘ በመሆኑ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 20ኛ ወንጀል ችሎት፣ በፈፀመው በሰው መነገድ ወንጀል ክስ አቅርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በክርክሩ ሒደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ የመከላከያ ማስረጃ ያሰማ ቢሆንም መከላከል ባለመቻሉ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ መሠረት ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ በ6 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራትና በ5 ሺ 500 ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ሲል ወስኖበታል፡፡