ፍትሕ ሚኒስቴር ከአለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራረመ

Ministry of Justice Signs Cooperation Agreement with the International Organization for Migration

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ህዳር 13 ቀን 2ዐ16 ዓ.ም. ከአለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ጋር በፍልሰት አስተዳደር ጉዳይ የትብብር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

የትብበር ስምምነቱ በፍልሰት አስተዳደር፣ በሠራተኛ ፍልሰትና የመዘዋወር ነጻነት፣ በድንበር አስተዳደር፣ በዲያስፖራ ተሳትፎ፣ መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት፣ በግዳጅ ፍልሰት፣ በወንጀል መከላከልና ሕግ ማስከበር፣ በፍልሰተኞች ጥበቃ እና ተያያዥ ጉዳዮች የሀገሪቱን ህጎች፣ ፖሊሲዎችና ተቋማዊ አሠራሮች መሠረት በማድረግ በትብብር ለመሥራት የሚያስችል ማዕቀፍ ለማጠናከር ያለመ ነው፡፡ በስምምነቱ የፊርማ ስነ-ሥርዓቱ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ስምምነቱን አስመልክቶ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ባደረጉት ንግግር ዓለም ዓቀፉ የፍልሰት ድርጅት የብሔራዊ ትብብር ጥምረት ፅህፈት ቤት በፍልሰተኞች ዙሪያ በሚያከናውናቸው ተግባራት የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ እንደቆየ አስታውሰዋል፡ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ምክንያቶች በዋናነት የተሻለ ሥራና ኑሮ ፍለጋ ወደ ተለያዩ ሀገራት መደበኛና መደበኛ ባልሆነ መንገድ ይጓዛሉ፤ ስለሆነም አብዛኞቹ ወደውጭ አገራት የሚፈልሱ ዜጎቻች መደበኛውን መስመር ከመከተል ይልቅ መደበኛ ያልሆነውን መንገድ በመጠቀም ጉዞ እንደሚያደርጉ እና በዚህም ለአስከፊ ጥቃትና ሰቆቃ እየተዳረጉ መሆኑን በማስመር የትብበር ስምምነቱ ለብሔራዊ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤቱ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን እንዲሁም በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን ለመቀነስ ብሎም በእነዚህ የወንጀል ድርጊቶች የሚሳተፉ አጥፊዎችን በሕግ እንዲጠየቁ ለማስቻል ያለመ ስምምነት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ ኃላፊ ማዳም ቺፍ አቢባቶ ዋኔ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ፍልሰትን በአግባቡ በማስተዳደር ረገድ የሕግ እና የአደረጃጀት ማዕቀፎች በመዘርጋት ሰፊ ሥራዎችን በመሥራት ላይ የምትገኝና ለዚህም የፍትሕ ሚኒስቴር የመሪነት ሚና የሚደነቅ መሆኑን አውስተዋል፡፡ አያይዘውም ፍልሰት በአግባቡ ማስተዳደር ከተቻለ ጠቀሚ፣ ባግባቡ መምራት ካልተቻለ ግን ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑን ጠቁመው ድርጅታቸው መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን፣ በሰው የመነገድ፣ ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመቀነስ ከፍትሕ ሚኒስቴር እና ሚኒስቴሩ በሚመራው ትብብር ጥምረት ሥር ከተደራጁ የሥራ ቡድኖች ጋር በጋራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን መንግሥት በተጎጂዎች መልሶ ማቋቋምና የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው አለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት በዚህ ረገድ እገዛና ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ ወ/ሮ ሁሪያ አሊ በበኩላቸው ዜጎችን ለፍልሰት የሚያነሳሱ ምክንያቶችን በመለየት በዚሁ ዙሪያ የሚያጠነጥን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መስጠት እንደሚያስፈልግ አውስተዋል፡፡

በመጨረሻም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስስር ዴኤታ ክቡር አቶ አለም አንተ አግደው ከአለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ ኃላፊ ከሆኑት ማዳም ቺፍ አቢባቶ ዋኔ ጋር የስምምነት ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡

Tagged Under: Bilateral Agreement border border management cooperation agreement Crime Prevention development cooperation diaspora diaspora engagement engagement financial assistance forced forced migration Human Trafficking international international organization for migration (iom) iom irregular Irregular migration labor labor migration Law Enforcement management Migration Migration Management organization Police Refugee Protection Security Smuggling Technical Assistance
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች