የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ለፌዴራል ተቋማት በሚሰጣቸዉ የኦንላይን አገልግሎቶች ዙሪያ ከተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ለተዉጣጡ የሕግ ክፍል የስራ ሀላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡
ፍትሕ ሚኒስቴር በአዋጅ ከተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት መካከል በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር፣በፍትሃብሄር የሕዝብንና የመንግሥትን ጥቅም ማስከበር፣በሰብዓዊ መብቶች እና በሌሎች ተግባራት ለተገልጋዮች አገለግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ የገለፁት የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ መዝሙር ያሬድ፤ እነዚህ ተቋማት ካሉበት ሆነዉ አገልግሎቱን እንዲያገኙ የሚያስችል የኦንላይን አገልግሎት ሲስተም ወደ ስራ መግባቱንና በዚህ ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር የአጠቃቀም ዉስንነትን ለመቅረፍ ታስቦ ሥልጠናዉ መዘጋጀቱን ተናግረዉ ፍትሕ ሚኒስቴር በቀጣይም የሚሰጣቸዉን አገልግሎቶች ዲጅታላይዝድ በማድረግ የማንዋል አሠራርን ማስቀረት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በዚህ የኦንላይን አገልግሎት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የሚመጡ የሕግ ማርቀቅ ፣ ህጎች ላይ ጥናት ማድረግ ፣ እርማት፣ በመመሪያዎች ላይ አስተያት መስጠትና እንዲመዘገቡ ማድረግ ፣የፍትሃብሔር ጉዳዮችን ሚመለከቱ አገልግሎቶች ለአብነትም የዉል ጉዳዮች እንዲሁም በፌዴራል ህጎች ተፈፃሚነት ክትትል በማድረግ ግብረ መልስ መላክ የሚያስችሉ አገልግሎቶች የተካተቱ ሲሆን በነዚህ አገልግሎቶች ዙሪያ ከዳይሬክቶሬቶች በመጡ ባለሙያዎች ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን የተግባር ላይ ሥልጠናዉን ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ዳይሬክቶሬት ባለሙያዎች ሥልጠናዉ ተሰጥቷል፡፡