የፍትህ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ አመራሮች በሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ማስተግበሪያ ረቂቅ የህግ ማዕቀፎች ዙሪያ ተወያዩ

Ministry of Justice Leaders Discuss Draft Legal Frameworks for Transitional Justice Policy

የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር የሆኑት ክብርት ወ/ሮ ሃና አርዓያስላሴን ጨምሮ የፍትሕ ሚኒስቴር ማኔጅመንት አባላት በተገኙበት በሽግግር ፍትሕ ረቂቅ የሕግ ማዕቀፎች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡ የሕግ ረቂቅ ዝግጅት የባለሙያዎች ቡድን አባላትም የሕግ ረቂቆቹን ለአመራሩ ያቀረቡ ሲሆን ከህጎቹ እና ድንጋጌዎቹ በስተጀርባ ያሉትን መሠረታዊ ጉዳዮች እና አመክኔዎችም አብራርተዋል፡፡

በውይይቱ የቀድሞ የፍትሕ ሚኒስትር በአሁኑ ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር የሆኑት ክቡር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ በመድረኩ ተገኝተው በረቂቅ የሕግ ማዕቀፎቹ ዙሪያ የግል ምልከታቸውን ለባለሙያዎች ቡድኑ አጋርተዋል፡፡

በመድረኩ መልዕክታቸው ያስተላለፉት ክብርት ወ/ሮ ሃና አርዓያስላሴ የሕግ ማርቀቅ ቡድኑ አባላት ከብዙ ጥረት በኋላ ረቂቅ ህጎቹ አሁን የያዙትን ቅርጽ እና መልክ እንዲይዙ ላደረጉት ጥረት አመስግነው ከመድረኩ የሚገኙትን አስተያየቶች እንዲሁም በቀጣይ በሰፊው ከሚካሄዱት የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮች የሚገኙ ሃሳቦችን በግብዓትነት በመውሰድ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን አቅጣጫዎች የሚያሳኩ ወይም እውን የሚያደርጉ የሕግ ማዕቀፎችን አዘጋጅተው እንደሚያስረክቡ እምነት እንዳላቸው ገልጸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርቡለትን እኝህን ህጎች ባልዘገየ ጊዜ ተወያይቶ በማጽደቅ ወደ ትግበራ ምዕራፍ እንደሚያሻግራቸውም እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡

ውይይት የተደረገባቸው የሕግ ማዕቀፎች፣ የዓለም አቀፍ ወንጀሎች ረቂቅ አዋጅ፤ የልዩ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ፣ የልዩ ችሎት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ፤ የእውነት እና እርቅ ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ እና የተቋማት ማሻሻያ ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ሲሆኑ የሕግ ረቂቆቹን ጥራት እና ተፈጻሚነት የሚጨምሩ ግብዓቶች ከውይይቱ ተገኝተዋል፡፡

Tagged Under: MinistryOfJustice
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች