በፍትሕ ሚኒስቴር የፕሮጀክት አስተዳደር፣የለውጥ አስተዳደር፣የስትራቴጂክ እቅድ እና አመራር ላይ ትኩረቱን ያደረገ ጥናት በሁለት አማካሪ ድርጅቶቸ አማካኝነት ተጠንቶ የተቋሙ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በተገኙበት ውይይት ተካሂዶበታል።
በዚህ ወቅት በመድረኩ ተገኝተው ውይይቱን የከፈቱት በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ኤርምያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) የለውጥ አስተዳደር፣የፕሮጀክት አስተዳደር፣ስትራቴጅክ እቅድና አመራር ወሳኝና ዘመኑን የዋጁ ጉዳዮች መሆናቸውን አንስተዋል።
በመሆኑም እነዚህ ጉዳዮች ተቋሙ በሕግ የተሰጠውን ተልእኮ ለማስፈፀምና ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉና ለዚህም ጊዜው የሚጠይቀውን አሠራር፣ግንዛቤና ክህሎት ሊኖረው እንደሚገባም አክለው ውይይቱም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ በመነሳት ፍትሕ ሚኒስቴር ውጤታማ በሆነ መልኩ የለውጥ አስተዳደሩን እንዲመራና በስትራቴጅክ እቅዱ እንዲቃኝ ሳይንሳዊ በሆነና ስታንዳርዱን ባሟላ መልኩ አገልግሎቱን እንዲሰጥ ታስቦ ጥናቱ እንዲሰራ መደረጉን ገልፀዋል።
በመሆኑም ጥናቱ ሲካሄድ በመረጃ ሰጭነት የተሳተፉ የተቋሙ አካላት የጥናቱ ግኝት የሚያሳየውን የተቋሙን ቁመና ተገንዝቦ የበለጠ በመረዳት በቀጣይ ምን ማድረግ አለብን የሚለውን ጥያቄ በመመለስና ወደየስራቸው በመውሰድ የአሠራር ሥርዓትና አደረጃጀት ለመቅረፅ ግብአት ሊያደርጉት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ቀጥሎ የጥናቱ ግኝት አስተያየትና ምክረ ሀሳቦች ጥናቱን በሰሩት አማካሪ ድርጅቶች አማካኝነት ቀርቦ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎበታል።
ውይይቱን የመሩት የፍትሕ ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በአራቱ ጉዳዮች የቀረቡ ጥናት ግኝቶች ተቋሙ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ የሚያመላክቱና ጥሩ ግንዛቤ የተገኘባቸው ብሎም ግብአት መሆን የሚችሉ መሆናቸውን አንስተዋል።
ከግኝቶቹ በመነሳት ወደፊት ምን መደረግ እንዳለበት በጥናቱ ከተመላከቱ ምክረ ሃሳቦች በተጨማሪ የውይይቱ ተሳታፊዎች በርከት ያሉ እና ግብአት ሊሆኑ የሚችሉ ሀሳብ አስተያየቶችን እንዲሁም ግልፅ ሊደረጉ የሚገቡ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
በመጨረሻም አጠቃላይ ከጥናቱን ውጤቶች በመነሳት የውይይቱ ተሳታፊዎች ወደስራ ሲመለሱ በቀጣይ ሊያከናውኗቸው የሚገቡ ተግባራትና የስራ አቅጣጫ በክቡር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አማካኝነት የተሰጠ ሲሆን፣ በተለይም የለውጥ አስተዳደርና የስትራቴጅክ እቅድ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከተነሱ ግኝቶች በመነሳት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አደራ ብለዋል።
በቀጣይም ከጥናቱ ግኝት በመነሳት የሥልጠና ማንዋሎች ተዘጋጅተው ለሚመለከታቸው ከካላት ሥልጠና እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።
ጥናቱ ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በተቋሙ የንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት የተሰራ መሆኑ ተገልፆል።