የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶችና ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን (March 8 ) ከተጠሪ ተቋማት ጋር መጋቢት 11 ቀን 2016 ዓ.ም በፓናል ውይይት አክብሯል፡፡
የፓናል ውይይቱን በንግግር የከፈቱት በፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶችና ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ዳግማዊት አለምኔ የሴቶች ቀን ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ113ኛ ጊዜ ሲከበር መነሻውንና ዓላማውን ስናስብ በወቅቱ የነበሩ ሴቶች መማር አትችሉም ፣ መምረጥ አትችሉም ፣ ስራ ሰርተው እንኳን ክፍያ አትከፈሉም ይባል እንደነበር አውስተው ሴቶች በጣም ታግለውና ብዙ ዋጋ ከፍለው ዛሬ መምረጥና መመረጥ የቻልነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም እኛ ዛሬ ተምረን ብዙ ነገር ማድረግ የቻልነው በዚያን ጊዜ በነበሩ ሴቶች ተጋድሎ ነውና ለበዓሉ የምንሰጠው ትርጉም ከፍያለ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሯ አክለውም ዛሬ ይህንን በዓል “ሴቶችን እናብቃ ልማትና ሰላምን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ቃል ስናከብር በየተቋሞቻችን የተቋቋሙት የሴቶችና ማኅበራዊ ክፍሎች ተቋሙ ውስጥ ካሉ ሴቶች ባለፈ ለአገልግሎት የሚመጡ ሴቶችን ሕፃናትንና አረጋዊያንን መጥቀም የሚችሉበት ሁኔታ የተደራጁ ናቸው ወይ? አቅማቸውስ ምን ያህል የተጠናከረ ነው? የሚለውን ፈትሸን ብናልፍ ሴቶችን ለማብቃት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልፀዋል፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ወ/ሮ ፀሐይ ሽፈራው በበኩላቸው በኢትዮጵያ የሴቶች መብት ጥያቄ ከ150 ዓመት በፊት መጀመሩን ጠቁመው በየጊዜው ለውጦች ቢኖሩትም እስከ አሁን ድረስ የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን ገልፀዋል፡፡ ሁላችንም ሴቶች አንድ በመሆን ጠንክረን በመሥራት አቅማችንን ማሳየት ይገባናል ያሉት ወ/ሮ ፀሐይ ሴቶችን በሚመለከት በተቋማቸው ያላቸውን ተሞክሮ አጋረተዋል፡፡
በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካቶ ትግበራ የተቋማት ማብቃት ባለሙያ በአቶ አበበ ሃይማኖት የአካቶ ትግበራ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ መዋቅር ተግባርና ኃላፊነትን አስመልክተው ለውይይት መነሻ ሰነድ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ቀጥሎም ከተሳታፊዎች በተነሱ ሃሳቦች፣ አስተያየት እና ጥያቄዎች ላይም ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (March 8 ዘንድሮ “ሴቶችን እናብቃ ልማትና ሰላምን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ113ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶት ተከብሯል፡፡